Homeነፃ አስተያየትየአማራ ብሔረተኝነትና ኢትዮጵያዊነት  - ክፍል አራት 

የአማራ ብሔረተኝነትና ኢትዮጵያዊነት  – ክፍል አራት 

Advertise Here
Advertise here
የአማራ ብሔረተኝነትና ኢትዮጵያዊነት  - ክፍል አራት 

በአበበ ኃብተሥላሴ  

…ካለፈው የቀጠለ ክፍል አራት 

ጥቅምት 10 2019  

ከላይ ኢትዮጵያዊ የሆነውን ወገን ጋዜጠኛ አንሙት ‘’ዞር በል’’ መባል ነው ያለበት ብሎ እየመለሰ እያለ ጠያቂው ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን እንዲህ ሲል ያቋርጠዋል። 

“አሁንም ቢሆን ስጋቴን አነሳለሁ ይሄ ትግል መስመር ስቶ መረን ወጥቶ ለኢትዮጵያዊነት አደጋ እንዳይሆን ማዕቀፉ አለ ወይ? ይህ አማራው የጀመረው ብሔረተኝነት ወደምንፈራው ወደማትቆጣጠሩት ጽንፍ ወደረገጠ ለኢትዮጵያ አደጋ ሆኖ እንዳይሻገር ከወዲሁ መመካከሩና ቀስ እያሉ ነገሮችን እያዩ መሄድ ጥሩ ነው። አይታወቅም በደል በደልን ነው የሚያመጣው ደም ደምን ነው የሚወልደው የአማራ ሕዝብ በተገደለ ቁጥር በድሮን በተጨፈጨፈ ቁጥር የሚታየው ያ ትውልድ በቀል ነው ነገ የገደለኝ ኢትዮጵያዊነት በሚል የተደራጀ ኃይል ነው እያለ ነገ ኢትዮጵያዊነትን እንደጠላት እንዳይመለከት ጥንቃቄ ያስፈልጋል። …ኢትዮጵያዊነት መዳኛችን ነው ቃሉን ስለምንፈገው አይደለም ኢትዮጵያዊነት መዳኛችንም ነው። ማንነታችን ነው። …. እኔ ደቡብ ነው የተወለድኩት ኢትዮጵያዊነት ተመዞ  

ከወጣ ደቡብ የሚባል የለም ያ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ተበታትኖ ነው የሚቀረው። ኢትዮጵያዊነት ህልውናው ስለሆነ ነው ደቡብ ውስጥ ያለው የማህበረሰብ ክፍል በአንድነት የኖረውና በዚህ እሳቤ ከሄድን ትግሉ ጤናማ በሆነ መልኩ ከኢትዮጵያዊነት መዳረሻው ልንነቅለው አንችልም። አማራን አድኖ ሌላውንም የኢትዮጵያ ክፍል ለማዳን የሚያስችል አቅም (የአማራ ትግል) እየፈጠረ ነው ይህንን ድል እንዴት ነው የምናየው?”1 

አንሙት “ጥሩ ሃሳብ ነው” በማለት መመለሱን ይቀጥላል። 

“አንድ ነገር ይሄንን የሚወስነው ምን መሰለህ መሳይ እውነት ለመናገር አሁን አማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ከቀጠለ ምናልባት  ሌላም ሌላም አካባቢ ያየናቸው የነፃነት ንቅናቄዎች ሊመጡ ይችላሉ በአማራ ፖለቲካ ውስጥ። አሁን ያለው ጥቃት ከቀጠለ፣ ስለአማራ  ነጻ መንግሥት ስለአማራ ነጻ አገረ መንግሥት የሚያስቡ ንቅናቄዎች አይመጡም ብዬ ማረጋገጫ መስጠት አልችልም። እኔ በደሉ ከቀጠለ  ያ የምትለው ስጋት [የኢትዮጵያ መፍረስ] እውን ሊሆን ይችላል። አሁን ስለአማራ ነፃ መንግሥት ተመልከት አሁን ሲኖዶስ ተብሎ 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የትግራይ ሲኖዶስ የኦሮሞ ሲኖዶስ የምናምን ሲኖዶስ ተብሎ ቤተክርስቲያኗ በዚህ ደረጃ ስትታመስ የአማራ ጳጳስ የአማራ ፓትርያርክ የአማራ ካህን ስሌለ እኮ አይደለም እንዲህ ዓይነት ከአማራው በስተቀር ያሉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በጣም ጡዘታቸው በቀጠለበት እየተጠቃ በቀጠለ ልክ ቅድም ያልከው ስጋት ኢትዮጵያ ለምን ፍርስርሷ አይወጣም የሚል እሳቤ ፎር ዛት ማተር ቅድም እንድላኩት  የነፃነት ንቅናቄዎች ሊጀመሩ ይችላሉ። ስጋት የሚሆነ የበደል መቀጠል ነው። አሁን ባለንበት ደረጃ የአማራ ብሔረተኝነት ከኢትዮጵያ ጋር ከኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ፀብ የለውም ተገንጣይም አይደለም። ጠላት ያልነውም አንድ ቡድን ነው የኢትዮጵያ ሕዝብም አይደለም”።2 

እዚህ ጋ አንሙት ከላይ “የኢትዮጵያ አንድነት ከአማራ ህልውና በታች ነው” ብሎም የአማራ ብሔረተኛነት ለኢትዮጵያ አንድነት ስጋት ነው ብሎ የሚያስብ የአንድነት ፖለቲካ አራማጅን “ዞር በል” ነው መባል ያለበት ኢትዮጵያዊነትን የምትል ሁላ በራስህ ሜዳ ተጫወት እንጂ በአማራ ብሔረተኛ ሜዳ መጫወት አትችልም ያላቸው አባባሎች ከላይ “ኢትዮጵያ ለምን ፍርስርሷ አይወጣም የሚል እሳቤ” ሊጀመር ይችላል ካለው ጋር የሚመጋገቡ ናቸው። በመሆኑም አንሙት አማራው ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ከቀጠለ አማራው የራሱን አገር መንግሥት ለመመስረት አያስብም ብዬ ማረጋገጫ መስጠት አልችልምና የሚታስበው የኢትዮጵያ መፍርስ ስጋት እውን ሊሆን ይችላል በማለት የራሱን ሃሳብ ገልጿል። ሆኖም ግን አንሙት አማራው ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና በደል መቀጠልን እንደማስፈራሪያ ተጠቀመ እንጂ ጥቃቱንና በደሉን ማን እንደሚፈጽምና ለዚህም መፍትሔው ምን እንደሆነ ያለው ነገር የለም። እዚህ ላይ ላለፉት ተከታታይ አመታት የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ የአገዛዙን ጥቃት መመከት የቻለ ትግል እየተካሄደ ያለው እኮ በተፈጥሮው አድሏዊ የሆነ የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት በግድ መተከሉን ተከትሎ እየተፈጸመ ባለ ወንጀል ምክንያት ነው፡፡ 

ሲጀመር አማራው ላይ እያደረሰ ያለው ሰቆቃ ከምንም ሳይሆን ለታሪካዊ ጠላት አገራት ያጎበደዱ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ሕዝብ የሆኑ የባንዳ ልጆችና አገር ገንጣዮች በቂም በቀል ተነሳስተው፣ ፍትሃዊነትን ተጠይፈውና በተፈጥሮው አድሏዊ የሆነ የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓትን በግድ መተግበራቸውን ተከትሎ ነው። ስለዚህ እንደ አንሙት ያለ የአማራ ብሔረተኛ ጥቃትና በደል ከቀጠለ ሲል አብሮ ማንሳት የሚገባው ጉዳይ ጥፋትና በደልን ማን እንደሚፈጽምና ለምን እንደሚፈጸም ብሎም ይህንን እንዳይደገም የሚያስችል አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሔውም ምን እንደሆነ ብሎም የትግሉ ረዕይና ግቡንም ግልጽ ማድረግ ይገባው ነበር። ሆኖም ግን ይህ ወገን ከዜግነት ይልቅ ማንነትን ያስበለጠ በመሆኑና ይህንንም ተከትሎ በተያዘ የፖለቲካ አቋም በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋትና በደል ሲፈጽሙ ከኖሩና ወደፊትም ለመፈጸም ከማይመለሱ ኃይሎች ጋር እየተባበረ ጥቃትና በደል ካልቆመ ብሎ ማስፈራራት ደግሞ አይችልም። ይህ አንሙት የሚፈራው አማራው ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት መቀጠሉ እኮ በአጠቃላይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ፈልጎት በተለይ ደግሞ የሌላ ማንነት ያለው ኢትዮጵያዊ ወገን ያንን በአማራ ላይ እየደረሰ ያለውን እፍዳ እንደ ትክክል ቆጥሮና ደግፎ ቢሆን ከላይ አንሙት እንዳለው የኢትዮጵያ አንድነት ከአማራው ህልውና አይበልጥም ብሎ ነፃ የአማራ አገር መመሰረት ቢታሰብ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል። 

ነገር ግን አማራው በኢትዮጵያዊነቱ ጸንቶ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ይህ አማራው ላይ የህልውና አደጋ በመጋረጥ እፍዳውን እያሰየው ያለውን ሥርዓት ደግፎ ማለትም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአንድነት ይልቅ በተለያየ ማንነት መቆሙን በግልጽ መርጦ ቢሆን አዎ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በማለቴ ይኸው ውድ ዋጋ እየከፈልኩና ህልውናዬ እጅግ ለከፋ አደጋ ተዳርጓል ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ምን አባቱ የሚለው አባባል ተቀባይነት ማግኘት ይችላል። በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት አገራት በባንዳነት ያጎበደዱ ጥቂት ጽንፈኞች የመንግሥት አስተዳደራዊ አቅምንና ኃይልን በመጠቀም በነዙት ፕሮፓጋንዳና በሕጋዊም ከሕግ በሰተጀርባም እያበረታቱ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀልና የሚሰሯቸውን ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ልማት ተግባራትን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲቀጥሉ የሚፈልግ ቢሆን አንሙት ከላይ እንዳለው “ኢትዮጵያ ለምን ፍርስርሷ አይወጣም” ብሎ አማራው የራሱን ሉዓላዊ መንግሥት ለመመስረት ቢመርጥ ይህም አሳማኝ ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል። 

- Advertisement -

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ1981 አንስቶ እየደረሰበት ካለው ሰቆቃና እየኖረ ካለው ሕይወት አረዳድ ብሎም ሕዝብ እንደ ሕዝብ ፍትህን እንጂ አድሏዊነትን የሚቀበል ባለመሆኑ ይህንን በአማራው ላይ የህልውና አደጋ የጋረጠ አድሏዊ ሥርዓትን እስከ መጨረሻው የሚፋለመው እንጂ በምንም አመንክዮ እንዲቀጥል ሊፈልግ አይችልም። ሆኖም ግን እንደ አንሙት ዓይነቶች ኢትዮጵያዊነትና የአንድነት ፖለቲካ እሳቤ የከሸፈ ነው ብለውና የአማራ ብሔረተኝነት አዋጭ መንገድ አድርገው በመያዝ አገዛዙን ጠላቴ ብሎ አብሮ እየታገለና መስዋዕት እየከፈለ ያለ አማራም ኢትዮጵያዊም ነኝ የሚለውን ወገን እንደጠላት ፈርጆ እያሳደደ መግደል መፍትሔ መሆን አልቻለም አይችልምም። ይባስ ብሎ አማራውን የዘመን ጠላት ካሉ፣ ኢትዮጵያዊነትንና የሕዝብ አንድነትን ከማይፈልጉና ይህንንም ተከትሎ አገር ለማፍረስ ከሚዝቱት ጋር ተባብሮ አማራው ላይ እየደረሰ ላለ በደል ኢትዮጵያዊነትን እንደ ምክንያት ማቅረብ በምንም ዓይነት አመንክዮ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም። አማራው ላይ እየደረሰ ያለው በደል ኢ-ፍትሃዊ በመሆኑና ነፍጥ አንስቶ እንዲታገልም ያስገደደው ያለው አድሏዊ ሥርዓት መሆኑን በማመን ነበር እኮ ገና ክጅምሩ ትግሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ትብብርና ድጋፍ እንዲለገሰው፣ ትግሉ በተቀናጀና አንድ ወጥ አመራር እንዲመራ፣ የትግሉን ግብ ማለትም የአማራውን ህልውና በአስተማማኝና በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚረዳ ሕዝባዊ ሥርዓት መመስረት እንደሚገባ ለማስረዳት የተለያየ ጥረት ሲደረግ የነበረው። 

ለዚህ ነበር የሕግ የበላይነት በሰፈነበት ሥርዓት ውስጥ ብዙ ማንነት ያለው ሕዝብ በሚኖርባቸው ሌሎች አገራት እንደሚታወቀው ሕዝብ በመከባበርና በመግባባት እንዴት ተስማምቶና ተከባብሮ መኖር እንደቻለ መረዳት በመቻሉ ነበር በጊዜው የተሰጠው ምክረ ሃሳብ ሊሰጥ የቻለው። ሆኖም ግን የሕግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት፣ ባለሥልጣናት ከሕግ በላይ በሆኑበትና ሕዝባዊ ሥርዓት ባልሰፈነበት የኢትዮጵያ ሁኔታ በተለይ ላለፉት ሰላሳ አምስት አመታት በተለይ አማራ ላይ ሲፈጸም የኖረ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል ወደፊት መቀጠል እንደሌለበት በመታመኑ ነበር የትግሉ ግብ የአማራውን እንደ ሰው የመኖር መብቱን የገፈፈ አድሏዊ ሥርዓት በፍትሃዊና በሕገ-ሕዝብ ላይ በተመሰረተ ሥርዓት እንዲተካ ሲመከር የነበረው። በተጨማሪም አማራው ላይ እየደርሰ ያለው ጭፍጨፋ፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል እንዳይቀጥል ብቻ ሳይሆን ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሔ መስጠት የሚቻለው ይህ ሁሉንም የጎዳና የዜሮ ድምር ውጤት ያስከተለ ሥርዓትንና አገልጋዮቹን ሁሉንም አሸናፊ ማድረግ በሚችል ሕዝባዊ ሥርዓትና የመንግሥት አስተዳደርም በአገር ወዳድ አመራር መተካት ሲቻል መሆኑ ከብዙ አገራት ተሞክሮ መረዳት በመቻሉ ነበር በጊዜው የተሰጠው ምክረ ሃሳብ ሊሰጥ የቻለው። 

ለዚህም ነው የአማራ ሕዝብን ህልውና እናስከብራለን ብሎ ነፍጥ አንስቶ ትግል የጀመረው ወገን ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር እንዲያብርና ሁሉም ያለውን አድሏዊ ሥርዓት በፍትሃዊና በሕገ-ሕዝብ ላይ በተመሰረተ ሥርዓት ለመተካት ራዕይ ሰንቆ መታገል እንደሚገባው ሲመከር የነበረው። ምክንያቱም ከ1983 ወዲህ በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋትና በደል ሥርዓታዊና መዋቅራዊ በመሆኑ መፍትሔው ያለውን ሥርዓት ከነጋሻ ጃግሬዎቹ ማስወግድ ብቻ በመሆኑ ነው። ለዚህም ነበር የፋኖ አንድነትን ማጠናከር አመርቂ ውጤት ማስከተል እንደሚችል ማለትም የተለያየ ማንነት ያለውን ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ትብብር ማግኘት፣ የሚከፈል መስዋዕትን መቀነስ፣ ለትግሉ የሚውል ሃብትና ንብረት በቀላሉ መሰብሰብ፣ ትግሉ የሚወስደውን ጊዜ ማሳጠርና በእርግጠኝነት ትግሉን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ እንደሚቻል ሲመከር የነበረው። ይህንን እምነት ተከትሎ ነበር ስለመደራጀት፣ ስለአንድ ወጥ አመራር አስፈላጊነት፣ ሁሉንም አሸናፊ ስለሚያደርግ በሕገ-ሕዝብ ላይ ስለሚመሰረት ሥርዓት ምስረታ እንደራዕይ እንዲወሰድ ምክረ ሃሳብ ሲለገስ የነበረው። ሆኖም ግን ለዚህ ሁሉ ጥረት ይሰጥ የነበረው መልስ እጅግ በጣም የወረደ ማለትም ትሕነግና ኦነግ እኮ ለመደራጀት አርባና አምሳ አመታት ፈጅቶባቸዋል ሲብስም ፋኖዎች እኮ ለመሰብሰብና ለመደራጀት ጊዜ የላቸውም ጊዜያቸውን በውጊያ ላይ ነው የሚያሳልፉት ብሎም ድፍን የሆነና ግልጽነት የጎደለው ትግሉ ቅድሚያ የሰጠው የህልውና ጥያቄን ለመመለስ ስለሆነ ሌላ ነገር ውስጥ መግባት እንደማያስፈልግ ማስፈራራት የታከለበት ነበር። ይህንን መሰል ማስፈራራት ደግሞ የእስራኤል ባለሥልጣናት በፓለስታይን ሕዝብ ላይ እየፈጸሙ ላሉት ወንጀል መጠየቅ እንደሚገባ የሚነሳ የፍትህ ጥያቄን ፀረ-ሴመቲክ ነው በማለት ለማሸማቀቂያነት እንደሚጠቀሙት መሆኑ ነው። 

ሆኖም ግን ይህ የህልውና ጥያቄን መመለስ የሚለው አባባል እንዴት ሊሳካ እንደሚችልና ለአማራ ሕዝብ ህልውና መረጋገጥ እንዴት አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ምንም ማለት ባለመቻሉ ይህን አባባል እንዲጠየቅ አድርጎታል። ስለዚህ ይህ ነፍጥ ላነገበ ትግል ምክንያት የሆነ በህልውና ላይ የተጋረጠ አደጋን እንዴት መመከት እንደሚቻል የሚያሳምን ማለትም የትግሉ ሂደትና ግብ ምን እንደሚሆን ግልጽ ማድረግ ባለመፈለጉ የፋኖ ትግል አንደነት እንዳይሰምር፣ እርስ በርስ መገዳደል ውስጥ እንዲዘፈቅ፣ ግለሰቦች ሃብት እንዲያካብቱና አንዳንዶች ደግሞ ከትግል እንዲሸሹ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ጊዜ ደጉ ማየት ተችሏል። በተጨማሪም ትግሉ የበለጠ ጊዜ፣ መስዋዕትነትና መዋለ ንዋይ እንዲጠይቅና የአገዛዙንም እድሜ ማራዘም ማስቻል ብቻ ሳይሆን የአማራ ብሄረተኛ ነኝ ባዩ ወገን ጭራሽ አማራውን የዘመን ጠላት አድርገው ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ ከኖሩና ይህንንም ተከትሎ በተቀነባበረ፣ በተቀናጀና፣ የመንግሥት አስተዳደር ኃይልን በመጠቅም በሕጋዊም ከሕግ ጭምር እንደ ሰው የመኖር መብቱን ገፈው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጽሙበት ከነበሩና የኢትዮጵያ አንድነትን ከማይሹ ከትሕነግና ከኦነግ ጋር አብሮ የሚሰራ ወገን መፍጠር አስችሏል። ለመሆኑ ይህ ህልውናን ማስጠበቅ የሚለው አባባል መፍትሔ ሊሰጥ የሚችለው ከዚህ በፊት ነበር የሚባል ጥፋትና በደል እንዳይደገም የሚያስችል ፍትሃዊ ሥርዓት በመትከል ወይስ አማራውን የዘመን ጠላት ብሎ ፈርጆ እንዲጨፈጨፍ ያስቻለ አድሏና ሥርዓትን ከሕዝብ ይሁንታ ውጪ በግድ ከተከሉት ጋርና አገርን ለመበታትን ከሚዝቱት ጋር በማበር? 

ጠያቂው ጋዜጠኛ በፋኖ ትግል ውስጥ ስለሚታዩ ከብሔረተኝነትም የወረደ አውራጃዊነት ስለመኖሩና እርስ በርስ እስከመጋደል ያደረሳቸው ችግር ምን እንደሆነ እንዲህ ብሎ ጥያቄውን ይቀጥላል።

“…ስለፋኖ ትግል ልምጣ ቀደም ሲል መልካም ነገሮችን አንስተሃል ግን የፋኖ ትግል ደግሞ ብዙ ክፍተቶች ያሉበት እንደሆነ የሚካድ አይደለም። …የሚገባውን ያህል አቅምና ጥንካሬ ከፈጠረ በኋላ እንኳን በሚጠበቀው ልክ ትግሉን እየመራ አይደለም። አሁንም አውራጃዊ ስሜት አሁንም የጎጥ ስሜቶች ትግሉን እያንቀራፈፉት ይገኛሉ። አሁን እንደውም ለሁለት የተከፈለ በሚመስል መልኩ ወደ እርስ በርስ ግጭት ውስጥም የገቡ ኃይሎች እንዳሉ ያው የምንሰማው ነገር አለ የግድ የተደበቀም ስላልሆነ ብናነሳው ችግር አይኖረውም። እስቲ ግን ምንድንነው አሁን የአማራ ሕዝብ ትግል የፋኖ ትግል ችግሮች ብለህ የምታስባቸው ምንድን ናቸው”?3 

አንሙትም የሚከተለውን ይመልሳል። 

“ቅድም እንዳልነው ይሄ ትግል ከአንድ የሽምቅ ትግል የስኬት መለኪያዎች አኩዋያ በመጀመሪያ ደረጃ ሊታዩ የሚችሉ ውጤቶች አምጥቷል። …የዕድገት ደረጃው የሚወስናቸውና እንደ ትግል ኦፍኮርስ አንዳንድ ጊዜ መቆም ሌላ ጊዜ ወደኋላ መመለስ ሌላ ጊዜ ወደ ዝቅጠትና ቅልበሳ ሁሉ የገባ የሚመስልበት አደጋዎች ያጋጥማሉ። ከዛ ደግሞ ተስፈንጥሮ ወጥቶ ወደ ፊት ወደ ድል የሚሄድበት እንዲህ ዓይነት ውጣ ውረዶች ይኖራሉ ሂደቱ ዝም ብሎ በቀጣይነት ወደላይ ብቻ የሚሄድ ብቻ አይደለም። ከዚህ አኳዋያ ፈተናዎች አሉበት። የአመራር ልምምዱም ውስንነት ስላለው ብዙ ጉዳዮች አሁን በብዙ ውጥረቶች ውስጥ ያለ ነው። አንደኛው አንተም እንደጠከስከው የዚህ  

ትግል አቆርቋዥ ነው የምንለው እኛ የዚህ አካባቢያዊ አስተሳሰብና ይሄን የመሰለው አካሄድ በአንድ በኩል ትግል አቆርቋዥ ስለሆነ አንደኛው የትግሉ ፈተና ነው። …የዚህ ችግር ምንጩ ትግሉን እየመሩ ያሉ አካላት የትግሉ መሪዎች ከሞላ ጎደል ሳይንሳዊ አድርጎ በከፍታ ትልቁን ስዕል በማየት ለመምራት የሚያስችል እኔ ከጓደኞቼ ጋር እከራከራለሁ እኔ የዕውቀት ውስንነት ይኖራል ከዕውቀት ችግር ነው  እላለሁ ሌሎቹ የቅንነት ችግር ነው ይላሉ። …በአግባቡ አጥርቶ ለመከራከርና ሳይንሳዊ ለማድረግ ውስንነት አለ ብዬ ነው የምመለከተው። በሌላ ረገድ ቅድም ስንል የነበረው የሁለቱ ጎራ አሰለላፍ የዚህ የሁለቱ ብሔረተኝነት (የአርባንና የአርሶ አደሩ) ግጭት ታች ፋኖዎቹ ጋር  እየደረሰ ነው ያለው። ስለዚህ የዚህ ፀረ-ብሄረተኛውና ብሔረተኛው ኃይል ግጭት ከሞላ ጎደል በፋኖዎች ዘንድም እየታየ በመሆኑ እሱም  ትልቅ ፈተና ነው”።4 

እንደሚታወቀው የአማራ ሕዝብ ትግል በየቦታው ያለ ፋኖ ተሰባስቦ በደመ-ነፍስ ህልውናውን ለማስከበር ብሎ የጀመረው በመሆኑ አንሙት ያላቸው የዕውቀት ማነስና ቅንነትም ቢኖር ሊያስገርም አይገባም። ፋኖ የጀመረውን ትግል ተገቢነት አምነው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከማሰብ ትግሉ የጎደለውን በመጠቆምና ሊያርም የሚገባውን ችግሮች በማንሳት ሃሳብ ቢቀርብም ሰሚ ማጣት ብቻ ሳይሆን ጭራሽ ሃሳብ አቅራቢውን እንደ ፀረ-አማራ መፈረጅ የሚጠቁመው እውነትም የእውቀት ማነስም ሆነ ቅንነት እጅግ የጎደሉ መሆናቸውን ነው። በፋኖ ትግል ውስጥ እንደተባለው አካባቢያዊ አስተሳሰብ ትግሉን ከማቆርቆዝ በተጨማሪ ወደ እርስ በርስ መገዳደል ደረጃ ያደረሰ ትልቅ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው አንኳር የሆነ ልዩነት የተፈጠረው አንዱ ወገን ኢትዮጵያዊነትን የሚጠየፍና ምርጫው የአማራ ብሔረተኝነት የሆነ ሌላኛው ደግሞ አማራነቱንም ኢትዮጵያዊነቱም አጣምሮ በመያዝ ለአማራውም ለተቀረው የኢትያጵያ ሕዝብም መፍትሔ በመስጠት አገርን ማስቀጠል ግቡ ያደረገ መካከል በመሆኑ ነው። ይህንን አንሙትም ልዩነቱን የሁለት ጎራ አሰላለፍ ብሎ የገለጸው በአማራ ብሔረተኛው (አርሶ አደሩ አማራ) እና በኢትዮጵያኒስቱ (አርባን አማራ) መካከል ያለው ግጭት ትልቅ ፈተና እንደሆነ መመስከሩን ልብ ይሏል። እዚህ ላይ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አንሙት ከዚህ በፊት ካላቸው አባባሎች መካከል አንዱን ለማስታወስ ያክል የአማራ ብሔረተኝነትን የሚያቀነቅነው ወገን እንደ ጠላት የሚቆጥረው አንድ ቡድን አንዳለ ማንሳቱንና ይህ ቡድንም ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅነውን ወገን እንደሆነ ልብ ማለት ይገባል። ይህንንም ተከትሎ ያለውን ችግር ተገንዝቦ የእርምት እርምጃ መውሰድ አለመቻል ወይም አለመፈለግ በመኖሩ ነው ፋኖ አንድ ሆኖ የትግል ሂደቱንና ግቡን የሚያሳይ ሰነድ ማዘጋጀት፣ የሚመጥን አደረጃጀት መፍጠር፣ ተቀባይነትና ብቃት ያለው አመራር መሰየም ብሎም በሃሳብ ላይ መሰረት ያደረገ ንግግር፣ ክርከርና አንዱ ሌላውን ለማሳመን መትጋትና መጣር ሳይሆን ሥልጣን ያስከረውን መሾም ሲብስም እርስ በርስ እስከመገዳደል መድረስ የተቻለው። 

እንግዲህ የአንድነቱ ጉዳይ እንዳይሳካ የዕውቀትና የቅንነት ችግር እንዳለ ቢጠቀስም የግለሰብ የሥልጣን ጥም፣ አውራጃዊ ስሜት፣ ኃብት የማካበት ስግብግብነትና ሌሎች ችግሮችም የራሳቸው ሚና ቢኖራቸውም ነገሮች ባሉበት እንዲገኙ በመሰረታዊነት ችግር ፈጣሪ የሆነው ጉዳይ አንድ የፋኖ ወገን ከኢትዮጵያዊነት በተቃራኒ በመቆም ልክ እንደሌሎቹ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች እራሱን የአማራ ብሔረተኝነት አቀንቃኝ አድርጎ መውሰዱ ነው። ይህ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ጠላት የቆጠረ የአማራ ብሔረተኛ የፋኖ ኃይል አንድ ጠንካራና ወጥ አካል መፍጠር ላይ ደንቃራ መሆኑ ሳይንስ አማራነቱንም ኢትዮጵያዊነቱንም አጣምሮ የያዘ ወንድም ፋኖን እያሳደደ እስከመግደል የደረሰና በዚም ሳያበቃ ከትሕነግ፣ ከኦነግና ከሌሎችም ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ልማት የሆኑና የአንድነት ጠላት ድርጅቶች ጋር በማበር ሉዓላዊ አንድነት ማስጠበቅ ላይ ትልቅ ችግር ፈጣሪ እንደሆነ ያለምንም መሽኮርመም በግልጽ መናገር ይገባል። ይህ ልዩነት በአማራ ብሔረተኛው ወገን እንደ ቀላል ያልተወሰደ እንደሆነና መግባባት ሊደረሰበት እንደማይችል ተደርጎ በመወሰዱ ምክንያት ልዩነቱ ተራ ልዩነት የሚባል ሳይሆን አንዳንዶች እንደውም ምን ያህል ከበድ ያለ እንደሆነ ለመግለጽ የአይዲዎሎጂ ልዩነት አድረገው እንዲወስዱት ግድ ብሏል። እንግዲህ የአማራ ሕዝብን ለሁለት ጎራ ከፍሎ ማለትም አማራ አማራ የሚለውን የአርሶ አደሩ አማራ ብሄረተኛና ኢትዮጵያዊና አማራ ነኝ የሚለውን ደግሞ የከተሜ አማራ በማለት ሁለት ጎራ በመክፈል ያለውን ልዩነት መፍታት ሳይቻልና እንደጠላት እየተያዩ ለጥቅሙ ቅድሚያ እሰጣለሁ የሚሉትን የአማራ ሕዝብ ህልውና ማረጋገጥ አይቻልም። በተጨማሪም ይህንን አቋም ተከትሎ ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ፣ ሕዝብና ፀረ-ልማት ከሆኑ ኃይሎች ጋር መተባበር የሚያስከትለው ውጤት ሕዝብን አንድ አድርጎ እጅግ ውስብስብ፣ ውድና እልህ አስጨራሽ ልማትን እውን ማድረግና የአማራውንም የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብንም ከድህነትና ኋላ ቀርነት በዘላቂነትና በአስተማማኝነት ማላቀቅ ሳይሆን ጭራሽ በሕዝብ አንድነትና በአገር ሉዓላዊነት ላይ ትልቅ ደንቃራ መሆንን ነው። 

ይህን የመሰለ አቋም ደግሞ ውድ የሕይወት ዋጋ እየተከፈለለት ያለው ትግል አድሏዊ፣ ጠላት ፈላጊ፣ ፀረ-ሕዝብና አንድነት ብሎም ፀረ-ልማት የሆነውን ሥርዓት የሕግ የበላይነት በሰፈነበት ማለትም ሁሉንም ዜጋ በእኩል ማስተናገድ በሚችል ፍትሃዊ ሥርዓት ለመተካት የሚደረግ ጥረት ላይ ውሃ የሚከለሰ ይሆናል። ይህ የሚሆነው ደሞ የአማራ ሕዝብ ትግልን እንመራለን የሚለው አካል እራሱን ከትሕነግና ከኦነግ ጋር ለክቶ፣ የአማራ አርሶ አደር ብሔረተኛ ነኝ ብሎ፣ የኢትዮጵያዊነት ካባውን አውልቆ ጥሎ፣ የጎሳ ፖለቲካ ካባ ለብሶ፣ የኢትዮጵያ አንድነት ከአማራ ህልውና በታች ነው ብሎ፣ ኢትዮጵያዊነትም የከሸፈ ነው ብሎ ምን ለምን አብረህ አዝግም እንደተባለው ከከፍታ ወርዶ በማንነት ጎጥ ወስጥ መወሸቅን የመረጠ በመሆኑ ነው። በዚህ መንገድ መቀጠል ማለት ደግሞ ተወደደም ተጠላም፣ ታወቀም አልታወቀም፣ ተፈለገም አልተፈለገም ኢትዮጵያ እንድ አገር እንድትቀጥል የተለያየ ማንነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተመው፣ መስዋዕትም ከፍለው በደምና አጥኝታቸው አስከብረው ያቆዩዋትን ኢትዮጵያ ለማፍረስ ለታሪካዊ ጠላት አገራት ካደሩ ባንዳዎችንና አገር ገንጣዮች ጋር እጅና ጓንት መሆን ነው። 

አሁን የአማራ ሕዝብን ትግል እንመራለን የሚለውና እራሱን የአማራ አርሶ አደር ብሔረተኛ አድርጎ የወሰደው ወገን የጎሳ ፖለቲካን በቅጡ ተረድቶና ጥፋቱን አመዛዝኖ ከጎሳ ፖለቲካ እሳቤ መላቀቅ ሲገባው በተቃራኒው ኢትዮጵያዊነትን የሚጠየፍ፣ የብአዴንና በጎሳ ፖለቲካ ዘመን ኃብት ያፈራ ሆዳም አማራ ተዕዕኖ ሥር የወደቀ በመሆኑ እሩቅ አላሚ፣ ብልህና ቅን መሆን ያልቻለ ኃይል ነው። ይህ በሥልጣን ጥም የሰከረና አገራዊ ራዕይ የሌለው ስብስብ ኢትዮጵያዊ ተብሎ ከተፈረጀ ወገን የሚመጣ ምንም ምክር አልሰማ ብሎ ኢትዮጵያዊነትን በመጠየፉና የአማራ ብሔረተኝነትን በመምረጡ ምክንያት ለአማራ ህልውና መረጋገጥ አብሮት እየታገለ ያለ ወንድሙን እያሳደደ ለማጥፋት ለመትጋት የመረጠ በመሆኑ ትግሉን በአጭር ጊዜ መቋጨት ሳይሆን ጭራሽ የአገዛዙን ዕድሜ እያራዘመና የአማራ ሕዝብን ጥቃት እያስቀጠለ ይገኛል። ታዲያ ወዴት ወዴት ነው ነገሩ? የፋኖ አንድነትና በአንድ አመራር ስር መታገል እንዳይቻልስ ማን ምን በማድረጉ ነው ትግሉ ከሚፈለገው በላይ ኪሳራ እያስከተለና የአማራውንም ሰቆቃ እያስቀጠለ ያለው?  የአገዛዙን ዕድሜ ማራዘም የተቻለው? የአማራ ውድ ልጆች መሰዋዕትነትን ማስቆም ሳይሆን ማስቀጠል የተቻለው? እዚህ ላይ በግልጽ መወያየት ያስፈልጋልና በእውነት ማን ምን እያደረገ በመሆኑ ነው እነዚህ ሁሉ የማይፈለጉ በአማራው ላይ የሚደርሱ ጥፋቶችና በደሎች እንደ አንሙት አባባል መቆም ያልቻሉት? እኮ የትግሉ ግብ ምን ቢሆን ነው አማራው ላይ የሚደርስ ጥፋትና በደል ካልቆመ አገር ሊፈርስ ይችላል ብሎ ማስፈራራት የተፈለገው? ለመሆኑ ትሕነግና ኦነግ ናቸው የሚባለውን ጥፋትና በደል አስቋሚ ወይስ የኢትዮጵያ ሕዝብ? እኮ ማነው አንሙት የሚለው ጥቃት ጠንሳሻና ፈጻሚ የዜግነትና የአንድነት ፖለቲካ አራማጁ ወይስ አሁን ወዳጅ ተብለው ተባባሪ የሆኑት ትሕነግና ኦነግ? ኸረ ወዴት ወዴት ነው ነገሩ ጎበዝ? 

ሲጀመር ይህን የሚለው ወገን የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ንቅናቄ (አፋብን) አካል ከመሆኑ አንፃር በአፋብን አመሰራርት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል። እንደሚታወቀው አፋብን ተመሰረተ መባሉ የብዙ ሕዝብን ቀልብ መሳብና ተስፋ መፈንጠቅ ችሎ እንደነበር የቀርብ ጊዜ ትዝታ ነው። እዚህ ላይ ታዲያ የኢትዮጵያ አንድነት ከአማራ ሕልውና አይበልጥም በሚለው የአማራ ብሔረተኛና አማራው ከተለያየ ማንነት ካላቸው ኢትዮጵያዊያን ጋር ከዚህ በፊት ማለትም ከ1981 በፊት እንደነበረው በሕብር አብሮ መኖር ይችላል፣ ከዚህ በፊት ተፈጸመ የሚባል በደል እንዳይደገምም አድሏዊ ከሆነው የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት በተጻራሪ ፍትሃዊ ሥርዓት በመትከል የኢትዮጵያን አንድነት ማረጋገጥ ይቻላል በሚለው ወገን መካከል ያለው ልዩነት እንዴት ተፈትቶ ነው የሚል ጥያቄ ተገቢና አጥጋቢ መልስ የሚሻ ጉዳይ ሆኗል። ለዚህ ጥያቄ የበለጠ አግባብነት የሚሰጠው ደግሞ የአማራ ብሔረተኝነትን የሚያቀነቅነው ወገን ከፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ማለትም ከትሕነግና ከኦነግ ጋር መወዳጀትን እንደ ፖለቲካ አቋም መያዙን የማይቀበል አካል በፋኖ ውስጥ መኖሩ ነው። 

ይህንንም ተከትሎ የአፋብን ሌላ ወገን ማለትም የጎንደር ጠቅላይ ግዛት በላይ ዘለቀ እዝ ይህንን መሰል ትብብር እንደማይቀበል በሐምሌ 5 2018 ላይ ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ ይታወቃል። የአፋብን ጎንደር ጠቅላይ ግዛት በላይ ዘለቀ እዝ በዚህ መግለጫው የአማራ ሕዝብን በጠላትን ከፈረጁና በኢትዮጵያ አንድነት ከማያምኑ እንዲሁም የአማራን ዕርስቶች በመውረር የራሳቸውን አገር ለመመስረት አልመው ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር የምናደርገው ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖርም ሲል ግልጽ አቋሙን አሳውቋል። እንደሚታወቀው እዚህ ላይ ከተጠቀሱት ውስጥ አማራውን የዘመን ጠላት ብለው የፈረጁና በኢትዮጵያ አንድነት የማያምኑ ነገር ግን የአፋብን አንድ ወገን ተባብሬ አብሬያቸው እየሰራሁ ነው የሚላቸው ደግሞ ትሕነግና ኦነግ ሲሆኑ የአማራን መሬት በመውረረ ወደ ትግራይ ክልል በኃይል አካሎ የይገባኛ ጥያቄ የሚያነሰውና የመገንጥል ጥያቄውን ያልተወው ትሕነግ ነው;። ኦነግም ከኢትዮጵያ የመገንጠል ፍላጎቱን ያላነሳና እስካሁን ድረስ ለዚህ እንደሚታገል እያሳወቀ ያለ ድርጅት ነው። 

ስለዚህ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ በሆነ ፕሮፓጋንዳ ታጅቦ በሕዝብ ላይ በአጠቃላይና በአማራው ላይ በተለይ ለአመታት ሲፈጸም ለኖረ የተለያየ ወንጀል ተጠያቂ ከሆኑት ትሕነግና ኦነግ ጋር አብሮ ለመስራት መወሰንና ለሥርዓቱ መገርሰስና በሕገ-ሕዝብ ላይ መሰረት ያደረገ ሥርዓት ለመትከል ራዕይ ሰንቆ የሥርዓቱ ጋሻ ጃግሬዎችን እየታገለ ያለ ወንድምን ኢትዮጵያዊም አማራም ነን ስላለ ብቻ ለማጥፋት ማሳደድና መግደል በምንም አመንክዮ አብረው የሚሄዱ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ይህንን አቋም ተከትሎ የሚከሰት ምንም ነገር የአማራውን ህልውና በአስተማማኝና በዘላቂነት ከማስጠበቅ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ የአማራ ብሔረተኝነትን የሚያቀነቅነው እንደ አንሙት ያለ ስብስብ መለስ ብሎ ደግሞ “ከኢትዮጵያ ጋር ከኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ፀብ የለውም ተገንጣይም አይደለም” ማለት ጅልነት ነው። ምክንያቱም ሲጀመር ለአማራው የህልውና አደጋ ተጠያቂ የሆነውን አድሏዊ የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት አናስነካም ከሚሉት ጋር ተባብሮና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ማለትም የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚፈቅደውን ለመተግበር ከሚዝቱ ጋር እያበሩ ስለኢትዮጵያ አንድነትና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ፀብ የለንም ማለት ዶሮን ሲያታልሏት ,…በመሆኑ ነው፡፡ 

ሆኖም ግን እንደ አንሙት ትግሉ በአማራ ብሔረተኝነት እሳቤ እየተመራና ኢትዮጵያዊነትን እየተጠየፈ ነገር ግን ከትሕነግና ከኦነግ ጋር እየተወዳጀ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያም ሆነ ስለሕዝቧ ብሎም በቃለ ምልልሱ መጀመሪያ ላይ እንዳለው አማራውን ከድህነትና ኋላቅ ቀር ኑሮ መገላገል እንደሚወራው ቀላል አይሆንም። ሲጀመር ይህ የአማራ ብሔረተኛነትን የሚያቀነቅን ወገን ቅድሚያ ለአማራ ሕዝብ ጥቅም የሚሰጥና ኢትዮጵያዊነትን የሚጠየፍ በመሆኑ እንደው እንደሚመኘው የመንግሥት ሥልጣን ቢይዝ እንኳን እንደ ግብረ አበሮቹ ትሕነግና ኦነግ የራሱንም የሌሎች ኢትዮጵያዊያንንም መብት በእኩል እውቅና ሰጥቶ ፍትሃዊ በሆነ ሥርዓት ለማስተዳደር ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ ወርዶ የተወሸቀበት ማንነት አይፈቅድለትም። በመሆኑም አማራው ከኢትዮጵያዊነት በላይ ነው በሚል የጎሳ ፖለቲካ እሳቤ እየተመሩ በተመሳሳይ መስፈርት ተደራጅተው ካሉ ከትሕነግና ኦነግ ጋር በመወዳጀት በአገዛዙ ላይ የሚገኝ ድል ቢኖር እንኳን ማንም የማንም የበታች መሆንን ስለማይፈልግ ኢትዮጵያዊያንን በፍትሃዊነት ማስተዳደርም ስለማይፈለግ አብሮና ተቻችሎ ከመኖር ይልቅ ለሁሉም የራስን ሉዓላዊ መንግሥት የመመስረት ዕድሉ የበለጠ ሰፊ እንደሆነ ነው ካለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት መረዳት የሚቻለው። 

ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የትብብሩ አካላት ሕዝባችን የሚሉትን ‘ነፃ የሚያወጡ’ መሆናቸውን ከስማቸው ማወቅ መቻሉ ብቻ ሳይሆን አንዳንዶቹ እንደውም በግልጽ ቋንቋ ያለውን የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚፈቅደውን አንቀጽ ‘ሕዝባቸው’  እንዲተገብር እንደሚፈልጉ ማሳወቃቸወና የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ማፍረስ ግባቸው እንደሆን ጭምር የሚዝቱ መሆናቸው የሚታወቅ በመሆኑ ነው። እዚህ ላይ ከዚህ በፊት በ1985 ላይ ሻቢያ የኤርትራ ክፍለ አገርን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል በጣም የሚፈልግ በመሆኑ የተከተለውን ማለትም ለሕዝቡ ያቀረበውን ‘ነፃነት ወይስ ባርነት’ የሚል የሸፍጥ አካሄድን ማስታወስና አሁንም በተለይ እንደ ትሕነግና ኦነግ ዓይነቶቹ ‘የሕዝባቸውን ነፃነት’ እንደሚፈልጉ ግልጽ ያደረጉ ድርጅቶች ተመሳሳይ መንገድ በመከተል ኢትዮጵያን መበተን የሚችሉበት ዕድል የለም ማለት አይቻልም። በመሆኑም ይህን የሚባለውን ትብብር አጥብቆ መዋጋት ለኢትዮጵያውን በድፍኑና ከድህነትና መሃይምነት ተገላግሎ በአገሩ በሰላም ወጥቶ ገብቶ ኑሮውን ለመሻሻል ለሚፍልግ የተለያየ ማንነት ላለው ዜጋ የህልውና ጉዳይ አድርጎ መውሰድ ግዴታው ነው። 

ይህንን ማለት ግድ ያለው እንደሚታወቀው ሲፈጠሩ ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ልማት ከሆኑ እንደ ትሕነግና ኦነግ ከመሳሰሉ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ አንድነት መገለጫ የሆነውን ኢትዮጵያዊነት ብሎም የሕዝብን ሰላምና ደህንነት መታደግና ማስጠበቅ ማለት ከእባብ ዕንቁላል እርግብ መጠበቅ ስለሚሆን ነው። ምክንያቱም በተለይ ትሕነግና ኦነግ አናስነካም የሚሉት የጎሳ ፖለቲካ እሳቤ ላይ የተመሰረተ፣ በተፈጥሮው ጠላት ፈላጊና አድሏዊ በሆነ ሥርዓት ውስጥ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ እንኳን ሳይጣሉ በእኩል ማስተዳደር እንዳልቻሉ ታሪካቸው ያሳበቀው ጉዳቸው በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚነገረው አይደለም። ምክንያቱም እነዚህ ኃይሎች የኢትዮጵያ ሕዝብን በፍትሃዊነት የሚያስተዳድር ሥርዓት እውን በማድረግ ተከባብሮና ተቻችሎ አብሮ እንዲኖር የማይፈልጉ በመሆናቸው የኢትዮጵያ አንድነት ከሦስት አሥርት አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ እንዴት ለአደጋ እንደተጋረጠ ማየት ተችሏል። 

በተጨማሪ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ከሚጠየፍና “ዞር በል” ከሚል የአማራ ብሔረተኛም የተሻለ ውጤት መጠበቅም እንደማይቻል እየታየ ነው። ከጎሳ ፖለቲካ ተፈጥሯዊ ባህሪ በመነሳት አድሏዊነት እንጂ ፍትሃዊነት ተቀባይነት ስለማይኖረው በአማራው ‘ፊታውራሪነት’ ለሚጸና መንግሥት ትሕነግና ኦነግ አሜን ብለው እንደማይቀበሉ ሁሉ በተገላቢጦሽም የአማራ ብቻ ጠበቃ ነኝ ባዩም ለማናቸውም የበታች ሆኖ መኖር ሊፈልግ አይችልም። እንግዲህ ከአብዛኛዎቹ ተባባሪ ድርጅቶች ስምና ግባችን ከሚሉት የዛቻ አቋም በመነሳት መጠበቅ የሚቻለው ‘ሕዝባችን’ የሚሉትን ወገን ከኢትዮጵያ በመገንጠል የየራሳቸውን ሉዓላዊ አገር ለመመስረት ያላቸውን ፍላጎት ተከትሎ የሚወስኑት ውሳኔ የተለያየ ማንነት ያላቸውንና አገር መሆን የማይችሉ ኢትዮጵያዊያንን እጣ ፈንታ እጅግ አስቸጋሪ እንደሚያደርግ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተለያየ ማንነት ካለው ወገኑ ጋር የተጋባና የተዋለደ በመሆኑ በማንነት መስፍረት የዚህኛው ወገን ነኝ ማለት የማይችል ሕዝብ ቁጥሩ ቀላል ባለመሆኑ የዚህ ሕዝብ ዕጣ ፈንታም እንዲሁ እጅግ አስቸጋሪ እንደሚሆን ለመረዳት ጠቢብ መሆን አይፈልግም። 

ስለዚህ በብዙ አገራት ውስጥ የተለያየ ማንነት ያለውን ሕዝብ ከጎሳ ፖለቲካ በተቃራኒ በፍትሃዊነትና በሕግ የበላይነት ማስተዳደር እንደተቻለው ሁሉ ኢትዮጵያዊያንም እሩቅ አሳቢ ሆነው የዜግነት ፖለቲካን መምረጥ ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ከሦስት አሥርት አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ አድሏዊው የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት ካደረሰባቸው ሰቆቃ ትምህርት ወስደው፣ ዜጋው በማንነቱ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ብቻ የሚከበርበት በሕገ-መንግሥት ሳይሆን በሕገ-ሕዝብ ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ ሥርዓት መዘርጋትና በአንድነት በድህነትና መሃይምነት ላይ መዝመት የሚችል እምቅ ኃይል ፈጥረው አገራዊ ልማትን እውን በማድረግ አገራቸውንም እራሳቸውንም ከኋላ ቀርነት አላቀውና የኑሮ ደረጃቸውን አሻሻለው ለመኖር መወሰን የህልውና ጉዳይ ማድረግ ስላለባቸው ነው። 

ከዚህ በመነሳት መደምደም የሚቻለው የአማራ ብሔረተኝነትን የተቀበለ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትን ደግሞ የሚጠየፍና ለአማራው መጠቃት እንደምክንያት የቆጠረ ወገን መፈጠሩ የአማራ ሕዝብን በተለይና የኢትዮጵያውያንን ህልውና በአጠቃላይ በአስተማማኝና በዘላቂነት ለማስከበር የሚደረግ ትግል ላይ ከፍተኛ ደንቃራ እንደሆነ ነው። ይህ ስብስብ የፋኖ አንድነት እንዳይሰምር፣ ትግሉ ግልጽ የሆነ አገራዊ ራዕይ እንዳይኖረው፣ አማራም ኢትዮጵያዊም ነኝ ያሉ የአማራ ፋኖ ታጋዮችን እያሳደደ በመግደል የትግሉን ዕድሜ ማራዘም ሳያንሰው ከትሕነግና ከኦነግ ጋር መተባበሩና ይህን ተከትሎ ለሚከሰት አሉታዊ ሁኔታ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ይሆናል። በተጨማሪም ተፈጠረ የሚባለው ትብብር ለሰላሳ አምስት አመታት አገርን ለመፍረስ አደጋ ያጋለጠና ሕዝብን ለሰቆቃ ኑሮ የዳረገ ሥርዓትን አስወግዶ በሕገ-ሕዝብ ላይ የተመሰረተ፣ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ፍትሃዊ ሥርዓት በመትከል የአገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን አንድነት ማስጠብቅ እንደማይችል መደምደም ይቻላል። ይህን ለመሰለ ድምዳሜ የሚከተሉትን የተለያዩ ምክንያቶች ማቅረብ ይቻላል። 

1- ሲጀመር ይህ አማራ አማራ የሚለው ወገን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አንድነት በመፍጠር መታገል ሳይሆን ያለውን ሥርዓት የተከሉ ጽንፈኞችን መንገድ ተከትሎ እራሱን በአማራ ማንነት ለመገደብ የመረጠ መሆኑ። 

2- ይህ በጎጥ ውስጥ መወሸቅን የመረጠ ወገን ኢትዮጵያዊነትን የሚጠየፍ በመሆኑ ከሰላሳ አመታት በላይ ችግር ፈጣሪ የሆነውን አድሏዊ ሥርዓት በማስወገድ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሰው በመሆኑ ብቻ መብቶቹን ማስከበር በሚችል በሕገ-ሕዝብ ላይ መሰረት ባደረገ ፍትሃዊ ሥርዓት ለመተካት ከሚሹት ጋር ሳይሆን የሥርዓቱን መቀጠል ከሚሹት ጋር መተባበሩ ለሥርዓት ለውጥ የሚደረግ ትግል ላይ ደንቃራ መሆኑ።

3-ከእነዚህ ተባባሪ ከሚባሉ በኢትዮጵያዊነትና በሕዝብ አንድነት እንደማያምኑ ከስማቸውና ከታሪካቸው የሚታወቅ አብዛኛዎቹ ኃይሎች ብሎም አማራም ኢትዮጵያዊም ነኝ የሚል ወንድም ፋኖን እያሳደደ የገደለ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚጠየፍ፣ አማራ አማራ ባይና የትብብሩ ‘ፊታውራሪ” ነኝ የሚለው የፋኖ ወገን ጭምር ለለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትም ሆነ ስለሕዝብ አንድነት ይጨነቃሉ ብሎ መጠነበቅ ስለማይቻል። 

4- ለትብብሩ አስፈላጊነት የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ከሚል አባባል በመነሳት የትብብሩ ‘ፊታውራሪ’ ነኝ የሚለው ይህ የአማራ ብሔረተኛ ያለውን የብልጽግና አገዛዝ የሁሉም የትብብሩ አካላት የጋራ ጠላት ነው ብሎ መቀበሉ መሬት ላይ ከሚታየው ሃቅ ጋር የሚጣረስ መሆኑ። ምክንያቱም ብልጽግና በተለይ ከትሕነግ ጋር ያለው ልዩነት በመካከላቸው የማይታረቅ ቅራኔ ኖሮ ሳይሆን ሊታረቅ ከሚችል ልዩነት ማለትም የበጀት፣ የሥልጣንና የግዛት ይጽናልኝ በመሳሰሉ ላይ የተፈጠረ በመሆኑ ነው። ከኦነግ ጋር ያለው ልዩነት በመሰረታዊነት በኦሮሞ ድርጅቶች በሚቀነቀነው ለምሳሌ በተረኝነትና ኦሮሙማን በማስፈን ብሎም በፀረ-አማራነት ላይ ሳይሆን የኦሮሞ ሕዝብን እኛ እናስተዳደር ማለትም የሥልጣን ጥያቄ ነው። አማራው ከብልጽግና ጋር ያለው ልዩነት ግን በስሁት ትርክት ላይ ተመስርቶ የአማራ ሕዝብ የዘመን ጠላት ተብሎ ተፈርጆ አሁን ወዳጅ የሚባሉት ትሕነግና ኦነግ በመንግሥት ሥልጣን ላይ በመፈራረቅ ከ1983 ጀምሮ የፈጸሙበት የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲቀጥል የፈቀደና በህልውናው ላይ የመጣ ነው። የብልጽግና አገዛዝ የነበረውን ጭፍጨፋ፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመትን ማስቆም ሳይሆን አባብሶ ያስቀጠለና ጭራሽ ጦርነት አውጆ ትምህርት ቤቶቹን፣ የጤና ጣቢያዎቹን፣ የእርሻ መሣሪያዎቹንና ምርቱን ሳይቀር በማውደም እንደ ሰው የመኖር መብቱን የገፈፈ በመሆኑ በአማራ ሕዝብና በአገዛዙ መካከል ያለው ልዩነት በማይታረቅ ቅራኔ የሚገለጽ ነው። 

5- ከኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ በመነሳት በተደጋጋሚ የሕዝብ ትግል ሊደናቀፍና የሕዝብ ሰቆቃ እየተባባሰ ሊቀጥል የቻለው የነበሩት ትግሎች በሕገ-ሕዝብ ላይ መሰረት ያደረገ ሥርዓት ለመትከል ግብና ራዕይ የበራቸው ሳይሆን የአገዛዝ ለውጥ ላይ ብቻ ያተኮሩ በመሆናቸው እንደሆነ ይታወቃል። አሁን ይህ የአማራ ብሔረተኛ የፈጠረው ትብብርም በዚሁ መንገድ በመሄድ ያለውን አገዛዝ ማስወገድ ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ ከሥርዓቱ ጋሻ ጃግሬዎች ጋር ከሚደረግ ትብብር የሚፈለገውን የሥርዓት ለውጥ እውን ማድረግ ስለማያስችል።  

6- የትብብሩ አካላት የሚባሉት አንዳንዶቹ ካላቸው ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ልማት አቋም አንፃር የኢትዮጵያ ሕዝብን ለሰቆቃ ኑሮ ለዳረገ ሥርዓት ጋሻ ጃግሬነታቸውን ተከትሎ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚፈቅደውን አንቀጽ ተጠቅመው ከኢትዮጵያ ነፃ ለመውጣት እስካሁን ድረስ የሚዝቱ መሆናቸው ከነሱ ጋር የሚደረግ ትብብር አገርን የሚበትንና ይህንንም ተከትሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መቅሰፍትን እንጂ የሚፈልገውን በረከት ሊያመጣ አለማስቻሉ። 

የአማራ ሕዝብን በሕይወት የመኖር መብትን የገፈፈ ሥርዓት በጥቂት ጽንፈኞች ከሕዝብ እውቅና ውጪ በግድ መተግበሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ ላለፉት ሰላሳ አምስት አመታት ያክል ጊዜ የመከራ ገፈት ሲጋት ኖሯል። ከ1983 ጀምሮ ጥልቅ አስተዳደራዊ ብልሽትና ሙስና እንዲሰፍን፣ ምጣኔ ኃብታዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶች እንዲባባሱ በመሆናቸው በሰላም ወጥቶ መግባት አለመቻል ብሎም የኑሮ ውድነት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ መጠን ከጥቂቶች በስተቀር የሁሉንም ዜጋ በሕይወት መኖር እየፈተነ መቀጠሉ የማይፈለግ ብቻ ሳይሆን የሚዋጉት ሆኗል። በተጨማሪም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላም እጦት፣ በኑሮ ውድነትና በወንጀሎች መበራከት እየተሰቃየ ባለበት አላባራ ባለ ጦርነት እየደረሰበት ያለው መከራ ሥርዓት ወለድ በመሆኑ ሥርዓቱንና ጋሻ ጃግሬዎቹን አምቢ ማለት የህልውና ጥያቄ ሆኗል። 

በመሆኑም ሕዝቤንና ወገኔን ብሎም አገሬን የሚል ሁሉ አሁን ካለው የኢትዮጵያና የሕዝቧ ሁኔታ አንፃር የአገዛዝ ለውጥ ሳይሆን የሥርዓት ለውጥ ብቻ አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሰጥ መቀበል ይገባዋል። ይህም ሥርዓት የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት፣ የተለያየ ማንነት ያለው ኢትዮጵያዊ ዜጋን ሁሉ ሰው በመሆኑ ብቻ የሰብዓዊና የዲሞክራሲ መብቶቹ የሚከበሩበትና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ፣ የአገር ሉዓላዊነትንና የሕዝብ አንድነትን የሚያጸናና የሚያረጋግጥ እንዲሆን በሕገ-ሕዝብ ላይ መሰረት ያደረገ ፍትሃዊ ሥርዓት ነው። ይህ ከጎሳ ፖለቲካ በተቃራኒ በዜግነት ፖለቲካ እሳቤ ላይ መሰረት ያደረገ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲሰፍን ደግሞ የፋኖም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ይህንን ግልጽ አድርጎና እንደ ራዕይ ወስዶ በጽናት መታገል አለበት። ልብ የሚልና የሚሰማ ካለ!!! 

ዋቢ ማጣቀሻ 

1 Anchor Media የፋኖ ትግልና ”ኢትዮጵያኒስት” – ጋዜጠኛ አንሙት አብረሃም – ክፍል 2 የተለቀቀው ሰኔ 9 2017  https://www.youtube.com/watch?v=6a3DBDxrMB4&t=80s 

2 ዝኒ ከማሁ 

3 ዝኒ ከማሁ 

4 ዝኒ ከማሁ

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

4 COMMENTS

  1. ወንድም አበበ፦

    የማከብረው ጋዜጠኛ ሲሣይ መኮንን ከሌላው ከማደንቀው ጋዚጠኛ ከአንሙት ጋር ሲወያይ የተናገረውን እንዲህ ብለህ ጠቅሰኸዋል፡ “አሁንም ቢሆን ስጋቴን አነሳለሁ ይሄ ትግል መስመር ስቶ መረን ወጥቶ ለኢትዮጵያዊነት አደጋ እንዳይሆን ማዕቀፉ አለ ወይ? ይህ አማራው የጀመረው ብሔረተኝነት ወደምንፈራው ወደማትቆጣጠሩት ጽንፍ ወደረገጠ ለኢትዮጵያ አደጋ ሆኖ እንዳይሻገር ከወዲሁ መመካከሩና ቀስ እያሉ ነገሮችን እያዩ መሄድ ጥሩ ነው። …” ይላል። የሲሣይ መኮንን አስተያየት የሚደገፍ ቢመስልም፣ መሬት ላይ ያለውን እውነታም ስላላገናዘበ ሊነቀፍም ይችላል። እኔም በተፈጥሮም ሆነ በሙያ ስምሪት ተጠራጣሪ ነኝ፤ ነገር ግን እዚህ ላይ መሬት ላይ ያሉትን ጽንፍ ያለመርገጥ ዋስትናዎች ሲሣይ አላስተዋለም።

    ታዲያ፣ ባለፉት 52 ዓመታት ወደ አደቀቀንና ያወደመን፣ ኢትዮጵያዊ ክብራችንን፣ ስማችንናና ዓለም አቀፍ ዝናችንን ወደ አስገፈፈንን ወደ አንድ ጠባብ፣ ራስ ወዳድ፣ በዝባዥና ባንዳ አረመኔ ቡድን አምባገነን ሥርዓት እንዳንዘቅጥ ዋስትናችን ምንድን ነው ?

    አንደኛው ዋስትናችን የትብብር ለሕልውና አባላት ስብጥር ነው። የትብብሩ አባላት ክቤኒሻንጉል፣ ከጋምቤላ፣ ከኦሮሞ፣ ከደቡብ፣ ከኦጋዴን፣ ከትግሬ፣ ከአፋርና ከአማራ የመጡ ታጋዮች በመሆናቸው ቢያንስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከ90 በመቶው ወስጥ የፈለቁ ናቸው። ሁሉም የታጠቁ፣ ሁሉም ባሉበት በትጥቃቸው ትርምስ መፍጠር የሚችሉ፣ አንዱን ትቶ ሌሎችም ሁሉ እንኳ አገር እናስተዳድር ቢሉ፣ ሰላም ማምጣት ስለማይቻልና ተመልሶ ጦርነትና የሕገ አራዊት አገዛዝ መጋበዝ ስለሚሆን፣ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ዲሞክራሲያዊነትና ሰላም ግንባታ አስፈላጊ በመሆናቸው፣ ትብብሩ ሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲከተል የእርስ በእርሰ ተቆጣጣሪዎቻችንና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዋስትናዎቻችን የትብብሩ አባላት ራሳቸው ናቸው።

    ደቡብ አፍሪቃውያን በ1980ዎች የተባበረችውን ዲሞክራሲያዊት አገር ሲመሠርቱ፣ ብዙ የታጠቁ፣ እርስ በርስ የሚዋጉ ቡድኖች ነበሩባት። ከሌሎች ጋር ቁጥራቸው 26 ነበር። ለምሣሌ፣ የደቡብ አፍሪቃ ኮሚኒስት ፓርቲ፣ የማንዴላ ኤኤንሲና የዙሉዎች ታጣቂ ቡድኖች የሚተያዩት እንደ ጠላት ነበር። ግን፣ አገር በሰላምና በጋራ ለመገንባት ብቸኛው አማራጭ ትብብር መሆኑን ተገንዝበው፣ እርስ በርስ መዋጋቱን አቁመው፣ እርስ በርስ መተማመኑን በሂደታ እያስተካከሉ፣ 26ቱም የሽግግር መንግሥት መሥርተው፣ ከሕገ መንግሥት እስከ ተለያዩ አዋጆች በጋራ በስምምነት አዘጋጅተው፣ ለዲሞክራሲያዊ ምርጫም ራሳቸው ባደራጁት ምርጫ ቦርድና ባዘጋጁት የምርጫ አዋጅ ተመርተው፣ ራሳቸውም የሽግግር መንግሥቱ ጉባዔ አባላት የነበሩት የታጣቂ መሪዎች ተቆጣጣሪ ሆነው፣ በ1986 ዓ.ም. ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃ ተወለደች ። እኛ ጋ ስንመጣ አንድም ታጣቂ እርስ በእርስ እምብዛም አልተዋጋም። ስለሆነም፣ ታጣቂዎች በጠላትነት አይተያዩም። ስለዚህ፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሜዳው ይበልጥ የተደላደለ ነው።

    ሁለተኛው ዋስትናችን፣ የትብብር ለሕልውና አባላት ሕይወታቸውን ለወገናቸው መስዋዕት ለማድረግ ቤት ንብረታቸውን፣ ሥራቸውን፣ ዘመድ አዝማዳቸውን ትተው ከአውሬ ጋር ጫካ የገቡት ለወገን የተሻለ ቀን፣ ሰው በሰውነቱ ብቻ ተከብሮ የአገር እኩል ባለቤት የሚሆንበት ሥርዓት ለመገንባት፣ አንዱ የበላይ ሌላው ዜጋ የበታች የማይሆንበት አገር ለመፍጠር፣ በኢትዮጵያዊነታችን የጋራ የባላገርነት ኩራት የሚሰፍንበት ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካና የአገር አስተዳደር ሥርዓት ለማስፈን፣ በተለይም በተሻለ የማውቀው አፋብን የአማራን ሕልውና ለማስጠበቅ በአማራነት እንዲደራጅ ቢገደድም፣ አባቶቹ አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው የገነቧትን ኢትዮጵያችንን በሁለተኛ ደረጃ ዝቅ አድርጎ የሚያይ ባለመሆኑ፣ አገርና ትውልድ አጥፊውን ጽንፍ የረገጠ ሥርዓት ተቃውመው የወጡ ጀግኖቻችን ሁሉ፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን አስከብረው የአማራንም ሕልውና ከኢትዮጵያዊነት ክብር ጋር ማረጋገጥ ሲችሉ መሆኑን ስለሚረዱና የአማራም ሆነ የሌሎች ወገኖቻችን ሕልውና በጠባብ ውዳቂ ቡድን የአገዛዝ ሥርዓት መረጋገጥ እንደማይችል በሰፊው ስላዩ፣ ፣ ወደ ሕገ አራዊት ተመልሰው የውድቀት አረንቋ ውስጥ ይገባሉ ማለት አይቻልም።

    በነገራችን ላይ፣ እስከ ዛሬ የኮሚኒስት ሥርዓቱን ውዳቂነት፣ የወታደር አገዛዙን ደንቆረነት፣ የጎሣ ቡድኖችን ዝቅጠት፣ ራስ ወዳድነቱ፣ ጠባብነት፣ በዝባዥነትና አገር አጥፊነት ቋቅ እስኪለን ድረስ እየተጋትን ስላየነው፣ አገር መገንጠልም ሆነ ማስገንጠል ተገንጣዩንም ሆነ አስገንጣዩንም ወደ ባሰ አዘቅት የሚወረውር ስሕተት መሆኑን በኤርትራ እየተመለከትን፣ እርስ በርስ እየተጠላለፍን ምንም ዓይነት ጠባብ የቡድን አገዛዝ ውድቀት እንጂ ዕድገት እንደማያመጣልን ባለፉት 52 ዓመታት እየተገደልን፣ እየተሰደድና እያወደምን ስላየነው፣ ዳግም አፋብንም ሆነ ሌሎች የትብብር ለሕልውና ታጣቂ አባላት ያለፈውን ውዳቂ ሥርዓት ይፈልጉታል ብሎ መጠርጠር አስተዋይ አዕምሮ ያላቸው ክቡር ሰብአዊ ፍጡርነታቸውን መካድ ነው። ስለሆነም፣ ባለለፉተ 52 ዓመታት፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን፣ ጎሣ ሳይለይ፣ ተወናብደን በተገዛንበት ጠባብ የሕገ አራዊት ሥርዓት ፍዳቸውን ያዩበት ዘመን ስለነበር፣ ወደዚያ የውድቀት፣ የጠባብ እና ጽንፈኛ ቡድን አገዛዝ ዘመን እንዳንመለስ ሁለተኛው ዋስትና ይኸው አስከፊ ያገዛዝ የጋራ ተሞክሯችን ነው።

    ሶስተኛው ጽንፈኛነትን የሚዋጋልን ዋስትናችን ትብብሩ ሲታወጅ የተሰጠን ተስፋ “ለሀገሪቱ ሰላምና ለሕዝቦች ቀጣይ ሕልውና ሲባል ሀቀኛ፣ ታማኝ፣ ሁሉንም ያካተተና ያሳተፈ ሕዝባዊና ሕገ መንግሥታዊ ውይይት (Constitutional Dialogue) በማድረግ ወሳኝ ሕዝባዊና ሀገራዊ ጥያቄዎችን በሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ መመለስ ይሆናል።” የሚለው ነው። ይህ ተስፋ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ እንኳን ለመተባበር ለመነጋገርም የማይፈልጉ የነበሩት አያሌ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ከትግሬ፣ ከአፋር፣ ከኦጋዴን፣ ከደቡብ፣ ከጋምቤላ፣ ክቤኒሻንጉል፣ ከኦሮሞና ከአማራ ጎሣዎች ተሰባስበው፣ ብስለትና አስተዋይነትን ተላብሰው፣ የቀድሞ ጽንፈኛ አመለካከታቸውን አርቀው፣ በኢትዮጵያ አንድነትና በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተማምነው፣ ለወራት ተነጋግረውና ተስማምተውበት የወጣ የትብብር ለሕልውና መግለጫ ነው። የኢትዮጵያን ያለፉት ዘመናት የቡድን አገዛዝ የጋራ ውድቀት የተረዱ ታጋዮች መግለጫ ነው። የኢትዮጵያን አንድነት ያለ ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ፣ ከወቅቱ ከፋፋይና ውዳቂ የቡድን ሕገ መንግሥት ለመውጣት በሕገ መንግሥታዊ ውይይት አገራዊ ጥያቄዎችን ከሕዝቡ ጋር በመወያየት መልሶ፣ ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት የምታይ ጠንካራ ዲሞክራሲያዊት አገር ለመመሥረት እንደተስማሙ መግለጫው ይነግራል። ይኸ በምንም ዘመን ተሰምቶ የማያውቅ ታሪካዊ ስምምነት ወደ ሌላ ኋላ ቀር ጽንፈኛ ሥርዓት እንዳንወድቅ ሶስተኛው ዋስትናችን ነው።

    ስለሆነም፣ የአማራ ብሔርተኛነት ወይም ሌላ ታጋይ ቡድን ወደ ጽንፈኛነት ይሸጋገራል ብሎ መስጋት መሠረት የለውም። በዚህ ላይ፣ አፋብን ደግሞ ደጋግሞ ኢትዮጵያዊ ዓላማውን ከብሔር ሕልውናው መከበር ለይቶ እንደማያየው የገለጠ ሲሆን፣ ሁለተኛም ለትብብር ለሕልውና ምሥረታ ያደረገውን ከፍተኛ የተሳካ ጥረት አገናዝበን፣ ሶስተኛም በአባቶቹ ደምና አጥንት የተገነባችውን ኢትዮጵያን ሰላምና ዕድገት በቡድን ጥቅም፣ ዝናና በማያዛልቅ የሥልጣን ልክፍት እንደማይለውጠው ማመን ይገባል።

    ለማጠቃለል፣ ካለፉት 52 ዓመታት ውድመት፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ ስደትና ችጋራ ትብብር ለሕልውና ሲገላግለን፣ ይቺን ሰፊ ለም መሬት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሥራ ፈት ሠራተኛ ወጣት፣ ያለ ጥቅም የሚፈስሱትን አያሌ ወንዞቻችንንና ሰፊ የማዕድን ሀብታችንን ከታደልነው የአየርና የመሬት ጠባይ ጋር አቀናጅተን በጋራና በተሻለ አስተዳደርና አመራር በማልማት የአፍሪቃ ከበርቴ አገር ለመገንባት ብዙ ጊዜ አይወስድብንም። ይህን እውን ለማድረግ ግን፣ ራሳችን የራሳችን ጠላት መሆናችንን በማቆም፣ ለትብብር ለሕልውና ያልተቆጠበ ድጋፍ መስጠቱ ያዋጣል።

  2. አማራ ራሱን መብላት የጀመረው ብሄሩን ታኮ ትጥቅ ካነሳ በህዋላ ነው። ይህን የብሄር ነክ ትጥቅ ማንሳት ለዘመናት ወያኔና ሻቢያ ሲቆሰቁሱት የኖሩት በመሆኑ ፋኖ የአማራ ነጻ አውጭ ነኝ ብሎ በየመንደሩ ሲሯሯጥ የወያኔና ሻቢያ እኩይ እቅድ በመሳካቱ ለደስታቸው ወሰን የለውም። ፋኖ የአማራን ህዝብ ከከፍታ ማማ ላይ ያወረደ ያልነበረውን የጠባብ ብሄርተኝነት እሳቤ በህዝብ ላይ የጫነ ክፉ ስብስብ ነው። በየጫካውና ገደሉ የሚርመሰመሰው ይህ ስብስብ ጊዜ አግኝቶ ወደኋላ ተመልሶ ታሪክን ቢያገላብጥ አንድ ጭብጥ ነገር ያገኝ ነበረ። ግን በደመ ነፍስ ለሚንገዳገድ ቀምቶ አዳሪ ስብስብ ሰክኖ ነገሮችን የመመልከቻ ጊዜ የለውም። ጉዳዪ እንዲህ ነው። በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን የወረሩ የውጭና የውስጥ የብሄር ሰካራም ታጋይ ነን ባዪች ሁሉ ያተኮሩት የአማራ ህዝብን ማዳከም ብሎም ማጥፋትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ማውደም ነው። ለሁለተኛ ጊዜ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት የአምስት አመት የመከራ ጊዜ የፈጸመችው በድል አማራን ማጥፋት ነው። ግራዚያኒ ወደ ሞሶሎኒ የላከው አንድ መልዕክት እንዲህ ይላል “በተለይም አማራ ተለይቶ እንዲጠፋ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ” በማለት በየስፍራው እየተለቀሙ እልፍ የአማራ ልጆች በጥይት ተደብድበዋል። ከዚያ በህዋላ ፍቅፋቂው የሻቢያና የወያኔ የፓለቲካ ቱልቱላ እንደሚለው ሳይሆን እውነቱ ሁለቱም ሃይሎች ለህዝባቸው አማራ ጠላትህ ነው በማለት ለዘመናት የፈጠራ ጥላቻን ግተውታል አስግተዋል። የኦሮሞው ጽንፈኛም የእነዚህ ሃይሎች የክፋት ዲቃላ ነው። ይህ የሚያሳየው በዘመናት መካከል የአማራ ህዝብ የደረሰበትን በደልና አሁንም እየደረሰበት ያለውን መገፋትና መከራ ነው። ታዲያ በምን ሂሳብ ነው ፋኖ የአማራን ህዝብ አሳንሶ በብሄሩ መሰለፉ? ይህ ለአማራ ህዝብ አይመጥንም። የአማራ ህዝብ የሚያቃጥል ሃገራዊ ፍቅርን የተላበሰ፤ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ሆኖ ዳር ድንበርን ያስጠበቀ ህዝብ ነው። በብሄሩ ስም ነጻ እናወጣሃለን የሚሉ ጉዶች አያስፈልጉትም። የሚያስፈልገው በሰላም ገብቶ መውጣትና ከወገኖቹ ጋር ሃገርና ህዝብ መጠበቅ ነው።
    ምን አልባት በሃሳብ የዘገዪ እኩይ ፓለቲከኞች ፋኖ እኮ ለሃገር አንድነትና ለህዝቦች ሰላም ነው የሚታገለው የሚሉን ካሉ አፋቸውን በእጃቸው ላይ ቢጭኑ ይመረጣል። በዘርና በብሄሩ ተሰልፎ ሃገር አንድ የሚያረግ ለራስ ሲቆርስ የማያሳንስ ምንም አይነት ታጣቂ በምድር ላይ የለም። 27 ዓመት በግፍ ኢትዮጵያን የገዛው ወያኔ ባርነት ትግራይ ለዚህ ዋና ማሳያ ነው። ሁሌ ለትግራይ ህዝብ በማለት የሚዳፍቀው ወያኔ ለትግራይ ህዝብ ያተረፈለት መከራ፤ ሞትና መሰደድ ብቻ ነው። ይኸው እንሆ ለ 4ኛ ጊዜ በለኮሰው ጦርነትም ሰው አፈር ዘግኖ መቃብሩ ላይ ቆሞ እየረጨም ቢሆን አለን እንመለሳለን በማለት ደብረጽዪን ሲደነፋ መስማት ያማል። ይህ እብደት አይደለም የሚሉ ካሉ ራሳቸው የታመሙ ብቻ ናቸው። መቼ ነው የኢትዮጵያ ፓለቲከኞች ከፉከራ ይልቅ ሰላምን መርጠው በቃ በቃ ተባብለው በሰላም መኖር የሚጀምሩት? ስለሆነም በዚህም በዚያም ተባለ የአማራ ብሄርተኝነት ኢትዮጵያዊነትን የሚያኮሰምን የጅል ሃሳብ ነው። ዛሬ በሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ስንት መሻሻል እየተደረገ ፋኖ መንገድ እየዘጋ፤ የመማሪያ ት/ቤቶች ላይ እየሰፈረ፤ ህዝብ እያስፈራራና እየገደለ የአማራ ህዝብ መከራ ውስጥ በመክተቱ ረሃብ በአንዳንድ ስፍራዎች መግባቱን ሰምተናል። አፈናውና ክፍያው ታፋኝ ለማስፈታት፤ ዝርፊያው፤ የሚያርስበትን በሬ ለሰንጋ መቀማቱ ወይም በተዘረፈ ሃብት በርካሽ እየገዙ መብላቱ፤ የብልጽግና ባለስልጣን ነህ በማለት አድብቶ በጥይት ሰዎችን መግደሉ ይህ ሁሉ የአማራን የመከራ ቀናት ማራዘም እንጂ አንድም እዚህ ግባ የሚባል ነገር ፋኖ ለአማራ ህዝብ አያስገኝም። እንኳን ፋኖ 30 ዓመታትን የተፋለመው ሻቢያ ነጻ ሃገር ነኝ የምትለው ኤርትራ ዛሬ የአፍሪካ ስሜን ኮሪያ በመባል ሲሾፍባት መስማት እንዴት ያማል። ያ ሁሉ መተላለቅ ምን ትርፍ አመጣ? ሞት፤ እርዛት፤ ስደት ወዘተ አንድ በቅርብ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ከሚሰደድ ዜጎች መካከል ኤርትራ 22% ይዛለች ይላል። ይቺ ትንሽ ሃገር ለምን ይህ ሁሉ ህዝብ ነፍሴ አውጭኝ እያለ ለመከራና ለሞት ራሱን ያጋልጣል? ልክ እንደትላንቱ ዛሬም ኤርትራ የሞት ሃገር በመሆኗ ነው። ተመድ በቅርቡ 550 ገጽ በፈጀ ትንታኔው ስለ ኤርትራ ያጠናቀረውን ዘገባ ላነበበ እየየ ያሰኛል። ለዚህ ነው ብሄርተኞች ድውያን ናቸው የምንለው። ቆመንለታል ለሚሉትም ህዝብ አይጠቅሙም። ፋኖ/ኦላ/ወያኔ/ሻቢያ ሁሉም አንድ ናቸው። ህመምተኞች!
    እኔ የፋኖ ነገር ያበቃልኝ ለዘመናት የአማራን ህዝብ በመርዝ፤ በየሰበቡ፤ በአፈና እና ግድያ በሲስተም ካዳከመው ወያኔ ጋር አብሬ እሰራለሁ ካለ በህዋላ ተጠማጅ እንጂ ጠማጅ እንዳልሆነ ገብቶኛል። ወያኔ የሃገሪቱን አንጡራ ሃብት ለራሱ ጥቅም ያደረገ ለ 20 ዓመታት ትግራይን ከሻቢያ የጠበቀለትን የስሜን እዝ በሴራ በተኙበት ያረደ፤ ሲኖ ትራክ የነዳ፤ ከግብጽና ከሱዳን ሃይሎች ጋር ሆኖ ሃገርን የሸጠ ስብስብ ነው። በምንም ሂሳብ አማራን እወክላለሁ የሚል ስብስብ ከወያኔ ጋር እንኳን አብሮ መስራት ሰላምታም አያስፈልግም ከሚሉት ወገን ነኝ። እንዴት በአርሲ፤ በባህርዳር፤ በቤኒሻንጉል በወለጋ በወሎ ወዘተ የፈጸመው በደል ይረሳል? ስለዚህ ፋኖ የፓለቲካ ቁማሩን በመተው ለብልጽግና የፓለቲካ ጥያቄዎችን አቅርቦ በመደራደር ለመላው ህዝባችን ሲባል ትጥቅ በመፍታት የሰላም ኑሮ ቢመርጡ ማለፊያ ነው እላለሁ። ሌላው የፓለቲካ አጀንዳ ሁሉ መዳከርና ማስዳከር ነው። አማራ ጠባብ ብሄርተኛ ሆኖ ኢትዮጵያዊ መሆን አይችልም። እይታችን የላቀና ሌሎች የሚማሩበት ካልሆነ በራፍ ላይ ሆኖ ሃገሬ ይሄ ነው ማለት የፓለቲካ ማናጃ መሆን እንጂ ለአማራ ህዝብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠቃሚነት የለውም። ብልጽግናም በየስርቻው እንበለ ፍርድ ያገትካቸውን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ፍታ! ዘምነናል፤ ታጥቀናል፤ ነቅተናል የሚል መንግስት በሰው ሃሳብ አይደነግጥም። እንግዲህ በዚህ አማችና አሻሚ ወሬ በሚናፈስበት የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን እውነትን ፈልጎ ማግኘት እየከበደ መቷል። ግራም ነፈሰ ቀኝ ይህን የብሄር ፍቅፋቂ ፓለቲካ ወደ ጎን አድርገን ለአንዲት ሃገርና ህዝብ ጠንክረን ካልሰራን መገዳደላችን ቀጣይ ነው። አማራ የሚጠጣ ውሃ አፍላቂ እንጂ ድልድይ ሰባሪና መንገድ ዘጊ፤ የህብረተሰብ መገልገያ ተቋሞችን ዘራፊ ጠበንጃ አንጋች ስብስብ አያስፈልገውም። ለሃገር አንድነትና ለህዝባችን ሰላም የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። ሌላው ሁሉ ለወፎች የሚሰጥ ሰው የማይበላው እንክርዳድ ነው! በቃኝ!

  3. ወንድም አበበ፦
    ይህ ድርሰት በወንድም አበበ ወይም በደርጉ ዘመን የምኒልክ ጋዜጣ ባለቤትና ተወዳጅ አዘጋጅ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ይልቅ በጭፍን ሥልጣንና ጥቅም አምልኮ ልክፍት፣ ዋና ዓላማውን ደብቆ በጸጉር ስንጠቃ ላይ በመሰማራት ኢትዮጵያን መሰላል አድርጎ የግሉን ግብ ለማሳካት ውሸት ደርድሮ ቢደርሰውም የተለየ አይሆንም ብሎ መገመት ይቻላል።

    በአፋብን ውስጥ የነበረው ቅራኔ እስክንድርና የመገናኛ ብዙሀን ጀሌዎቹ ሆን ብለው የዘሩት በሽታ ነው። አፋብን ለአማራነት ቅድሚያ ሰጥቶ ኢትዮጵያዊነትን ተጠየፈ የሚባለውም ቅጥፈት በቅርቡ በትብብሩ መግለጫ ላይ ፉርሽ ስለተደረገ ተጨማሪ ማስተባበያ አያሻውም። በመግለጫው እንዳየነው፣ አፋብን የአማራን ሕልውና ለማስከበር የኢትዮጵያን አንድነትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑ ተረድቶ፣ በዚሁ በአፋብን ዓላማ የተስማሙ ወገኖቻችን ሁሉ የትብብሩ አካል መሆናቸው ወንድም አበበ “ይህም ሥርዓት የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት፣ የተለያየ ማንነት ያለው ኢትዮጵያዊ ዜጋን ሁሉ ሰው በመሆኑ ብቻ የሰብዓዊና የዲሞክራሲ መብቶቹ የሚከበሩበትና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ፣ የአገር ሉዓላዊነትንና የሕዝብ አንድነትን የሚያጸናና የሚያረጋግጥ እንዲሆን በሕገ-ሕዝብ ላይ መሰረት ያደረገ ፍትሃዊ ሥርዓት ነው።” ያለውን መደምደሚያ አስተያየት ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ነው። ለዚህም ማጠናከሪያ እንዲሆን፣ የማከብረው ሲሣይ መኮንን ለጋዜጠኛ አንሙት አቀረበ የተባለውን ጥያቄ አስቀድሜ፣ የትብብሩን የምሥረታ መግለጫ ሐረግ አስከትላለሁ።

    መሣይ “አሁንም ቢሆን ስጋቴን አነሳለሁ ይሄ ትግል መስመር ስቶ መረን ወጥቶ ለኢትዮጵያዊነት አደጋ እንዳይሆን ማዕቀፉ አለ ወይ? ይህ አማራው የጀመረው ብሔረተኝነት ወደምንፈራው ወደማትቆጣጠሩት ጽንፍ ወደረገጠ ለኢትዮጵያ አደጋ ሆኖ እንዳይሻገር ከወዲሁ መመካከሩና ቀስ እያሉ ነገሮችን እያዩ መሄድ ጥሩ ነው። “ ብሎ ለአንሙት አቀረበው ተብሏል። የመሣይ ስጋትም ሆነ የአንሙት መልስ ተገቢ አይደሉም። ፋኖ በደል ሲመርረው ጎጠኛ መሆን ቢፈልግ ኖሮ፣ ሶስት የሰቆቃ አመት አይጠብቅም፣ ትብብርንም አይፈልግም። ግን የአማራ ህልውናም ሆነ የሌሎቹ፣ በቡድን አገዛዝ ሊረጋገጥ እንደማይችል አፋብን ተረድቷል። ስለሆነም፣ የፋኖ ዓላማ ጸረ አማራውን ኃይል አስወግዶ፣ የአማራ ሕልውና መከበር ከኢትዮጵያ አንድነት፣ ዲሞክራሲያዊነትና ሰላም ጋር ያለውን ቁርኝት ተገንዝቦ፣ አፋብን ትግሉን በዚህ ግንዛቤ መሠረት እየመራ መሆኑን አንሙት አላስተዋለም።

    የመሣይ “አሁንም ቢሆን ስጋቴን አነሳለሁ ይሄ ትግል መስመር ስቶ መረን ወጥቶ ለኢትዮጵያዊነት አደጋ እንዳይሆን ማዕቀፉ አለ ወይ?” ያለው አደጋ ቢያንስ በሶስት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡ 1ኛ/ የትብብሩ ጉባዔ አፋብን ወይም ሌላ አባል አምባገነን ልሁን ቢል አይፈቅዱም፤ 2ኛ/ የቡድን አገዛዝ እስካለ ድረስ የማንም ሕልውና እንደማይከበር ከ983 ዓ.ም. ጀምሮ አስከፊነቱ ስለታየ ማንም የትብብሩ አባል አምባገነን ልሁን አይልም፣ 3ኛ/ ስለትብብሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰጠውን የምሥረታ መግለጫ ሽሮ፣ አንድ የትብብሩ አባል የቡድን አገዛዝ ላምጣ ቢል የትብብሩ አባላትና የኢትዮጵያ ሕዝብም አይፈቅዱም። እንደዛሬው ጽንፈኛ፣ በቡድን አገዛዝ ሰላምም አይኖርም።

    አንዱ ወሳኝ የመግለጫው ሐረግ የትብብሩን ዓላማ “ለሀገሪቱ ሰላምና ለሕዝቦች ቀጣይ ሕልውና ሲባል ሀቀኛ፣ ታማኝ፣ ሁሉንም ያካተተና ያሳተፈ ሕዝባዊና ሕገ መንግሥታዊ ውይይት (Constitutional Dialogue) በማድረግ ወሳኝ ሕዝባዊና ሀገራዊ ጥያቄዎችን በሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ መመለስ ይሆናል።” ብሎ ገልጾታል። ይኸ ሐረግ፣ ቢያጥርም፣ ላይ ካሰፈርሁት የወንድም አበበ መደምደሚያ ጋር ይዘቱ አይለይም።.የትብብሩ አባላት ሁሉ፣ በወንድም አበበ ድርሰት ላይ እንደተጠቀሰው፣ ተገንጣይ፣ ጸረ አማራ ወይም ጸረ ኢትዮጵያ ሳይሆኑ፣ በዲሞክራሲያዊ ግንባታ የሚያምኑ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማጽናት የተስማሙ፣ በ1967 እና በ1983 በጥቂት ጀሌዎች እንደተደረገው ሳይሆን፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወሰን መሆኑ፣ ሌላ የጓዳ ልክፍት ካልጎተተ በስተቀር ሁላችን ለዘመናት ስንመኘው የኖርነው ጉዳይ ነው። በዚህም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ስለሚሳተፉበት፣ የእስክንድር “ እርባን አማራም ” ይኖርበታል።

    በነገራችን ላይ በሕዝብ ላብና ደም በተገነቡ የድሀ ሕዝብ የትምሕርት ተቋምት ተማርሁ የሚል ዘመነኛ ሊቅ፣ አፋብንን “የአርሶ አደሩ አማራ”፣ የእስክንድሩን “እርባን አማራ “ ብሎ መከፋፈሉ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን የጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ ቅድመ-አድዋ ክፍፍል የባሰ አስቀያሚና አስነዋሪ ነው። የአንድን አገር ልጆች፣ ለሥልጣንና ለቡድን ጥቅም ብሎ፣ በወንድማቸው በአማራ እንደዚህ ሲከፋፈሉ፣ ከፋፋዩ ሁሉ የአማራ አፍቃሪ ያልሆነ፣ ኢትዮጵያንም ከልቡ የማይወድ ርካሽ ደላላ ነው ማለት ይቻላል። እንዲያው ለነገሩ ክፍፍሉንም እንቀበለውና፣ በገጠር የሚኖረው አማራ የከተሜውን አማራ ከ10 እጥፍ በላይ ስለሚሆን፣ ብዙሐኑን የገጠር አማራ የወከለውን “የአርሶ አደሩ አማራ” አሜን ብሎ መቀበሉስ የዲሞክራሲያዊነት ሽታ ማሳየት አይሆንም? ከአውሬው ደርግ ጀምሮ ሁልጊዜ እናውቅልሀለን የሚሉን ሁሉ የደንቆሮነት ልክፍት ያለባቸው ናቸው።

    ካለፉትም 2000 ዓመታት ኋላ ቀር የግብርና መሣሪያ ያላሳቀቀው ባለቪላ፣ ባለመኪናና የፈረንጅ ቅራሪ ገልባጭ በዝባዥ ከተሜ፣ ብዙሀኑ ፋኖ ባላገር የሆነበትን የጀግና ስብስብ እኔ ካልመራሁት ማለት ዘላለም ገጠሬውን አፍኖ ከመግዛት በምን ይለያል ? በዚህ ላይ፣ ዘመነ፣ ጀኔራል ማሞ፣ ምሬ፣ ዝናቡ ልንገረውና ሌሎች የአፋብን ጀግና መሪዎች ሁሉ ጠበቆች፣ የዩኒቬርሲቲ አስተማሪዎች፣ የጦር መሪዎች፣ የት/ቤት አስተማሪዎች የመሥሪያ ቤት ሹሞችና የንግድ ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ የገጠር አማራ በመሆናቸው “የአርሶ አደሩ አማራ” መሪ ሆኑ ከተባለ፣ የአዲስ አበባው ልጅ እስክንድር ሞፈር-ቀንበር-ድግር-ማንጠቢያ ምን እንደሆነ የማያውቀው የ “እርባን አማራ “ መሪ ነኝ ባይ ምን አግብቶትና ምን አውቆ ነው አርሶ አደሩ ባየለለበት አፋብን ውስጥ መሪ የሚሆን ? ፋኖ የአርሶ አደር ንቅናቄ መሆኑም ታወቅም ? ስለ ገጠሩ ጭቆና እያወሩ፣ ገጠሩን ማታለሉና በገጠሩ መነገዱ አይበቃም?

    የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሕዝብና ለአገር ለመቆም ሳይሆን በዋናነት ሆድ ለመሙላት በመሆኑ፣ የእስክንድርን “ምኒልክ ጋዜጣ” ከማንበብ ባለፈ ባለፉተ 52 ዓመታት የምንም የፖለቲካ ስብስብ አባል ሆኘ አላውቅም። ኢትዮጵያን ግን ለምንም ለማንም ነግጀባት አላውቅም። በተለያዩ ሰፊ መድረኮች በተሰማራሁበት ጊዜ ሁሉ የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ስም ሳስጠብቅና ወረቀቶችንም ሰብስቤ፣ በወቅቱ ሰፊ ዕድል ቢኖርም፣ አንድም ቀን ለፈረንጅ አገር ጥቅም አልተሸነፍሁም። ኢትዮጵያም ሹመት ለማግኘት የዘፈንሁበት ወይም ያጨበጭሁበት ወቅት የለም። በአገር ቤት ለየት ያለ ነገር የገጠመኝ ኢትዮጵያን አትንኩ ማለቱ ዋጋ አስክፍሎኛል። ዛሬም በደረጃየ፣ በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ ድርድር የለም። የፋኖም አቋም ተመሳሳይ ይመስለኛል።

    ወንድም አበበ፣ በድርሰትህ ላይ እጅግ የቆረቆረህ ትህነግ የትብብሩ አባል መሆንና ተሳስተህ ወይም አውቀህ የጠቀስኸው፣ የትብብሩም አባል ያልሆነው፣ የኦነግ ጉዳይም ነው። ትህነግ፣ የ83 ጎሣ ኢትዮጵያን ለዘጠኝ ጎሣ አካፍሎ የቀሩትን 74 ጎሣዎች አገር፟አልባ አድርጎ ከፋፍሎ፣ ኤርትራን አስገንጥሎ፣ አማራንም ከሕገ መንግሥቱ ዝግጅትና ከመንግሥቱም አግልሎ በአማራም ላይ ጸረ አማራ ትርክት ነዝቶ ከወገኖቻችን ጋር ሁሉ አናክሶ፣ እኔም እጅግ እጅግ እጅግ እጠላዋለሁ። ኦላ፣ የትብብሩ አባል፣ ትህነግ የነዛውን የውሸት ትርክት ተቀብሎ የራሱን ውሽት አክሎ ከወንድሙ ከአማራ ጋር መቃቃሩንም አውቃለሁ። ነገር ግን፣ የዛሬው ጥያቄ የኢትዮጵያ የሕልውና ጥያቂ በመሆኑ ከግል፣ ግፋ ሲልም ከቡድን፣ ስሜት እጅግ የላቀ ነው። እዚህ ላይ፣ የ1980ዎቹን የደቡብ አፍሪቃ ተሞክሮ ማንሳቱ ይጠቅማል።

    በ1982 ዓ.ም. ማንዴላን ከሥር ቤት አስጠርቶ የአፓርታይዱ መሪ “ በል እንግዴህ አንተም የራስህን ጎሣ አገር ውሰድና እኛም የራሳችንን አገር ይዘን፣ ሰላም እንመሥርት።” ይለዋል። ኔልሰን ማንዴላም፣ እኔማ እስከ ዛሬ የታገልሁት ለተባበረች ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃ ብየ ነው እንጂ የጎሣ አውራጃ ለማግኘት አይደለም ብሎ፣ በዚህስ ከምስማማ ወደ እሥር ቤት መመለሱን እመርጣለሁ ብሎት ወደ ሮቢን ደሴት ተመለሰ። ታዲያ ተተኪው መሪ ደክለርክም፣ ሰላም ለማስፈንና የአገር ውድመት ለማስቆም፣ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች ያሉበትና ሌሎችንም ባለጉዳዮች ጨምረው፣ በድምሩ 26 መሪዎች የሽግግር ጉባዔ መሥርተው ሕግ መንግሥት አርቅቀው፣ የተለያዩ አዋጆችን ቀርጸው፣ ምርጫውን በጋራ መርተው ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃን አዋለዱ። የአፓታይድ መንግሥቱና ብዙዎች ታጋይ ድርጅቶች ከ3000 ዓመት በላይ ተዋግተዋል፣ ተዳምተዋል። ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃን ለመመሥረት ግን ሁሉም አብረው የሽግግር መንግሥት ጉባዔ መሥርተዋል።

    ከ26ቱ የሽግግር ኡባዔ አባላት መካከል፣ ጦረኞች ዙሉዎች ከማንዴላ ጦር ጋር መዋጋት ብቻ ሳይሆን ብዙ ጠላትነት ተመሥርቶ ነበር። ግን፣ የሽግግር መንግሥት ጉባዔው ሲመሠረት፣ ዙሉዎች በአንድ ጉዳይ ስላልተስማሙ በጉባዔው አንሳተፍም ስላሉ፣ ማንዴላ “ዙሉዎች እሺ የሚሉ ከሆነ ተንበርክኬ እለምናቸዋለሁ።” ነበር ያለው። በዙሉዎች አለመሳተፍ፣ ሰላማዊ ምርጫም አይቻልም፣ ደቡብ አፍሪቃም ሰላም አትሆንም። ማንዴላ ተንበርክኮ ሊለምን የፈቀደው ለሰላምና ለአንድነት ብሎ ነው። ወደ ትብብሩ እንመለስ !

    የትብብሩ አባላት በኢትዮጵያ አንድነትና ዲሞክራሲያዊነት ተስማምተዋል። የ1987 ዓ.ም. አንቀጽ 39 የሻገተ ደንጋጌ መሆኑን አምነዋል። በትብብሩ ምሥረታ የገረመኝና ያስደሰተኝ ሁሉም የታጠቁ አባላት በትብብሩ መካተታቸው ነው። ያለፈውን ፋይል፣ እንደ ደቡብ አፍሪቃውያን ዘግተው፣ ለአዲሷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የጋራ ግንባታ መሰለፋቸው፣ ኢትዮጵያን ከዛሬው የጎሣና የመንደር ሥርዓት ለማስቀደማቸው በቂ ምስክር ነው። ይኸ ደግሞ በኃያሏ አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮጳና በብራዚልም ያለ አሠራር ነው። በታሪክ ቁርሾ ላይ ተቸክሎ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንዳትመሠረት ማደናቀፍ፣ የሚጠቅመው ለደላሎች፣ ለሆድ አደሮችና ለውጭ ጠላት ነው።
    ትህነግም ሆነ ኦላ በ1980ዎች እምነታቸው ላይ ተቸክለው አልቀሩም። ሁሉም በኢትዮጵያ አንድነትና በዲሞክራሪያዊ ሥርዓት ግንባታ እንደተስማሙ፣ ፕሮፌሶል ሕዝቅኤል ጋቢሳን፣ አቶ በቀለ ገርባን፣ የሁሉም ወሳኙን ጦረኛውን ጃል መሮን ፣ የአፋሩን መሪ፣ ደብረ ጽዮንን፣ የኦጋዴኑን ነጻ አውጪ ግንባር መሪና ሌሎቹንም ማዳመጡ ይበጃል። አገር አስገንጠለን፣ በጎሣ ተደራጅተን፣ በወታደር እንደ ከብት ተነድተንና በቡድን ሕገ መንግሥት ታግተን የት እንደ ደረስን አይተነዋል። ውጤቱ መተላለቅ፣ ውድመት፣ ረሀብ፣ ስደትና ውድቀት ሆኗል። የሚበጀን፣ ትብብሩም እንደገለጠው፣ ይቺን ባለሰፊ ለም መሬት፣ የተትረፈረፈ የውሀ ሀብትና ሰፊ ማዕድን ሀብት በሚሊዮን ከየሚቆጠር ሠራተኛ ወጣት ጋር ያላትን ከበርቴ አገር በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እየተመራን፣ መሪዎች ዳግም አምባገነን የማይሆኑበትን ፍቱን የቁጥጥር ሥርዓት አደራጅተን፣ በጋራና በእኩልነት አገራችን መርተን፣ ብዝበዛንና አምባገነንነትን አስወግደን፣ አገራችንን አፋጥነን ማበልጸግ ነው።

    በግልጽ እንደሚታየው፣ የእርባን አማራና የአርሶ አደሩ አማራ ክፍፍል ለአማራ በማሰብና በመጨነቅ የመጣ ሳይሆን፣ ለሥልጣንና ለጠባብ ቡድን ጥቅም የተደራጀ ኋላ ቀር አሠራር ነው። ይህንንም በደርግ፣ በኢሐፓ፣ በመኢሶን፣ በወያኔ ክፍፍልና ዛሬም ደጋግመን አይተነዋል። አውሬ እንኳን የማያደርገውን የእኛ ምሁር ነን ባይ ልሂቃን የራሳቸውን አገርና ሕዝብ ሲከፋፍሉ፣ ሲያጋድሉ፣ ሲያራቁቱ፣ ሲገድሉ፣ ሲያፈናቅሉ፣ ወጣቱን ሲያሳድዱና አገር ሲያስርቡ፣ የራሳቸው ቀፈት እስከሞላ ድረስ ምንም ቅር የማይላቸው መሆኑና ለዛሬይቱ ኢትዮጵያም ውድመትና ውድቀት ዋና ተጠያቂ መሆናቸውን አለመረዳታቸውም ስብአዊ ተፈጥሯቸውን ወደ መጠራጠር ይመራናል። በዚህ አሳዛኝ ከባቢ ላይ እያለን፣ የትብብር ለሕልውና አባላት እንደ ሰው አስበውና አመዛዝነው፣ እርስ በርስ መዋጋቱን አቁመው፣ የአድዋ አባቶቻችን እንዳደረጉት፣ ለኢትዮጵያ ትንሣዔ በጋራ እንቆማለን ማለታቸው ታሪካዊ ነው። ድርሻችን ትናንሽ ክፍተት ማስፋት ሳይሆን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ምሥረታ ከልብ ማገዝ ነው።

  4. ወንድም ተስፋ፦

    በኢትዮጵያዊነትህ ላይ የማይናወጥ ጥንካሬህንና ለአገር እንደምትቆረቆርም ተረድቻለሁ። እኔም የአማራው አርሶ-አደር ልጅ፣ ዛሬም ከገጠር ዘመድ አዝማድ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ስላለኝ፣ በደጋውና በቆላውም የምወለድ በመሆኔ፣ ቢያንስ የአንዱን ብርቱ ክፍለ ሀገር ሁኔታ ከገጠር ዘመድ አዝማድና ወዳጅ ስለምሰማና ስለማውቅ፣ እኔም እንዳንተ ይኸ ለ2000 ዓመት ከሞፈር-ቀንበር-ድግር-መርገጫ-ማንጠቢያ ያልተገላገለውንና የተማርነው ወገኖቹ የረሳነውን ወገኔን የዘመናት የችጋር ኑሮ የምከታተል በመሆኔ፣ በዘመናዊ ትምሕርትም ረገድ፣ ምናልባት ተማሩ ከተባሉ ሁሉ የማያንስ አቅምም ስላለኝ፣ በጥናትም ሆነ በዘመድ አዝማድ ዘገባ አጣርቼ ያወቅሁትን ባካፍልህ ምናልባት በተከታታይ ያየሁትን የማይለወጥ ግንዛቤህን አዳብሮ ቁጭትህንም እንዲቀንስ በማለት ይህን አስተያየት አቅርቤያለሁ።

    አንተም እንዳመንኸው፣ “ … በዚህ አማችና አሻሚ ወሬ በሚናፈስበት የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን እውነትን ፈልጎ ማግኘት እየከበደ መቷል።” ስለሆነም፣ በመገናኛ ብዙሀን የሚቀርበው ሁሉ አይታመንም። “አማራ ጠባብ ብሄርተኛ ሆኖ ኢትዮጵያዊ መሆን አይችልም።” ያልኸውም ትክክል ነው። ነገር ግን፣ አማራ ጠባብ ብሔርተኛም ሆኖ አያውቅም። ስለሆነም የአማራን ኢትዮጵያዊነት፣ የቀበሌ መታወቂያ አዘጋጅ ፀሐፊዎች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የጠቅላይ እስታቲስቲክስ ሕዝብ ቆጠራ ሹሞችና ራሱ የዘረኛነት አባቱ ወያኔም፣ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ደምና ላብ የተማረውም የአዲስ አበባ ዩኒቪርሲቲው ዲን የነበረው ዶ/ር ሶሎሞን እንቋይ ዓይነቱ፣ ከመቀሌ በሬዲዮ “ አማራ ሊያታልለን ኢትዮጵያዊነቱን ያጠብቃል፣ ሊገዛን ነው አትመኑት!” እያለ ያቅራራ ነበር። አማራ ከኢትዮጵያዊነት ተለይቶ ታይቶ አያውቅም። ፋኖም በዘር አማራ በዜግነት ኢትዮጵያዊ መሆኑን ማንም አይስተውም።

    ነገር ግን፣
    “…. ፋኖ መንገድ እየዘጋ፤ የመማሪያ ት/ቤቶች ላይ እየሰፈረ፤ ህዝብ እያስፈራራና እየገደለ የአማራ ህዝብ መከራ ውስጥ በመክተቱ …..” ያልኸውና
    “…. በደመ ነፍስ ለሚንገዳገድ ቀምቶ አዳሪ ስብስብ ሰክኖ ነገሮችን የመመልከቻ ጊዜ የለውም።” ያልኸው፣ እንዲሁም
    “…..አማራ ራሱን መብላት የጀመረው ብሄሩን ታኮ ትጥቅ ካነሳ በህዋላ ነው።”

    ያልኸውም ውሸት ናቸው። ከደጋም ሆነ ከቆላ ዘመዶቼ የምሰማው ጸረ ሕዝቡ ፋኖ ሳይሆን፣ በፋኖ ስም በአማራ ብልፅግና የተደራጀ፣ ፋኖን ለማስጠላት የሚሠራ፣ ብአዴን የፈጠረው ጸረ ሕዝብና ጸረ አማራ ድርጅት ነው።

    ፕ/ሮ አሥራት ወልደየስ፣ የመአሕድ ሊቀ መንበር የነበሩት በተለይ የአማራ ድርጅት መሪነቱን አልቀበልም ብለው፣ የአሰቦትን፣ የአርባ ጉጉንና የሌሎችንም አካባቢዎች አማራ እየተለየ እንደ አውሬ መታደን ሲያስረዷቸው፣ በስንት ሽማግሌና መነኩሴ እማላጅ ሥራውን ተቀበሉ። ፕሮፌሶሩ የሐርረርጌ ተወላጅ በመሆናቸው፣ ያደጉትና ወዳጆቻቸውም አደሬዎች፣ ቆቱዎችና ኢሳዎች ጭምር ስለነበሩ የአማራ ድርጅት መሪ መሆናቸውን የተቀበሉት አማራን እንደ አውሬ መታደን ማስቆሚያ ሌላ ዘዴ በመጥፋቱ ነበር። ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጎሣ ተደራጅተው፣ በአማራውም ላይ እንዲዘምቱ በመንግሥት እየተገፉ በነበረበት ዘመን፣ አማራም ራሱን ለመከላከልና ሕልውናውን ለማስከበር በዘሩ መደራጀት መገደዱን መካድ አይቻልም። ሌላ መከላከያ አጥቶ፣ አማራ በዘር ተደራጅቶም፣ ኢትዮጵያ አገሩን የረሳበት ወቅት የለም። ስለሆነም፣

    “….ፋኖ የአማራን ህዝብ ከከፍታ ማማ ላይ ያወረደ ያልነበረውን የጠባብ ብሄርተኝነት እሳቤ በህዝብ ላይ የጫነ ክፉ ስብስብ ነው።”

    ያልኸው ክስ ከእውነታ የራቀ ነው። አንተ እንደምትለው፣ ፋኖ ጸረ አማራ ቢሆን ኖሮ፣

    (1) በጥቂት ፋኖዎች ጀምሮ፣ ዛሬ ካለበት አያሌ እዞች አይደርስም ነበር፣
    (2) ጦሩ በፋኖ ዓላማ ባያምን፣ ዛሬ ያለው ትጥቅ አይኖረውም፣ በየጊዜው የምንሰማውም ድልና ምርኮ አይኖርም፣
    (3) አዝማሪዎች፣ አርቲስቶች፣ የኢትዮጵያም ህዝብ ስለ ፋኖ ያለው ግንዛቤ እንደ ዛሬው ያማረ አይሆንም፣
    (4) የዛሬው ትብብር ለሕልውናም አይኖርም ነበር፣
    (5) ወንድም ዘመነ ካሤም የትብብሩ ሰብሳቢ ሆኖ አይመረጥም ነበር።

    ፋኖ፣ እንዳልኸው፣ ክፉ ስብስብ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ በትብብሩ ውስጥ ወደው ፈቅደው የተሰለፉት 7 የታጠቁ ኃይሎች ለምን ከፋኖ ጋር ይተባበራሉ? የፋኖን ሊቀ መንበርስ ለምን ሊቀ መንበር አድርገው ይመርጣሉ ? ቀድሞ የማይገናኙ፣ የማይነጋገሩና በውሽት ትርክት የተቀያየሙ ዘሮች ታጋዮች፣ በገዛ ፈቃዳቸው ትብብር መፍጠራቸውና ኢትዮጵያን በጋራ ሊታደጉ መወሰናቸው የተሳካው አማራም በዘር ተደራጅቶ፣ የወገን ምርኮኛ ገዳይና አራጅ አለመሆኑን አሳይቶ፣ ዓላማው አውሬነት ሳይሆን እኩልነት መሆኑን አሳምኖ፣ አንድ ላይ ሆኖ ኢትዮጵያን በጋራና በእኩልነት እንታደግ በማለቱ መሆኑን አልተረዳህም ?

    በዘመናት ኢትዮጵያዊነቱ ላይ ብቻ ተቸክሎ፣ አማራ የተለያዩ ጎሣ ተቋማትን አብረን እንደራጅ ቢል፣ የሚቀበሉት ይመስልሀል? አማራም በጎሣ መደራጀት ብቻ ሳይሆን ለማረካቸው የተለየዩ ዘር ወንድሞቹ ያሳየው ወንድማዊነትና ሰብአዊነት ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር ተጣምረው፣ ፈረንጅች Birds of the same feather flock together እንደሚሉት፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተማምነው እኩልነትንና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የዛሬውን ታሪካዊ እውነተኛ የሰው ልጆች ትብብር አዋልደዋል።

    ሌላው ያንተ ቅሪታ አፋብን ለምን ከወያኔና ከኦላ ጋር ተባብሮ ትብብርን ለሕልውና አደራጀ የሚል ይመስላል። ለዚህ እንዲረዳህ፣ የደቡብ አፍሪቃን ዙሉዎችና የኤኤንሲ ጦር ለዘመናት የነበራቸውን ጥላቻና የዘመናት መጋደል ወደ ጎን አድርገው፣ ከማንዴላ ጋር የዛሬው ፕሬዚደንት ዋና ፀሐፊ የነበሩበትን ጉባዔ ፈጥረው፣ የዛሬዋን ከበርቴና ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃ አዋለዱ። የተጣሉትም ዘሮች በመተባበራቸውና ደቡብ አፍሪቃን በማስቀደማቸው አጠፉ ?

    እኛስ፣ ያለፈውን የቅጥፈት ትርክት ወደ ጎን አድርገን፣ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ፣ በኢትዮጵያዊነታቸውና በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ በጋራ መግለጫቸው ካመኑት ከወያኔና ኦላ ጋርም ትብብር መፍጠሩ ምኑ ነው ተገቢ ያልሆነው? ኢትዮጵያዊነትንና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በጋራ እንገንባ ማለታቸውና ኢትዮጵያን ማስቀደማቸው ለምን አስቀየመህ? ወያኔና ኦላ ከትብብሩ አይግቡ ካልህ፣ እነዚህን ወገኖቻችንን ያልጨመረ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ መንግሥትና ሰላም ሊኖሩ ይችላሉ? ከትብብሩ ይውጡ ካልህ፣ የወያኔ/ኢሐዴግን የ1983 የቡድን አገዛዝ ሥርዓት መመለስ ነው እንጂ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ምሥረታ ሊሆን አይችልም። በአማራነት ላይ ኢትዮጵያንም የምታስቀድም ከሆነ፣ አስብበት !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News