Homeነፃ አስተያየት ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች - ይድረስ ለሁላችን!!! (በፊልጶስ) 

 ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች – ይድረስ ለሁላችን!!! (በፊልጶስ) 

Advertise Here
Advertise here

በፊልጶስ 

ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የዘመኑ የሥልጣኔ ውጤቶች ናቸው። በአግባቡ የተጠቀሙባቸው ሕዝቦች ብልጽግናን፣ እድገትን፣ ዕውቀትንና አብሮነትን አግኝተውባቸዋል። እኛ ግን በተቃራኒው፣ ሕዝብን ለመከፋፈል፣ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስፋፋት፣ ከዚያም አልፎ የአገራችንን ሕልውና ለአደጋ ለማጋለጥ እየተጠቀምንባቸው እንገኛለን። 

ዓለምን ያስተሳሰረውና የመረጃ ምንጭ የሆነው ይህ ዘመናዊ መሣሪያ፣ ለአንዳንድ ጎሰኞችና ለግል ጥቅም የቆሙ ሰዎች የጥላቻ መሣሪያ፣ የቃላት ጥይትና የማኅበረሰብ መከፋፈያ ቦምብ ሆኖ እያገለገለ ነው። የአገር ችግርና የዜጎች ኃላፊነት 

በገዥዎቻችን እኩይ አስተዳደርና ኋላቀርነት፣ እንዲሁም በእኛ ቸልተኝነትና በተደገሰልን አደጋ ላይ በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስከፊ ፈተና ውስጥ ወድቋል። ሕዝባችን በጋለ የብረት ምጣድ ላይ እንደተጣደ ሰው፣ መውጫና መግቢያ አጥቶ፣ በየአቅጣጫው በሚቀሰቀስ ጦርነት መካከል በሕይወትና በሞት መካከል እየታገለ ይገኛል። አንድ ሶማሊያዊ ምሁር ከናይሮቢ እንደተናገሩት ፦ “ኢትዮጵያ ሕዝብ አላት፤ መንግሥት ግን የላትም።” ይህ አባባል የአገራችንን ሁኔታ በጥልቅ ለማሰብ የሚጋብዝ ነው። 

ታዲያ በዚህ አስቸጋሪና በጦርነት በተከበበ ወቅት፣ እንደ ዜጋ የምንችለውን ሁሉ በማሰባሰብ ወገናችንንና አገራችንን ለመታደግ መሥራት ሲገባን፣ ብዙዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጠምደው በተቀሰቀሰው የጦርነት፣ የዘረኝነትና የጥፋት እሳት ላይ ነዳጅ እያርከፈከፉ ይገኛሉ። 

የጥላቻና የመንደርተኝነት መርዛቸውን ይተፋሉ። አንድ ሃይማኖት በሌላው ላይ እንዲነሳና ተከታዮቹ እርስ በርሳቸው እንዲገዳደሉ ያለመታከት ይሰብካሉ። “ፍለጠው፣ ቁረጠው፣ ግደለው” በሚሉ አጥፊ መልእክቶች ጥላቻን ያስፋፋሉ። 

የዚህ ውጤት ምንድን ነው? ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ያልተረዳው ወገን በወገኑ ላይ ይነሳል፤ የገዥዎችም መሣሪያ ይሆናል። በተለይም ባለፉት ዓመታት ግድያንና መገደልን፣ መፈናቀልንና መሰደድን እስክንለምድ ድረስ አይተናል፣ ሰምተናል፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ደርሶብናል። የጥላቻ መልእክቶችና የሐሰት ዜናዎች አደጋ 

በአሁኑ ወቅት በቲክቶክ፣ በፌስቡክ፣ በዩቲዩብ፣ በቴሌግራምና በሌሎች መድረኮች የሚሰራጩ መልእክቶች ከፍተኛ ድርሻ የጦርነትንና የጥላቻን መንፈስ የሚያባብሱ፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሱ ናቸው። ከዚህም በላይ እጅግ ጸያፍና ሥነ ምግባርን የሚጥሱ መልእክቶች ይሰራጫሉ። 

አንዳንዶቹ በአንድ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል እንኳን መከፋፈልን በመፍጠር፣ የእግዚአብሔርን ቤት የጥላቻ መድረክ እያደረጉት ነው። ሃይማኖት ሰዎችን ለፍቅር፣ ለሰላምና ለመከባበር ሊያነሳሳ ሲገባ፣ በጥላቻ ለማነሳሳት መጠቀሙ አሳዛኝ ነው። 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ይበልጥ የሚያሳዝነው፣ በስድብና በጥላቻ የተካኑ ሰዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮችን ማፍራታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከተከታዮቻቸው ምስጋናና ውዳሴ ማግኘታቸውና የውይይት መድረኮችን መቆጣጠራቸው ነው። እኛም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዝምታን በመምረጥ፣ ተገቢውን ኃላፊነት ባለመወጣትና ሕግን በማስከበር ላይ በቂ ጥረት ባለማድረግ ለዚህ ሁኔታ አስተዋጽኦ እናደርጋለን። 

በዚህ መካከል፣ ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ህልውና ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ተዘንግተው፣ የተለያዩ ግለሰቦች ወድቀዋል፣ ታስረዋል ወይም ተገድለዋል ተብሎ የሚሰራጨው ያልተረጋገጠ ወሬ የሕዝብን ትኩረት ይወስዳል። የሐሰትና የተዛቡ ዜናዎች በፍጥነት ሲሰራጩ፣ እውነተኛ መረጃን መለየት ይከብዳል።

ብዙዎቹ የጥላቻና የመከፋፈል መልእክቶችን የሚያሰራጩ ሰዎች በምዕራቡ ዓለም እየኖሩ፣ የሰው ክብር በሚጠበቅበትና ሕግና ሥርዓት ባለበት አገር የኑሮ ዕድል እያገኙ ይገኛሉ። ሆኖም የትውልድ አገራቸውንና ወገናቸውን በጥላቻ እንዲከፋፈሉ፣ እርስ በርሳቸው እንዲጋጩና አገራቸውም ወደ የባሰ ቀውስ እንድትገባ የሚያበረታቱ ንግግሮችን ያሰራጫሉ። 

አንዳንዶች ከጥላቻ ወይም ከፖለቲካዊ ግጭት የግል ጥቅም ሊያገኙ እንደሚችሉ ይታያል። ሕዝቡን ለመከፋፈል የሚረዱ ወሬዎችን በማሰራጨት ተከታዮችን ይሰበስባሉ፤ ተራው ሕዝብም የሚሰማውን ወሬ ሳያረጋግጥ ለሌሎች ያጋራል። 

- Advertisement -

አንዱን ጎሳ ወይም ሃይማኖት እያወደሱ፣ ሌላውን እያንቋሸሹ የሚናገሩ ሰዎች በተከታዮቻቸው ዘንድ እንደ ጀግና ሲቆጠሩ ይታያል። እንዲህ ያለው አካሄድ ለአንድነት ሳይሆን ለጥላቻና ለግጭት ይሰራል። በተለይም ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጋር ያለውን ታሪካዊና ማኅበራዊ ግንኙነት በጥላቻ የሚያቃጥሉ መልእክቶች ለሁለቱም ሕዝቦች የማይጠቅሙ ናቸው። 

እንዲህ ያሉ አካሄዶች ለሰዎች የግል ጥቅም ወይም ለአንዳንድ ቡድኖች የፖለቲካ ፍላጎት ሊጠቅሙ ቢችሉም፣ የሚከፍለው ዋጋ ግን ተራው ሕዝብነው። የሚያጣው ሕይወቱን፣ቤቱን፣ ሰላሙንና የወደፊት ተስፋውን ነው። ወደህሊናችን እንመለስ 

በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ የምንንቀሳቀስ ሁላችን፣ በተለይም በጥላቻና በግል ጥቅም የታወርን ሰዎች፣ ወደ ህሊናችን እንመለስ። ዛሬም አልረፈደም። 

አገራችን በከባድ ፈተና ውስጥ ባለችበት፣ ሕዝባችንም በጦርነትና በመከራ በሚሰቃይበት ወቅት፣ ከምንጊዜውም በላይ ጨዋነት ያለው፣ በእውነት ላይ የተመሠረተና አገርንና ሕዝብን ለአደጋ የማያጋልጥ ገንቢ ውይይት ያስፈልገናል። 

ከእኛ ጋር የማይስማሙትን ሰዎች ማዋረድና መስደብ የመፍትሔ መንገድ አይደለም። ይልቁንም ቆም ብለን ማሰብ፣ ማዳመጥ፣ መረጃን ማረጋገጥና በሰላም መወያየት አለብን። አንዳንድ ጊዜ ጎጂ መልእክትን ከማሰራጨት መቆጠብ፣ ዝም ማለትና ግጭትን አለማባባስ ራሱ ትልቅ አስተዋጽኦ ነው። 

በኢትዮጵያ ውስጥ በጥላቻና በ“ከፋፍለህ ግዛ” ፖለቲካ የተነሳ የፈሰሰው ደምና የደረሰው ጉዳት እጅግ አሳዛኝ ነው። አሁንም የምንጓዝበትን መንገድ ካልመረመርን፣ በኃላፊነት ካልቆምንና ለአንድነት ካልተባበርን፣ የሚያጣው ሁላችንም ነን። ስለዚህ፣ እባካችሁ፣ ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮችን፦ 

• ከመከፋፈል ይልቅ ለአብሮነት፤ 

• ከጥላቻ ይልቅ ለፍቅር፤ 

• ከመናናቅ ይልቅ ለመከባበር፤ 

• ከማፍረስ ይልቅ ለመገንባት፤ 

• ከሐሰት ይልቅ ለእውነት፤ 

• ከግጭት ይልቅ ለሰላም፤ 

• ከግል ጥቅም ይልቅ ለአገርና ለወገን ጥቅም እንጠቀምባቸው። ሶቅራጥስና “ወዳጁ”፦ ሦስት ጠቃሚ ጥያቄዎች ለሁላችንም ትምህርት ይሆናል ብዬ ስለማምን፣ በብዙ መንገዶች የሚተረከውን የሶቅራጥስን ታሪክ ላካፍላችሁ እወዳለሁ። አንድ ቀን “ወዳጅህ ነኝ” የሚል ሰው ወደ ሶቅራጥስ ቀርቦ፣ 

“ስለ አንድ ወዳጅህ የሰማሁት ደስ የማያሰኝ ነገር አለ” አለው። ሶቅራጥስ 

ግን በጸጥታ አዳመጠው። 

ሰውየውም እንደገና፣ “ከእርሱ ይህን አልጠብቅም ነበር፤ በጣም ገርሞኛል!” አለው።

ሶቅራጥስም፣ “ስለ ወዳጄ ልትነግረኝ የፈለግከውን ነገር ከመስማቴ በፊት ሦስት ጥያቄዎችን ልጠይቅህ። መልሶችህ ካሳመኑኝ እንረዳዳለን” አለው። ሰውየውም ተስማማ። የመጀመሪያው ጥያቄ፦ እውነት ነው? 

ሶቅራጥስ፣ “ስለ ወዳጄ የሰማኸው ነገር መቶ በመቶ እውነት መሆኑን አረጋግጠሃል?” ብሎ ጠየቀው። ሰውየውም፣ “መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን አልችልም” አለው። ሶቅራጥስም፣ “እንግዲያውስ 

የምትነግረኝ እውነትነቱ ያልተረጋገጠ ነገር ነው” አለው። ሁለተኛው ጥያቄ፦ መልካም ነው? 

ከዚያም፣ “ልትነግረኝ የፈለግከው ነገር ስለ ወዳጄ መልካም የሚናገር ነው?” ብሎ ጠየቀው። 

ሰውየውም፣ “አይደለም፤ መልካም ነገር አይደለም” ብሎ መለሰ። ሶቅራጥስም፣ “እንግዲያውስ እውነትነቱ ያልተረጋገጠና መልካም ያልሆነ ነገር ልትነግረኝ ነው” አለው። ሦስተኛው ጥያቄ፦ ጠቃሚ ነው? በመጨረሻም፣ “ይህን ነገር ማወቄ ለእኔ ወይም ለሌላ ሰው የሚጠቅም ነገር አለው?” ብሎ ጠየቀው። ሰውየውም፣ “የለውም” ብሎ መለሰ። ሶቅራጥስም በመጨረሻ፣ 

“እንግዲያውስ እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፣ መልካም ያልሆነና ጥቅም የሌለውን ነገር ለምን ልስማ?” አለው ይባላል። 

ይህ ታሪክ በተለያዩ መልኩ የሚተረክ ሲሆን፣ ዋናው መልእክቱ ግን ግልጽ ነው። ከመስማታችን፣ ከመናገራችንና ከማጋራታችን በፊት እውነትነቱን፣ መልካምነቱንና ጠቃሚነቱን መመርመር አለብን። 

እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፣ መልካም ያልሆነና ለአገራችንና ለወገናችን ሰላምና አንድነት የማይጠቅም መልእክት ላይ ጊዜያችንን ማጥፋት፣ ከዚያም አልፎ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት አይገባንም። ከሰው ፍርድ ልናመልጥ ብንችልም፣ ከራሳችን ህሊና ፍርድ ግን ልናመልጥ አንችልም። ለሃይማኖተኞችም የእግዚአብሔር ፍርድ የማይዘነጋ ነው። 

እስካሁን ድረስ የነበረው የማኅበራዊ መገናኛ አጠቃቀማችን በብዙ አጋጣሚዎች የሕዝባችንን መከራ ከማሳነስ ይልቅ እንዲባባስ አድርጓል። የኢትዮጵያዊነትን መንፈስና የጋራ ትግላችንን አዳክሟል። ከኤርትራ ወገኖቻችን ጋር ያለንን ግንኙነትም በጥላቻ እያበላሸን እንገኛለን። የኢትዮጵያን ትንሣኤና አብሮነት ለማምጣት መተባበር ሲገባን፣ በጥላቻ መንገድ መጓዛችን ከዓላማችን እያራቀን ነው። 

ስለዚህ ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮችን ለአገርና ለወገን መድኅን፣ ለሰላምና ለፍቅር፣ ለእውቀትና ለልማት እንጠቀምባቸው። እንደ ዜጋ ያለንን ኃላፊነት እንወጣ። የምንለውን እናስብ፣ የምናጋራውን እናረጋግጥ፣ የማንስማማበትንም ሰው በክብር እንያዝ። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በአንድነት፣ በፍቅርና በኃላፊነት እንታደግ! 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!! 

ፊልጶስ 

E-mail.: Philiposmw@hotamil.com


__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News