Homeነፃ አስተያየትየአገራችን ፕሬዚደንት በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ አንድ ኃያል መንግስት የበላይነቱን ለማስፈን ጥረት...

የአገራችን ፕሬዚደንት በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ አንድ ኃያል መንግስት የበላይነቱን ለማስፈን ጥረት የሚያደርግ ከሆነ የሰላም እጦት ሊኖር ይችላል ሲል ምን ሊለን ፈልጎ ነው!

Advertise Here
Advertise here

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ጥቅምት 8፣  2019 

የኢትዮጵያው ፕሬዚደንት ተብዬው አቶ ታዬ አተስከ ስላሴ ባለፈው መስከረም ወር 2026 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ዓመታዊ ስብሰባ ጉባዔ ላይ አፄ ኃይለስላሴ በ1963 ዓ.ም እንደዚሁ ዐይነቱ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን ንግግር በመጥቀስ በዓለም ላይ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው አንድ ኃያል መንግስት ጥንካሬውን በመተማመን በሌሎች አገሮች ላይ የበላይነቱን ለማስፈን  ሙከራ ሲያደርግ ሳይሆን በመከባበርና በመተባበር ሲሰራ ብቻ ነው ያሉትን በመጥቀስ በተዘዋዋሪም ቢሆን ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላም እጦትና ለጦርነት መቀስቀስ ኃያል መንግስት ነኝ የሚለው ተጠያቂ እንደሆነ ለማሳሰብ ሞክሯል። ይሁንና የኢትዮጵያው ፕሬዚደንት አቶ ታዬ የሚረሳው ነገር በዓለም ታሪክ ውስጥ፣ በተለይም ካፒታሊዝም የበላይነትን ከተጎናጸፈበት ጊዜ ጀምሮ መሰሪህ የሆኑ ልዩ ልዩ መንገዶችን በመፈለግ እንደኛ የመሳሰሉ በኢኮኖሚ ባላደጉና የምሁራዊ መሠረታቸውም ደካማ የሆኑ አገሮችን ልዩ ወጥመድ ውስጥ በመክተት የባሰ እንዲዳከሙና፣ እንደ ሃይማኖትና የጎሳ የመሳሰሉ ጉዳዮችን በመጠቀም ርስ በርሳችን እንድንበላላና የሰላምም እጦት እንዲኖር ማድረጉን ነው። በተለይም ከ1945 ዓ.ም በኋላ የተፈጠረውን የዓለም ሁኔታና፣ አንድ ኃያል መንግስት ነኝ የሚል የበላይነቴን ተቀዳጅቻለህ ካለበት ጊዜ ጀምሮ የዓለም አቀፍን ፖለቲካ ሁኔታ ለተከታተለ ወይም ላጠና የከፋፍለህ ግዛውን ፖለቲካ የሚከተለውና ለሰላምም እጦት ጠንቅ የሚሆነውና የሚሆነው ሰለጠንኩኝ የሚለው የነጩ ኦሊጋርኪ መደብ፣ በተለይም የአሜሪካኑ የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የስለላ፣ እንዲሁም በኒዎ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ የሚመራው የነጩ ኤሊት ብቻ ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ እንደኛ የመሳሰሉ አገሮችና መንግስታት ሊገነዘቡ የማይችሉት ነገርና ከመንፈሳቸውም ጋር ሊዋሃድ የማይችለው ነገር አንድ አገርና ህዝቡም ብሄራዊ ነፃቱን ሊያስከብር የሚችለው አገዛዙ ተግባራዊ በሚያደርገው በሳይንሳዊ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ወደ ውስጥ ያተኮረ ሁለ-ገብ የሆነ የአገርና የህብረተሰብ ግንባታ ተግባራዊ ሲያደርግ ብቻ መሆኑን ነው። በተለይም ከአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ጊዜ ጀምሮ የተዘነጋው ነገር ወደ ውስጥ ያተኮረና ህዝባችንን የመንፈስ ጥንካሬ ሊሰጠውና ራሱን እንደ አንድ ህዝብ በመቁጠር ሁሉንም ሊያሰባስብ የሚችል ሁለ-ገብ የሆነ የህብረተሰብ ግንባታ አትኩሮ አለመሰጠቱ ነው። ከዚህም በላይ ከፍተኛ የሆነ የምሁራዊ ድክመት ቀድሞም ሆነ ዛሬም ስላለ አንድ አገርና ህዝብ በምን መሰረት ላይ ቢቁሙ ነው በቀላሉ ብሄራዊ ነፃነታቸው የማይደፈረው ወይም የሚከበረው በሚለው ላይ በፍጹም ጥናት፣ ውይይትና ክርክር ሰለማይካሄድ ህዝባችን ግራ ተጋብቶ ይገኛል፤ ማንም ኃይል ወይም ግለሰብ እየተነሳ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር እንደፈለገው የሚፈነጭበት መድረክ ለመሆን በቅቷል።  በተለይም ድሮም ሆነ በአሁኑ ወቅት በአገርም ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰበጣጥሮ የሚገኘው ምሁር ነኝ ባይ በጣም ተዕቢተኛና ንቀት በተሞላበት መንፈስ ስለአገርና ለህዝብ ደንታ የሚሰጠው ባለመሆኑ አገራችንና ህዝባችን እንደ አሜሪካን በመሳሰሉት ኃያል ነኝ ባይ መንግስታት እንዲናቅ ለመደረግ በቅቷል።

ይህንን በሚመለከት ከአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ጀምሮ የተሰሩ መሠረታዊ ስህተቶች አሉ። እንደሚታወቀው የአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ምሁራዊ መሠረቱ በጣም ደካማ ስለነበር አንድ ህብረተሰብ ከታች ወደ ላይ ርስ በርሱ በመያያዝ (Organically) እንዴት እንደሚገነባና እንደሚጠነክር የተረዳ አልነበረም። በአፄው ዘመን ተግባራዊ የሆኑትን እንደትምህርትና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ስንመረምር በፍጹም ለህብረ-ብሄር ግንባታና መጠንከር የሚያመቹ አልነበሩም። በአጠቃላይ  የትምህርቱን ከሪኩለሙን ስንመረመር የትምህርቱ አቀራረጽ ዓላማው ለምን እንደሆነ በፍጹም አይታወቅም ነበር፤ አሁንም አይታወቅም። ዝም ብሎ ለመማር ወይስ የመጨረሻ መጨረሻ አገራችንን በሁሉም አቅጣጫ እንደ ሙሉ ማህበረሰብና ህብረ-ብሄር ለመገንባት ያስችላል? ተብሎ ነው የተቀረፀው ወይስ ዝምብሎ ሸምድዶ ፈተና ካለፉ በኋላ የመጨረሻ መጨረሻ የምስክር ወረቀት ተቀብሎ ለመውጣት? ከዚህ ስንነሳ የትምህርቱ ይዘት ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት፣ ለከተማዎች ግንባታ፣ ሰፋ ላለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ለተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚና፣ ከዚያም አልፎ በመሄድ በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ ባህላዊ እንቅስቃሴን ለማዳበር የሚያስችል እንደሆነ በፉጹም አይታወቅም ነበር፤ አሁንም አይታወቅም።  ከዚህም በላይ የትምህርት ይዘቱ ራሳችንን እንዳንውቅና ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ በመጠየቅ ፈጣሪ ሊያደርገን በፍጹም አልቻለም። መንፈሳዊ ጥንካሬ በመስጠት ወደ ውስጥ የተረጋጋና ሰላማዊ የሆነ ማህበረሰብ እንድንገነባ በፍጹም አላስቻለንም። ሰብአዊና ማህበራዊም በፍጹም አላዳረገንም።  እንደምናየው የተምህርት አሰጣጡ በፍጹም በተለያየ መልክ የሚገለጸውን የአገራችንን ችግር ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያስችለን አልነበረም፤ አሁንም አይደለም። በአንፃሩ በተቆነፀለ መልክ የገባውና የተስፋፋው ትምህርት ትዕቢተኞችና አመፀኞች ነው ያደረገን። ይህ ብቻ ሳይሆን በራሳችን እንዳንተማመንና በውጭ ኃይሎች፣ በተለይም የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝምን አፍቃሪና ለእሱም ሰጋጅ እንድንሆን ነው ያደረገን። በተለይም የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ ያላት አገር  ናት ተብላ በምትጠራው አገር እንደዚህ ዓይነት መንፈሱ በጣም ደካማ የሆነ ኤሊት ኃይል መፈጠሩ በጣም ያሳዝናል።

ወደ መንግስቱ የመኪና አወቃቀር ጋ ስንመጣ ብሄራዊ ነፃነትን ለማስጠበቅ ተብሎ ደረጃ በደረጃ የተዋቀረና የተገነባ አልነበረም፤ አይደለምም። በዚህ ላይ የመንግስቱን የመኪና አወቃቀር ስንመረምር ከወታደሩ እስከፀጥታ ኃይሉ ጀምሮና እስከ ሲቪል ቢሮክራሲው ድረስ ያለውን አሰለጣጠንና አደረጃጀት ስንመለከት የአሜሪካን፣ የእንግሊዝና የእስራኤል ተፅዕና ከፍተኛ ነበር፣ አሁንም ነው። እንደሚታወቀው በውጭ ኃይሎች በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚሰለጥኑ እንደወታደርና እንደፀጥታ የመሳሰሉ ኃይሎች በቀላሉ የመታለል መንፈስ ስላላቸው ብሄራዊ ስሜታቸው በጣም ደካማ ነው። ከዚህም ባሻገር አፄ ኃይለስላሴ ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አንድ ጋሽ መሬት የሚያክል ለኤምባሲ ግንባታና መቀመጫ የሰጡት ቦታ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አዲስ አበባና፣ የኋላ ላይ ደግሞ አስመራ ላይ የገነባው የጦር ካምፕ እንደልቡ እንዲፈነጭና ከውስጥ ሆነው አገራችንን የሚሰረስሩ ሰላዮችን ለማስልጠን አመጪ ሁኔታ ፈጥሮለታል። ይህ ዐይነቱ አገርን ከውስጥ የመቦርበርና ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም መሰለልና ማገልገል በአብዮቱ ወቅት ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው። በተለይም በቀይ ነጭ ሽብር ዘመን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ያሰለጠናቸውን ሰላዮች በመጠቀም ብሄራዊ ባህርይ ያላቸውና ተራማጅ ኃይሎች እንዲገደሉ ለማድረግ በቅቷል። ከዚህም በላይ ጋፋት ላይ በሰሜን ኮሪያ ድጋፍ በመገንባት ላይ የነበረው የጦር መሳሪያ ፋብሪካ በዚያው እንዳይቀጥል ለመደረግ በቅቷል። በዚያን ወቅት ይህ ዐይነቱ የጦር መሳሪያ ፋብሪካ ግንባታ በአንዳንድ የኢትዮጵያ የሚሊተሪና የስለላ ሰዎች ለአሜሪካን ኢምፔሬያሊዝም ባይሰልሉና መረጃም አሳልፈው ባይሰጡ ኖሮ ኢትዮጵያ በአሁኑ ውቅት እንደ ባሊስቲክ ሚሳይል የመሳሰሉትን የጦር መሳሪያዎች የመስራት አቅሟ ከፍ ያለ ይሆን ነበር። የጦር መሳሪያን ፋብሪካ የማክሸፍ ጉዳይ አስመልክቶ በአንድ አገር ወዳድ መኮንን መጽሀፍ ተጽፏል። ለማንኛውም ይህ ዐይነቱ የኢምፔሪያሊዝምን፣ በተለይም የነጭ ኦሊጋሪኪውን እንደ አጋር ወይም ወዳጅ አድርጎ አምኖ የመቀበልና በአገራችን ምድር እንደፈለገው እንዲፈነጭ ማድረግ ለ50 ዓመታት ያህል በአገራችን ምድር ለሚታየው የርስ በርስ መጋጨትና የጎሳ ፖለቲካ የሚሉት ፈሊጥ ማቆጥቆጥና የራስ ምታት መሆን ሁላችንም በጋራ በመነሳሳት አንድ የተከበረና የጠነከረ አገር እንዳንገነባ አድርጎናል።  የሲቪል ቢሮክራሲውንም ሁኔታ ስንመለከት በተለይም በኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ያልሰለጠነ ስለነበር ወደ ውስጥ ያተኮረ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ፓሊሲ እንዴት እንደሚተገበር የሚያውቀው ነገር ስላልነበር ዝም ብሎ ብቻ የውጭ ትዕዛዝን በመቀበል ድህነትን የሚፈለፍል ወይም የሚያመርት የተራ የቴክኖክራቲክ ፖሊሲ በማውጣት ነው እንዲተገበር ያደርግ የነበረው። ስለሆነም ኢ-ሳይንሳዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በመሆኑ በቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረና በኢንዱስትሪ ተከላም ሊሰማራ የሚችል የከበርቴ መደብ ብቅ ሊል አልቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ህዝቡን ሊያስተሳስር የሚችል ጠንካራ የሆነ የውስጥ ገበያ ሊገነባ አልተቻለም። ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችም እዚህና እዚያ በመቋቋም ለስራ ፈላጊው ወጣት የስራ መስክ ዕድል መክፈት አልተቻለም። ስለሆነም የውስጥ ገበያው በዐይነትም ሆነ በስፋት ለማደግና ህብረተሰቡን ለማያያዝ በፍጹም አልቻለም።

ይህ ዐይነቱ ሁኔታና ከትምህርት መስኩና ከመንግስት መኪናው አወቃቀር ጋር የነበረው በጣም ደካማ ሁኔታ ለውጭ የስለላ ኃይሎች በጣም የሚያመች ነበር። የመጨረሻ መጨረሻም የአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ሊወድቅ የቻለው በሰራው ታሪካዊ ስህተትና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረቱ በጣም ደካማ ስለነበር ነው። አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ የተፈጸመውን ምስቅልቅል ሁኔታ ስንመለከት በአብዮቱ ወቅት የተሳተፈውና የመሪነቱን ቦታ የያዘው ኃይል በሙሉ ሁኔታዎችን በደንብ ያጠናና በቅደም ተከተል ምን ምን እርምጃዎች ተግባራዊ ቢሆኑ ነው? ጠንካራ የሆነ አገርና ህዝቡንም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ከድህነት ሊያላቅቀው የሚችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለተገበር የሚችለው? በሚለው ላይ ግንዛቤ ስላልነበርና ቅድሚያም የተሰጠው ስላልነበር የአብዮቱ ግንባር ቀደም ኃይል ነኝ የሚለው ቅድሚያ የሰጠው ስልጣን ላይ ወጥቶ ቁጥጥ ለማለት ብቻ ነበር። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ኢ-ፖለቲካዊ የሆነ አስተሳሰብና አካሄድ ለምሁራዊ ውይይትና ለጠንካራ የምሁር ኃይል መዳበር አመቺ ሁኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ በቃ። በተለይም እንደ ኢህአፓ ከመሳሰሉት እጅግ አደገኛ ኃይሎች የተሰነዘረው ጥቃት አገሪቱን ሊያዳክምና ሊበታትን የሚችል ሁኔታ ተፈጠረ። ኢህአፓ ጠለቅ ላለ ጥናትና ምሁራዊ ውይይትና ክርክር ቅድሚያ ባለመስጠቱና ያለ የሌለ ኃይሉን በመጠቀም ይቀናቀኑኛል የሚላቸውን ተራማጅ ኃይሎች በመጨረስ የግዴታ ስልጣን መያዝ አለብኝ ብሎ ስለተነሳ ለእንደዚያ ዐይነት የርስ በርስ መጨራረስ መንገዱን ከፈተ። ይህ በራሱ በየቦታው ጎጠኛ ኃይሎች ብቅ ብቅ እንዲሉና እንዲጠናከሩ የበኩሉን አመቺ  ሁኔታን ፈጠረላቸው። እነዚህ ጎጠኛ ኃይሎችና ብሄራዊ ባህሪ አለን የሚሉ ሁሉ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም መሳሪያና መጫወቻ በመሆን አገራችንና ህዝቦቿን በጣም ሊያዳክሟት ቻሉ። ደርግም በራሱ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ፖለቲካዊ በሆነ መልክ ከማየትና ነገሩ ረገብ እንዲል የተሻለ ስልት ከመከትል ይልቅ አመጽን በአመጽ መመለስ ያስፈልጋል በሚለው ፈሊጡ በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣት ልጆች በግፍ እንዲገደሉ አደረገ። ይህ ዐይነት የአመፀኝነት መንፈስና የርስ በርስ መገዳደል የፖለቲካ ክፍተትን ፈጠረ። ይህንን ክፍተት በመጠቀም ነው ሻቢያና ወያኔ በአሜሪካን የስለላ ኃይል በመደገፍ ስልጣን ላይ ለመውጣት የበቁትና አገራችንን እንደፈለጋቸው ለመበወዝ የቻሉት። ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተግባራዊ ያደረገው የጎሳ ፊዴራሊዝምና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አገራችንን እንደ ነቀርሳ በሽታ ሊሰረስራት ቻለ። በተጨባጭ ሲታይ የወያኔ አገዛዝ የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም አሻንጉሊት የሆነ አገዛዝ ነበር። እነሱ የሚፈልጉትን የከፋፍለህ ግዛውን ፖሊሲ በመጠቀምና ተግባራዊ በማድረግ ነው ውስጣዊ ጥንካሬ እንዳይኖርን ያደረገው። ይህ ዐይነቱ ከምሁራዊ ብስለት እጥረት የተካሄደ የአሻጥረኞች ፖለቲካና ቂምበቀል የተሞላበት አካሄድ የመጨረሻ መጨረሻ አገራችንን በሁሉም አቅጣጫ ነው ሊያዳክማት የቻለው። የባህል እሴት እንዳለ እንዲጠፋ ነው ለመደረግ የበቃው። ከዚህም ጋር ተያይዞ አገራችን በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ የባህል መድረክ ከማድረግ ይልቅ ወደ ብልግና መድረክነት በመለወጥ ነው የፈረንጆች መጫወቻ ለመሆን የበቃችው።

አቢይ አህመድ ስልጣኑን ከያዘ ጊዜ ጀምር የወያኔን ፖሊሲ ልዩ ጥልቀት በመስጠት ነው ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ቅራኔ እንዲባባስ ለማድረግ የበቃው። አቢይ አህመድና አገዛዙ በአማራው ወገናችንና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ የከፈቱት ጦርነት አገራችንን ክፉኛ አዳክሟታል። በተጨባጭ ሲታይ የአቢይ አህመድ አገዛዝ የሴተኛ አዳሪ አገዛዝ ነው ማለት ይቻላል። ፖሊሲውና ፓለቲካው ለተባበሩት የአረብ ኢሚራትና ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነት መንፈስና በአገራችን ምድር ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚያስችላቸው ነው። አቢይ አህመድና አገዛዙ የሚከተሉት ፖለቲካና ፖሊሲ በምንም ዐይነት እሱ እንደሚለው የኦሮሞን ብሄረሰብ የበላይነት ያሰፈነ ሳይሆን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተባበሩት የአረብ ኢሚራት በአገራችን ፖለቲካ ላይ የበላይነት እንዲኖራቸው ያደረገና ተፅዕኖም ለማሳደር የቻለ ነው። የኦሮሞ ኤሊት ነኝ ባዩና፣ በተለይም “የፕርቴስታንት ሃይማኖት አማኝ ነኝ” የሚለው በጥራዝ ነጠቅ መንፈሱ በሚያካሂደው ዕውቀተ-አልባና ከሳይንስ ጋር የማይጣጣም ፖለቲካ እወክለዋለሁ የሚለውን የኦሮሞ ብሄረሰብ ያደነቆረና ግራ ያጋባው ነው። በተለይም መታወቅ ያለበት ጉዳይ ለውጭ ኃይሎች ተገዢ በመሆንና የእነሱን አጀንዳ በማራመድና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ እወክለዋለሁ የሚለውን ብሄረሰብ በፍጹም ነፃ ማውጣት አይቻልም። እነ አቢይ አህመድ ሳይገባቸው በብላጣብልጥነት ወይም በሽወዳ መልክ የሚያካሄዱት ፀረ-ሳይንስ ፖለቲካ የኦሮሞ ብሄረሰብ የሚባለውን ብቻ ሳይሆን አገራችንን እንዳለ እያዳከመና ህዝባችንንም አቅጣጫውን እንዲያጣ እያደረገው ነው። አቢይ አህመድና አገዛዙ፣ እንዲሁም በእሱ ዙሪያ የተሰባሰበው የሃይማኖት ሰባኪ ኤሊት ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የአፍሪካ ህዝብ ጠንቆች  ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ በጊዜያዊ ጥቅም በመታለልና ጭንቅላትን እንዳለ በመሸፈን በአገራችን ምድር ላይ የርስ በርስ ጦርነት እንዲመጣ እየሰሩ ናቸው ማለት ይቻላል

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የአገሪቱ ፕሬዚደንት አቶ ታዬ የራሱ አገዛዝ የሚፈጽማቸውን አገርን የማዳከምና የሰላም እጦት ሁኔታን መመርመር ነበረበት። በሌላ አነጋገር፣ ብሄራዊ ባህርይ የሌለውና ምሁራዊ መሠረቱ ደካማ አገዛዝ ስልጣንን እስከያዘ ድረስ ወደ ውስጥ ፀጥታ መደፍረሱ ይቀጥላል። በዚያው መጠንም ዓለምን እንዳለ ለመቆጣጠር የሚቅበዘበዘው በተለይም እንደ አሜሪካ የመሰለው ባህልና ታሪክ ምን እንደሆኑ የማያውቅ ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይል ያለውን ውስጣዊ ድከመት በመጠቀም በአገራችን ምድር የስላም እጦቱ እንዲባባስ ያደርጋል። ባሰማራውና አብሮ በሚሰራው እንደ ብላክ ወተር በመሰለው ጎጠኛ ኃይሎችን የሚያስታጥቀው  ኩባንያ በነገሩ እንዲገፋበት በማድረግ ህዝባችን በሰላም እጦት እንዲሰቃይ ያደርጋል። ሌላው ደግሞ በተቻለ መጠን ወደ ውጭ ለመውጣት ጥረት ያደርጋል።

ለማንኛውም የአገራችን ብሄራዊ ነፃነት ሊከበር የሚችለው፣ በአገራችን ምድር ሰላም ሊሰፍን የሚችለውና ህዛባችንም የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን የሚችለው አንተ የበላይነትን ለማስፈን የምትፈልግ ኃይል እባከህን ተወን በማለት ሳይሆን እንደ አቢይ አህመድና ህወሃት የመሳሰሉትን ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ህዝብ ኃይሎች በማስወገድ በራሱ የሚተማመን ብሄራዊ ባህርይ ያለው አገዛዝና መንግስት ሲቋቋሙና አገራችንም በሁሉም አቅጣጫ ስትገነባ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በአገርችን ምድር ዕውነተኛ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እባክህ የኃይልነት መንፈስህን ተው በማለት ሳይሆነ በጠነከረ መንፈስ እሱን አሽቀንጥሮ በመጣል በጋራና በብሄራዊ ስሜት አገርን በሁሉም አቅጣጫ መገንባት ሲቻል ብቻ ነው።  ለዚህ ደግሞ ከኒዎ-ሊበራሊዝምና ከነፃ ንግድና ከተራ የገበያ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ መላቀቅ ያስፈልጋል። አንድ አገርና ህዝብ ሁለንታዊ በሆነ መልክ ነው መታየትና መገለጽ ያለባቸው። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ህብረተሰብ የገበያ ኢኮኖሚ የሚሉት ፈሊጥ የሚካሄድበት መድረክ ብቻ ሳይሆን እንደ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ በልዩ ልዩ ተቋማት እንደሚገለጽና፣ በቆንጆ ቆንጆ ከተማዎች፣ ይሁንና ደግሞ ሰፊውን ህዝብ የማያገልሉና የማያስፈሩ አነስ አነስ ያሉና ህዝቡን ለማሰባሰብ በሚችሉ ህንፃዎች የሚገለጽ ነው። ይህን ዐይነቱ አስተሳሰብና መንፈስ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ በፍጹም አይፈልጉም። ጦርነቱና ወከባውም የሚካሄደው ወደ ውስጥ ያተኮረ ስራ እንዳሰራ ነው። መልካም ግንዛቤ!!

__

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

1 COMMENT

  1. “ደንቆሮ ደፋር ነው ይባል የለ ?” የስሜን ተወላጁ ፕሬዚደንት ችግርም ይኸው ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News