spot_img
Saturday, April 13, 2024
Homeአበይት ዜናግልጽ ደብዳቤ ለኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የተከበሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢትዮጵያ...

ግልጽ ደብዳቤ ለኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የተከበሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ – ኢትዮጵያ የጋራ አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ እንዳይኖራት የሚያደርገው ፖሊሲ አደገኛነት

Ethiopia News _ language policy

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ምሁራንና ባለሙያዎች የተሰጠ አስቸኳይ መግለጫና ብሔራዊ ጥሪ

ጥር 12፣ 2015 ዓ.ም

የተከበሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር
አዲስ አበባ፣

አሁን አገራችን ኢትዮጵያ እየተስተዳደረችበት ያለችበት ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 5፣ ቁጥር 2፣ ስለአገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ሲደነግግ፣ “አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል” ይላል። እንደዚሁም መንግሥት እንደአውሮጳ አቈጣጠር (እአአ) በ1994 ያወጣዉና፣ በትምህርት ሚኒስቴሩም ድረ-ገጽ ላይ አሁን ድረስ ሰፍሮ ያለው፣ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ቁጥር 3.5.4፣ አማርኛ ቋንቋ ለአገራዊ ተግባቦት በትምህርት ቤቶች እንደ አንድትምህርት መሰጠት እንዳለበት ይደነግጋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ ይኸው የትምህርት ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ በብዙ ባለሙያዎች ያስጠናው ጥናት፣ ለአገራዊ መግባቢያነት አማርኛ በአጠቃላይ በአገሪቱ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ ትምህርት ተጠናክሮ መሰጠት እንዳለበት በጥኑ አሳስቧል።

ይሁንና፣ በዚህ ወቅት ለብዙ ኢትዮጵያውያን ግልጽ ያልሆነ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ እየተካሄደ ስላለ፣ ከዚህ በታች የተጠቀሱት ሁለት ድርጅቶች ባንድነት ባዘጋጁት ጥናት ውጤትና ማሳሰቢያ ላይ ተመሥርተን፣ የድርጅቶቹ አባላት፣ ለአገራችን የዘለቄታ ህልውናና ጥቅም፣ ለሕዝባችንም አንድነትና ዕድገት ስንል፣ የአገራችንና የሕዝባችን ሁናቴና የወደፊት ዕጣፈንታ ይመለከተናል፣ ያገባናል፣ ያሳስበናልም የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲያውቀው መግለጫ በይፋ አዉጥተናል ፣ ዜጎችም በጉዳዩም ላይ ጉልህና ጠንካራ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ፣ ትምህርት ሚኒስቴርም ከህዝብ ደብቆት የነበረዉንና ከመስከረም 2015 ዓ.ም  ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገውን የትምህርት ፖሊሲ/ ስርዓተትምህርት ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ እንዲያደርግ ጥሪ አድርገናል። ይህንም ተከትሎ ትምህርት ሚኒስቴር በጀኗሪ 14፣ 2023፣ “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ (ረቂቅ)” የሚል ሰነድ  በድረገጹ አዉጥቷል።

ይህ ረቂቅ ሰነድ የነበረንን ስጋትና የፖሊሲዉን አደገኝነት የበለጠ የሚያረጋግጥ ሆኖ አግኝተነዋል።  ሁላችንም እንደምናውቀው፣ እአአ በሐምሌ 2-6፣ 1991 ዓ/ም በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት)ና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ቊጥጥር ሥር የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት የሰላምና የዲሞክራሲ ኮንፈረንስ [ጉባኤ]  በመባል በሚታወቀው ስብሰባቸው የተወሰነው የፖለቲካ ውሳኔ፣ ዜግነትን ሠርዞ ሕዝቡን ክልል በተባለ የጐሣ ሥርዐት በማደራጀት የአገሪቱን አንድነት አዳክሟል፣ ሕዝቡን ከፋፍሏል። በዚያም ጉባኤ ላይ የተወሰነውን የፖለቲካ ወሳኔ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ብለው በማውጣት የትምህርቱ ጥራት እንዲወድቅ ተደርጓል።  ከሁለቱ ፓለቲካ ድርጅቶች ተከታታይ ውድቀት በኋላ፣ አሁን ሥልጣኑን እየተቈጣጠሩ ያሉት አመራሮች፣ ከነሱም ሆነ ከሌላው ታሪክ ሊማሩ የቻሉ አይመስሉም። ስለዚህም በሐሰት ትርክትና ጥላቻ፣ እንዲሁም አሻጥርና መጠላለፍ በተመላበት በከንቱ ጊዜያዊ ጥቅም በመመራት፣ እላይ ከጠቀስነው ሕገ መንግሥትም ሆነ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ባካሄደው ጥናት ላይ ተመሥርቶ እንዲተገበር ካማጠነው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ፍጹም ባፈነገጠና ተቃራኒ በሆነ መልኩ፣ አማርኛ ለአገራዊ መግባቢያነት እንደአንድ ትምህርት መሰጠት እንዳለበት የማይጠቅስ፣ ረቂቅ ፖሊሲ ተነድፎ ገና ሳይጸድቅና ህዝብ ሳያዉቀው፣  ከመስከረም 2015 ዓ/ም ጀምሮ በአገራችን በሥውር ተግባራዊ ተደርጓል። ይኸንንም በኅቡእ ያወጣውን ረቂቅ መምርያ፣ በሕግ ሽፋን ለማጽናት ሲል፣ መንግሥት አጠቃላይ የትምህርት አዋጅ (ረቂቅ) የሚል ሰነድ፣ በድብቅ እያዘጋጀ እንደሆነ ግልጽ ሆኗል። 

ይኸ በድብቅ ወጥቶ ከመስከረም 2015 ዓ/ም ጀምሮ በሥራ የዋለው ረቂቅ መምርያ፣ ከዚህ በላይ እንዳልነው፣ ሕገመንግሥቱንና የትምህርት ሚኒስቴሩን የትምህርት ፍኖተ ካርታም ሆነ፣ በባለሙያዎች  የተሰጠውን ምክር በመቃረን፣ ኢትዮጵያን እንደድርና ማግ ያስተሳሰራትንና ለዘመናት በየጊዜው ከየብሔረሰቡ ተወልደው ሥልጣን የያዙ ነገሥታት የተጠቀሙትን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ብሔራዊ መግባቢያና የሥነጽሑፍ ልሳን አድርገው ያቈዩትን፣ ለድፍኑ ጥቁር ሕዝብ ደግሞ ኩራት የሆነዉን፣ የአማርኛ ቋንቋ እንደአንድ ትምህርት እንዳይሰጥ የሚያበረታታ ነው።  

ይህንን እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ አስመልክቶ፣ People to People (P2P) Inc. ና Global Ethiopian Scholars Initiative (GESI)] በተሰኙት ሁለት ድርጅቶች በጋራ የተዘጋጀ፣ በውጭና በአገር ዉስጥ የሚኖሩ ምሁራንን ያሳተፈ የባለሙያዎች ውይይት ታኅሣሥ 1 ቀን 2015 ዓ/ም ተካሂዷል። (ዉይይት ክፍል 1፣ ዉይይት ክፍል 2) 

ውይይቱ፣ አማርኛ ቋንቋ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የተቀመረና ከየማኅበረሰቡ አስተዋፅዖ የተውጣጣ ልሳን በመሆን፣ በዘመናት ዐድጎና በልፅጎ የኢትዮጵያውያን የጋራ አገራዊ መግባቢያ ከመሆኑ ባሻገር፣ በዓለምም የታወቀ፣ ለትምህርትና ለሥነ ጽሑፍ የበቃ፣ አፍሪቃውያን የሚኮሩበትና ወደፊትም በስፋት ሊገለገሉበት ብቃት ያለው  ቋንቋ እንደሆነ የተለያዩ ተጨባጭና የማያፋልሙ ማስረጃዎችን በማስረገጥ አሳይቷል። አሁንም አማርኛ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ከመሆኑም በላይ፣ በአገራችን በአፍ መፍቻ ወይንም እንደ ሁለተኛ ቋንቋ በመነገር ተቀዳሚው ቋንቋ እንደሆነም አስገንዝቧል።  ይህ ነባር ሐቅ መሆኑ እየታወቀ፣  ትምህርት ሚኒስቴር ከመስከረም 2015 ዓ/ም ጀምሮ ተግባር ላይ ያዋለው ፖሊሲ በሐሰት ትርክትና ጥላቻ ላይ የተመሠረተ፣ አደገኛና የሕዝብን አንድነት የሚሸረሽር፣ የዘውግ ፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን በውይይቱ መድረክ ላይ ምሁራኑ በጥናት ላይ በተመረኰዘ ዘገባቸው አስረድተዋል። 

ከሁሉም በላይ፣ በአፍሪቃ ብቸኛ የሆነውን አገራዊ የጽሑፍ ቋንቋ እንደብሔራዊ ትምህርት እንዳይሰጥ የማድረግ ተግባር፣ ዓላማው ለሺህ ዓመታት በነጻነት የኖረችዋንና አኩሪ ታሪክ ያላትን አገራችንን የመናድ፣ ዜጎቿም ርስበርሰ እንዳይግባቡ፣ የገዛ አገራቸውን የጋራ ብሔራዊ ልሳን የማሳጣት፣ እንዲሁም የሕዝባችንን አንድነት የሚያናጋ፣ የአገሪቷ ህልውናና ታሪክ መሠረት የሚሸረሽር አደገኛ ፖሊሲና አካሄድ መሆኑ በስብሰባው በአፅንኦት ተገልጿል። 

ከዚህም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ዋና ሀብቷ ወጣት ዜጎቿ እንደመሆናቸው መጠን፣ እነሱም የሚገነቡትና አገራዊ ማንነት የሚኖራቸው ጥራት ባለው ትምህርት ታንጸውና ተቀራርበው ሲያድጉ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያም አሁን ላለችበት ቀውስና አስቸጋሪ የሰላም ዕጦት ምክንያት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የአገሪቱ የዘውግ ፖለቲካ ስርዓት ነፀብራቅ የሆነውና ጥራቱ የወደቀው የትምህርት ሥርዐት መሆኑንም ምሁራኑ አስታውሰዋል። በይበልጥም፣ የትምህርቱ ጥራትና ፋይዳ ተሻሽሎ፣ አገሪቱን ከገባችበት ችግርና ማጥ ለማውጣትና ለአገር መግባባት፣ ምክክርና አንድነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ ሲጠበቅ፣ አሁንም መንግሥት ትምህርትን ዜጎችን በቋንቋና በብሔር ለመከፋፈል በመጠቀም አደገኛ ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑ በተሰብሳቢዎቹ አንደበት ተነግሯል።  

ትምህርት ሚኒስቴር ከብዙ የብዙሃን መገናኛ ዉትወታ በኋላ ደብቆት የነበረዉን ረቂቅ ፖሊሲ  “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ (ረቂቅ)” ጀኗሪ 14፣ 2023 ለህዝብ ግልጽ አድርጓል። በዚህ ረቂቅ ፖሊሲም፣ የአገሪቱ የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ የሆነውንና ለአገራው መግባቢያነት በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች እንደአንድ የትምህርት አይነት መሰጠት ያለበትን የአማርኛ ጉዳይን በሚከተለው መንገድ ሳይገልጽ አልፎታል።

“አንድ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ከፌደራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል የተማሪው/የወላጅን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ በየደረጃው ባለው የትምህርት መዋቅር ተወስኖ ከ3ኛ እስከ 10ኛ ክፍል የሚሰጥ ይሆናል።”

እዚህ ላይ በግልጽ መታወቅ ያለበት፣ እስከዚህ ጊዜ ድረስ፣ በህገመንግስቱ በአንቀጽ 5፣ ቁጥር 2 አንድ ብቻ የፌደራል የስራ ቋንቋ ያለ መሆኑንና እሱም አማርኛ መሆኑ ነው።  ይህንም ያልጸደቀና ከትምህርት ፍኖተካርታው ምክረሃሳብና ከአገሪቱ ህግ ጋር ተጻራሪ የሆነ ረቂቅ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ፣ ከመስከረም 2015 ጀምሮ ተግባር ላይ መዋሉ የለየለት ተራ የዘዉግ ፖለቲካ ዉሳኔ ሆኖ አግኝተነዋል።  ይህንም መሰረት አድርጎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ የብዝሃ-ቋንቋ ብሎ ያስተዋወቀው ፖሊሲ፣ ጉዳዩ በድብቅ ዉስጥ ለዉስጥ ሲሰራበት እንደነበረ ማሳያና ለሌሎች ክልሎችም ለህገወጥነትና አማርኛን እንደ አንድ የትምህርት አይነት ላለመስጠት በር የሚከፍትና ኢትዮጵያዊያንን አንድ የጋራ አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ እንዳይኖረን የሚያደርግ ተግባር ነው።   

የምሁራኑ ውይይት፣ አማርኛ ከአገሪቱ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ቋንቋ በመዛነቅ፣ ከልጆቿ አብራክ ወጥቶ፣ በኢትዮጵያ ጸንቶ የኖረ፣ በረጅም ጊዜ የዳበረ የመነጋገርያና የጽሕፈት ቋንቋ እንደሆነ አስገንዝቧል። ስለዚህም፣ ቋንቋው ከምጣኔ ሀብቷና ማኅበራዊ ጥቅሙ ዐልፎ፣ አገራችንን በአንድነትና በነጻነት በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ቦታ እንዳለው፣ በዚህ ብሔራዊ ሚና አንጻር ሲታይ፣ በትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዳይሰጥ የወጣውና ተግባራዊ የተደረገው ረቂቅ ፖሊሲ የሚያመጣው ጉዳት መጠነ-ሰፊና ለመጪው ትውልድ የተወሳሰበ ችግርን የሚያወርስ ነው። የዳበረውን አገራዊ ቋንቋ ከትምህርት መምሪያ መሰረዝ፣ አገርን ይጐዳል፤ ሕዝባችንን ከማቀራረብ ይልቅ ያራርቃል፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ዜጎች እፈለጉበትና እተመቻቸው አካባቢና ሙያ ተሰማርተውና ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብታቸውን ይነፍጋል፤ እንዲሁም አገር ከመገንባት ይበልጥ ወደ አገር መናድና መበታተን ያመዝናል። እንዲሁም ኢትዮጵያዊያንን፣ የራሳቸውን ቋንቋ በመጣል፣ በቅኝ እንደተገዙት አገራት፣ እንግሊዘኛን ለአገራዊ መግባቢያነት እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ አዝማሚያ ነው።

ከዚህም የተነሣ፣ በምሁራኑ ዕይታ፣ የአገራችንና የመላው አፍሪካ ኩራት የሆነዉን የጽሑፍ ቋንቋችንን አዳብረን፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቋንቋ ማድረግ ሲገባ፣ ለቀመር [ኮምፑዩተር] ቴክኖሎጂ ተመራጭ የሆነዉንና የዳበረዉን አማርኛን በትምህርት ቤቶች እንደ አንድ ትምህርት ይሰጥ የሚለውን መምርያ መቀየሩ፣ “አገር-በቀል ዕውቀት እናሳድጋለን፣ አገራዊ መግባባት እንፈጥራል፣” የሚለው መንግሥትም ሆነ ትምህርት ሚኒስቴር ሕዝቡን የሚያስተባብር፣ አገርን የመገንባት፣ ወደፊት በአንድነቷ የሚያስቀጥልና አስተማማኝና ግልጽ ራእይ እንደሌለው ያረጋግጣል።  

ይህ ክሥተት የትምህርቱን ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ በጠቅላላ የአገራችንና የዜጎቿን ህልውና የሚመለከት አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ስለዚህ የምሁራኖቹን ጥናትና ማሳሰቢያ በመከተል፣ ሳይውሉ ሳያድሩ ታይተው መታረምና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ስለሆኑ፣ የሚከተሉት ነጥቦች በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረጉ በጽኑ እናሳስባለን።  

 1. አገሪቱ የዘውግ ፖለቲካ በፈጠረው ችግር ተወጥራ እያለ፣ ሕዝብ ያልመከረበት፣ ከህጉና ራሱ ትምህርት ሚኒስቴር ካስጠናው ጥናት ተቃራኒ የሆነ ፖሊሲና ሕግ በድብቅ አዘጋጅቶ ማውጣትና፣ በይፋ ሳይጸድቅ ተግባርዊ ማድረግ አገርንና መንግሥትን አደጋ ላይ ይጥላል።  ስለዚህ አሁን ድረስ ባለውና እንደ አዉሮጳዊያን አቆጣጠር 1994 በወጣዉ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲና እንዲሁም ራሱ መንግሥት በባለሙያዎች ባስጠናው የትምህርት ፍኖተካርታ መሠረት፣ በሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የፌደራል የሥራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ለአገራዊ መግባቢያነት በመላው የአገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንደአንድ ራሱን የቻለ ትምህርት አላንዳች ሕገወጥነት ለሁሉም እንዲሰጥ እንዲደረግ። 
 2. የወቅቱ የሐሰት ትርክት በወለደው በዘውግ አመለካከትና ውሳኔ ታሪክን ማጥፋትና ወደኋላ መመለስ ለጊዜያዊ ፖለቲካ ቢያመችም፣  የሕዝብን አንድነት የሚያናጋና አገሪቱንም ለውጭ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑ ታውቆ፣ በአመራር ላይ ያለው መንግሥት፣ የትምህርትና የቋንቋ መምርያን በህጉ መሰረት እንዲያወጣ።  ሕገመንግሥቱ  በአንቀጽ ዘጠና በቊጥር ሁለት “ትምህርት በማናቸዉም ረገድ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ፣ አመለካክቶችና ባህላዊ ተጽዕኖዎች ነጻ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት።” ሲል እንዲሁም የኢፌዴሪ ህገመንግስት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ስልጣን አስመልክቶ በሚገልጻው አንቀጽ ስባሰባት ቁጥር ስድስት መሰረት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት “የኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራተጂዎችን ይነድፋል ያስፈጽማል።” አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ክልል-ተሻጋሪ ስለሆነ፣ ፖሊሲዉን የማዉጣት ስልጣኑ ለክልል የሚተው ሳይሆን፣  የፌደራል መንግስት ስልጣን ነው። ስለዚህ የአገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ጉዳይ፣ ከተራ የዘውግ ፖለቲካ እንዲለይና፣ የቋንቋ ጉዳይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይበልጥ ማቀራረቢያ፣ ማገናኛ፣ ማስተባበሪያ፣ ማስተሳሰርያና አገር መገንቢያ እንጂ የመከፋፈያና የጥላቻ መሣሪያ እንዳይሆን፣ የፌደራል መንግስቱ ሃላፊነቱን እንዲወጣ። 
 3. በትምህርት፣ በቋንቋ፣ በታሪክና በሥርዐተ-ትምህርት ጉዳዮች ውስጥ የፖለቲካ ጣልቃ-ገብነት በአስቸኳይ እንዲቆም፤ ጉዳዩ ለዘርፉ ባለሙያዎች ብቻ እንዲተው፤ ለባለሙያዎቹም ሥራ የኢትዮጵያ ሕዝብና፣ ዓለም-ዐቀፉ ኅብረተሰብ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል።
 4. መንግሥት አማርኛ ቋንቋን በማበልፀግ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የቀመር [ኮምፒዩተር]፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት መማሪያና የምርምር ቋንቋ እንዲሆን፣ ሌሎችም የአገራችን ቋንቋዎች ተደጋግፈው የሚዳብሩበትና የሚያድጉበት ስልታዊ ዕቅድ በማውጣት ሥራ እንዲሠራ። 
 5. በቋንቋና በክልል መዝሙር ሰበብ የኢትዮጵያ ለጋ ሕፃናትን በዘውግ መለያየት፣ ወይንም በውስጣቸው የጎሳ ጥላቻ ዘር መዝራት አሳፋሪና አገር የሚያፈርስ አደገኛ ተግባር መሆኑ ታውቆ እንዲቆም እንዲደረግ። ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጥላቻንና የጎሳ መለያያ ቦታ ሳይሆኑ፣ መተሳሰብን፣ አካታችነትን፣ አብሮነትን፣ ህግ አክባሪነትን፣ በምክንያት ማሰብና መወያየትን፣ አንድነትን፣ ኢትዮጵያዊነትንና  የጋራ አገራዊ ራዕይና አመለካከትን የሚያዳብሩባቸው ተቋማት እንዲሆኑ መንግስት እንዲሰራ እናሳስባለን።

  ይህን አገራዊ መግባቢያ ቋንቋን ጉዳይ አስመልክቶ፣ መንግሥት እየተከተለ ያለው አገር-ጐጂ ፖሊሲ ተስተካክሎ፣ ትምህርቱ ለአገር አንድነት፣ ዕድገትና ሰላም አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ ተስፋ እናደርጋለን።

  People to People (P2P) Inc.
  Global Ethiopian Scholars Initiative (GESI)

  [1]https://moe.gov.et/storage/Books/Education%20and%20Training%20Policy%20of%20Ethiopia.pd
  [2]https://planipolis.iiep.unesco.org/sites/default/files/ressources/ethiopia_education_development_roadmap_2018-2030.pdf
  [3]https://moe.gov.et/storage/Books/Education%20and%20Training%20Policy%20Second%20draft%2003-01-2023.pdf
  [4] https://www.youtube.com/watch?v=zmemlQs5h_k
  [5] https://www.youtube.com/watch?v=TzR7aIxwuS0&t=14s
  [6]https://moe.gov.et/storage/Books/Education%20and%20Training%20Policy%20Second%20draft%2003-01-2023.pdf

  _
  በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
  የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
  ትዊተር ፡ @zborkena
  ፌስቡክ ፡ Borkena
  የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

 1. ይህን የፃፉ እና እነርሱን መሰል ቡድኖች የት ትምህርት ቤት እንደ ተማሩ ማወቅ ይቸግራል። ስለ ሥርኣተ ትምህርት ወይም ስለ ቋንቋ እውቀት የላቸውም። የገደዳቸው ስለ አማርኛ ቋንቋ ነው። ሁላቸውም አማራ ቡድኖች ናቸው። (እኔም አማራ ነኝ) አማርኛ ብቸኛ ቋንቋ ካልሆነ አገር ትፈርሳለች ይላሉ። ስለ ትምህርት አሠጣጥ ሳይሆን የበላይነት የሚወሰድባቸው መስሎአቸው ነው። በየትም አገር የተደረጉ ጥናቶች የሚያስረዱት፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ህብረ ብሄር አገሮች ከአንድ በላይ መግባቢያ ቋንቋ መኖራቸው ለመጠናከር እንደሚጠቅም ነው። ወኔ እና ዘራፍ ትቶ ዝግ ብሎ ለአገራችን በሚበጀው መረባረብ ይሻላል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here