

በአዲስአለም ቀለመወርቅ
ነብር፣ ጅብና ቀበሮና ተኩላ በአንድ ላይ ለአደን ይወጣሉ። ቀኑን ሙሉ ሲለፉ ውለው አንድ የሜዳ አህያ ይጥላሉ። ከዚያም በሉ ስለራበን መብላት እንጀምር አለ አያ ጅቦ። ነብርም እንዴ የያዝናት አህያ አንድ ናት ለሁላችን ተካፍለን ምን ትጠቅመናለች ባይሆን በሆነ መላ ለአንዳችን እንድትሆን ብናደርግ አለ የከፋ ነገር ቢመጣ እንኳ ሮጬ ዛፍ ላይ እወጣለሁ ብሎ አስቦ። ጅብና ተኩላ ግራ ተጋብተው በመተያየት ይቺ ነገር ብቻዬን ልብላት እንዳትሆን ብለው ሰግተው እንዴት አሉ። ቀበሮ ፈጠን ብላ እጣ እንጣል አለች። ነብሩ በቁጣ የለም ከሁላችን በእድሜ የሚበልጥ ይውሰድ ነገር ግን ማንም ከመቶ በላይ ቁጥር መጥራት አይችልም አለ። ጅብም ከሁሉ እኔ ነኝ ታላቅ 90 አመቴ ነው አለ። ነብርም እኔ መቶ አመቴ ነው እኔ ነኝ ከሁሉ ታላቅ አለ። በዚህ ጊዜ ጅብና ተኩላ ተቆጡና በመካከላቸው ከባድ ክርክር ተነሳ። ቀበሮ የሆነውን ዝም ብላ ተከታተለችና ማውጣት ማውረድ ጀመረች።
ክርክሩ በዚህ ከቀጠለ እንኳን ስጋ ልናገኝ እኛም አንተርፍም ብላ እንዲህ ስትል አሰበች ቢያንስ ለነብር አግዤ ጥቂት ቅንጥብጣቢ ባገኝ ይሻላል ብላ ጣልቃ ገባች። እኛ ምንም እድሜያችን ቢበዛ ነብርን አያክልም እንደውም ነብር መቶ አመት እንደሞላው እኔ ህያው ምስክር ነኝ እሱ ሲወለድ አራስ ቤት ለመጠየቅ ዳቦ ተሸክሜ ሄጃለሁ አለችና አያ ጅቦና ተኩላን ተስፋ አስቆርጣ ሸኘች። አያ ነብሮም ወገኖችሽን የከዳሽ ለኔ ምን ልትጠቅሚኝ ብሎ አባረራት ይባላል።
አምስት አመት ሙሉ ሲከራከር የከረመው የምክክር ኮምሽን የ150 አመት ላይ የቆመ ተረትን ለመንገር ብቻ መሆኑን ስንሰማ ይሄ ሁሉ ግርግር የነብሩን ጥያቄ ለመመለስ ብቻ ነው? ብለን መታዘባችን አልቀረም። ያ ሁሉ ፕሮፈሰርነትና ዶክተርነት ያ ሁሉ አምባሳደርነትና ጉምቱ የስራ ልምድ፣ የንግግር ጋጋታና የጥናት መአት ከ150 በላይ ቁጥር መጥራት አይቻልም የሚለውን የኦነግ ድንበር ማለፍ ያልቻለ የቀበሮዋ ቅንጥብጣቢ ባገኝ ዘፈን መሆኑ ማመን የማንፈልገው እውነት ነው። የሰላም ኮሚሽን ተብሎ ተቋቁሞ ጸረ ሰላም፣ የምክክር ኮሚሽን ተብሎ የፉክክር፣ በታሪክ ላይ መግባባት ያመጣል የተባለ ስብስብ ጭራሽ አዲስ የክርክር ያለመግባባት ታሪክ ባለቤት ሆነና አረፈው። የምክክር ኮሚሽኑ ያስገኘልን አንድ ትሩፋት ቢኖር ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ያለመግባባትና ችግር የሚፈጥር ኮሚቴ መርጠው ነበር የሚል ታሪክ ነው።
የሰው ልጅ በዚህ ምድር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የተለያየ ምርጫ፣ የተለያየ ባህል፣ አኗኗር ዘይቤ፣ቋንቋ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በአለም ላይ አሁን ያለው አይነት የተለያየ ታሪክና ማንነት ሊኖረው ችሏል። ይህ የተለያየ ምርጫና ፍላጎት የተለያየ ስልጣኔ እንዲኖረው አስችሎታል። በተጨማሪም የሰውልጅ በተፈጥሮው ተንቀሳቃሽ ፍጡር በመሆኑ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ አካባቢ በመንቀሳቀስ በአካባቢው የሌለውን አዲስ ነገር የመማር የመገብየትና የመጠቀም ባህሪውም ከተፈጥሮአዊ ማንነቱ የተቀዳ ነው። ሃገራችን ኢትዮጵያም የዚሁ የሰው ልጅ አለም አካል በመሆኗ የሰው ልጆችን ተፈጥሯዊ ስሪት ትጋራለች።
ይህ ደግሞ በሃገራችን የተለያየ ስልጣኔ፣ ማህበራዊ ስሪትና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲኖረን አድርጓል። በዚህ ረገድ ሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ለባህር በር የቀረበ በመሆኑ ከሌላው አለም ጋር ትስስር መፍጠር ችሎ ነበር። ይህ ደግሞ በአለም ላይ ያሉ ልዩ ዩ ሰልጣኔዎችን ለማየት ስላስቻለው ያንን መሰረት አድርጎ የራሱን የጥበብ ስራዎች እንዲሰራ አስችሎታል። በቀድሞ ዘመን ታላላቅ እሳቤዎችና ስልጣኔዎች ተብለው የሚታወቁት ንግድ፣ የግብርና ስራ፣ የአልባሳት ስራ፣ የጦር መሳሪያዎች የማእድን ማውጣትና ልዩ ልዩ ጌጣጌጥ ስራዎች፣ ፊደልና ጽሁፍ፣ ሙዚቃና የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ የእርሻ መሳሪያዎች የየብስና የባህር የንግድ መጓጓዣ ስራዎች፣ ከተሞች፣ ቤተመንግስቶች፣ አብያተ ክርስቲያናት እና የመሳሰሉት የስልጣኔ ስራዎች የትልልቅ መንግስታት የሃያላንነት መገለጫ ከመሆን ባሻገር የማህበረሰባዊ ጥበብ እውቀትና የስራ ማሳያዎች ነበሩ። እነዚህ በአለም ላይ አሉ የተባሉ የጥበብ ውጤቶችን የሰሜን ማህበረሰብ በመስራቱ ዛሬም ድረስ በአስደናቂነት መዝገብ ላይ የሰፈሩ በመሆኑ ከተለያየ የአለም ክፍል ጎብኚዎች የሚጎርፉበት ህያው ምስክር ነው።
የተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ መልክአምድር፣ አመጋገብ አልባበስ አኗኗር ዘይቤ የነበረው ነው። ከፊሉ ከብት በማርባት፣ ከፊሉ እርሻ በማረስ ከፊሉ ጥብቅ ደን ውስጥ መኖር፣ከፊሉ ደግሞ ወቅትን እየጠበቁና የዝናብ ሁኔታ እየተከታተሉ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የበረሃ እንስሳትን እያረቡ መኖር የአብዛኛው የሃገራችን ክፍል አኗኗር ዘይቤ ሲሆን የሰሜንና መእከላዊ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ደግሞ ከተማ ገንብቶ፣ ስርአተ መንግስት መስርቶ፣ ስርአተ ትምህርት ቀይሶ፣ ፊደል ቀርጾ ታሪኩን መጻፍ ችሏል። በተጻራሪው ሌላው የሃገራችን ክፍል ከነዚህ ስልጣኔዎች አንጻር አርኪዮሎጂያዊም ሆነ ታሪካዊ ማስረጃዎች ውስን ናቸው። ይህ ደግሞ የተለያየ የታሪክ ሚዛንና ማስረጃ እንዲኖረው አድርጎታል። አንደኛው አካል የተጻፈ ታሪክና ማስረጃ ሲኖረው ሌለኛው የለውምና የተጻፈውን አልቀበልም ወይም ውሸት ነው ማለት ጨቅላነት ነው። ሁለት ሰዎች ልጆቻቸውን የተለያየ ነገር አስተማሩ አንዱ ሃኪም ሆነ አንዱ ዘበኛ ሆነ። ዘበኛ የሆነው ሃኪሙን እኔ ማከም ስለማልችል አንተ ሃኪም ልትሆን አትችልም ማለት ከድንቁርናና ምቀኝነት ያለፈ ምን ስያሜ ሊሰጠው እንደሚቻል ሌላ ምርምር የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም።
የብሄራዊ የምክክር ኮሚሽንም ይህን ህጻን ሊረዳው የሚችልን ሃቅ መረዳት አንሶት ማየት አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ የቱንም ያህል ተምሮ አውቆ ማገናዘብ ሊያንሰው እንደሚችል ያረጋግጣል። የሀገራችን የተጻፉ ታሪኮች እኛን አይወክሉምና የደብተራ ተረት ነው አንቀበልም ማለቱ አስተዛዛቢ ነው። አንዱ ታሪክ ጽፎ ፊደል ቀርጾ አስተዳደር መስርቶ ከተማ ሰርቶ የኖረበትን ታሪክ በእኩልነት ሰበብ መካድ ከምሁርነት ተጻራሪ አካሄድ ነው። የሃገሪቱ ርእሰ መዲና አዲስ አበባም ብትሆን በበርካታ ማእከላዊ ዘመን ታሪኮች በታሪክ ማስረጃ የተደገፉ ማንነት እያላት ከ150 አመት በታችም በላይም ያለ ታሪክን መጥራት አይቻልም የሚል ማስረጃ ቢስ ተረት ይዞ ለአንድ ወገን ለመወሰን መጋጋጥ በምሁርነት ስም የተሸፈነ ጥላቻና ለትውልድ አሳፋሪ የራስ ታሪክ ከማስቀመጥ ያለፈ ፋይዳ የለውም። በዚህ ረገድ ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ያልነበረበት ዘመን እንዲሁም በሌለ ማስረጃ አምስት አመት ሙሉ ከቀድሞ ታሪክ ጋር እራሱን ሲያላትም የቆየ የፉክክርና የቅሌት ስብስብ መሆኑን በራሱ ፊርማ ያረጋገጠ ጉባኤ ከለባት ወጉባኤ ደናቁርት ነው።
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena





