Homeነፃ አስተያየትመንግስትን በኃይል የመጣል ፖለቲካ እና ልደቱ አያሌው ለታጣቂ ኃይሎቹ  ትብብር ያቀረቡት የድጋፍ...

መንግስትን በኃይል የመጣል ፖለቲካ እና ልደቱ አያሌው ለታጣቂ ኃይሎቹ  ትብብር ያቀረቡት የድጋፍ አመክንዮ

Advertisement
World Wide Travel Group
መንግስትን በኃይል የመጣል ፖለቲካ
ቻት ጂፒቲ

(በፍቅርተሥላሴ)

ሰሞኑን ልደቱ አያሌው፣ “የታጣቂ ኃይሎች ትብብር ፋይዳ ምንድን ነው?” በሚል ርዕስ ባጋሩት መጣጥፍ፣ በተለያዩ ታጣቂ ኃይሎች (በፋኖ፣ በኦላ እና በህወሓት) መካከል የሚሰማውን የትብብር አዝማሚያ መነሻ በማድረግ፣ ትብብሩ ሊደገፍ ይገባዋል የሚሉባቸውን አመክንዮዎች፣ 1) ከህዝብ–ለሕዝብ ግንኙነት አኳያ፣ 2) ከህዝብና ከሀገር ሕልውና አኳያ፣ 3) ከመስዋዕትነት ቅነሳ አኳያ፣ 4) ከዘላቂ የሥርዓት ለውጥ አኳያ በሚሉ አራት ነጥቦች ዘርዝረው አቅርበዋል።

ሆኖም፣ ለእነዚህ አመክንዮዎች የሰጡት ማብራሪያ፣ ከመልስ ይልቅ ብዙ ጥያቄ የሚያጭር ነው። በተለይም፣ የታጣቂ ኃይሎቹ ትብብር፣ ዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓት ለማምጣት ስለሚኖረው ዕድል፣ በቂ መከራከሪያ አቅርበዋል ብዬ አላምንም።

ልደቱ አያሌው፣ በታጣቂ ኃይሎቹ መካከል የሚደረገውን ትብብር ለመደገፍ በቁጥር አንድ የሚያቀርቡት አመክንዮ፣ ትብብሩ በሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን ቅራኔ ከማርገብ አንጻር የሚኖረውን በጎ ተጽዕኖ ነው። ስለ ትብብሩ መዳረሻ ያለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ ታጣቂ ኃይሎቹ ለመተባበር፣ ትግላቸውን ተመጋጋቢ ለማድረግና ትርክታቸውን ወደ አማካኝ ቦታ ለመሳብ የሚያደርጉት ሙከራ፣ እርግጥም በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን ውጥረትና መጠራጠር ከማርገብ አንጻር አዎንታዊ ሚና ሊኖረው ይችላል።

ልደቱ አያሌው፣ በታጣቂ ኃይሎች መካከል የሚደረገውን ትብብር ለመደገፍ በሁለተኛ ተራ ቁጥር የሚያቀርቡት አመክንዮ ደግሞ፣ ትብብሩ የሕዝብና የሀገርን ሕልውና ከማስጠበቅ አኳያ ሊኖረው የሚችለውን ሚና የሚመለከት ነው። ልደቱ አያሌው፣ ታጣቂ ኃይሎች ግልጽነት ባለው የጋራ አጀንዳ ውጤታማ የሆነ ትብብር መፍጠር ከቻሉ፣ ትብብሩ ሀገሪቱና ህዝቡ የተጋረጠባቸውን የሕልውና አደጋዎች በከፍተኛ መጠን የመቀነስ ዕድል ይኖረዋል ይላሉ። ትንሽ ዝቅ ብለው ደግሞ፤ “ለሀገሪቱ ዜጐች የወቅቱ ቁጥር አንድ አጀንዳ ሕልውናን ማስቀጠል ስለሆነ ጉዳዩን ከሥልጣን ጥያቄ ጋር አያይዞ የማያይ ማንኛውም ዜጋ ሕልውናን ለማስቀጠል የሚረዳን ማንኛውም ዓይነት ጥረት ደግፎ ሊቆም ይገባል። የወቅቱን የታጣቂ ኃይሎች የትብብር ጥረትንም ከጠባብ ፍላጐትና እይታ ወጥቶ ከዚህ ታላቅና ቀዳሚ የሕዝብ አጀንዳ ጋር አያይዞ ማየት ተገቢ ይሆናል” በማለት ያብራራሉ።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ልደቱ አያሌው፣ ትብብሩ “የሕዝብና የሀገርን ሕልውናን ለማስቀጠል ይረዳል” ይበሉ እንጂ፣ እንዴት አድርጎ፣ በምን መልኩ፣ የሕዝብና የሀገርን ሕልውና ለማስቀጠል እንደሚረዳ አያብራሩም። የሕልውና ጥበቃ እንዲደረግ የሚታሰበው፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጥላ ሥር ነው? ወይስ በአምባገነን ሥርዓት ጥላ ሥር ነው? ወይስ ሌላ አማራጭ አለ? የሚለው ግልጽ አይደለም።

ምናልባት፣ ልደቱ አያሌው ጥምረቱ “ሕልውናን ለማስቀጠል” ይረዳል ሲሉ፣ ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ታሳቢ አድርገው ነው እንዳንል ደግሞ፣ ራሳቸው በተራ ቁጥር አራት፣ ከዘላቂ የሥርዓት ለውጥ አኳያ ለትብብሩ ያላቸውን ግምገማ፣ “በእኔ አመለካከት በተናጠልም ይካሄድ በትብብር፣ ጦርነት ለሀገራችን ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ያመጣል የሚል እምነት የለኝም።” በማለት ያስቀምጣሉ። ዝቅ ብለው ደግሞ፣ አንድ ቦታ ላይ፣ “ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የዴሞክራሲ ጥያቄ ከህልውና ቀጥሎ የሚመጣ ሁለተኛ ደረጃ ጥያቄ ስለሆነ የታጣቂዎቹን መተባበር ለመቃወም አሳማኝ ምክኒያት ሊሆነኝ አይችልም።” ይላሉ። 

ድምዳሜው እንደዚህ ከሆነ፣ ትብብሩ ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዲያዋልድ የማይጠበቅ ከሆነ፤ ልደቱ አያሌው ትብብሩ ያስጠብቀዋል ብለው የሚያስቡት፣ “የሕዝብና የሀገር ሕልውና” የሚጠበቀው በምን መልኩ፣ በምን ዓይነት ማዕቀፍ ውስጥ ነው? በማንስ አካል ነው? ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዲያዋልድ እምነት የማይጣልበት ጥምረትስ፣ በየትኛውም መልኩ ቢሆን፣ የሕዝብና የሀገር ሕልውና እንዲታደግ እንዴት ተስፋ ሊጣልበት ይችላል?

እዚህ ላይ፣ “የሕልውና አደጋ” የሚለው አገላለጽ፣ አንድ ሕዝብ በዴሞክራሲያዊና በዜግነት መብቶቹ ላይ ከሚደርስበት አፈና አልፎ፣ ደህንነቱ፣ ሰርቶ የማደር ዕድሉና በሰላም ወጥቶ የመግባት መብቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ የሚፈጠረውን ነባራዊ ሁኔታ ለመግለጽ ሲውል ትርጉም ይኖረዋል። በተረፈ፣ “ሕልውናን ማስቀጠል”፣ “ለሕልውና የሚደረግ ትግል” ወዘተ በሚል የሕዝብንና የሀገርን ደህንነት ማስጠበቅን፣ ዴሞክራሲያዊና የዜግነት መብቶችን ከማስከበር የተነጠለ፣ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ግብ አድርጎ የማቅረቡ አካሄድ፣ አንድ ፊቱን ግባችን አዲስ “የተሻለ አምባገነን” ማዋለድ ነው ካልተባለ በስተቀር፣ ትርጉም የሚሰጥ ነገር አይደለም።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ልደቱ አያሌው፤ ሌላው በታጣቂ ኃይሎች መካከል የሚደረገውን ትብብር ለመደገፍ የሚያነሱት አመክንዮ፣ ታጣቂ ኃይሎቹ በመካከላቸው ሊኖር የሚችለውን የጎንዮሽ ግጭት ማስቀረት ከቻሉ፣ የጦርነቱን ጊዜ ከማሳጠርና መስዋዕትነትን ከመቀነስ አንጻር ሊኖረው ከሚችለው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሚነሳ ነው። እውነት ነው፤ በታጣቂ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ስምምነት፣ የጎንዮሽ ግጭትን ማስቀረትና ትግላቸውን ተመጋጋቢ ማድረግ ካስቻለ፣ የትግሉን ዕድሜ የማሳጠርና መስዋዕትነትንም የመቀነስ ዕድል ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን፣ የትግሉን ጊዜ ማሳጠርና መስዋዕትነቱን መቀነስ፣ ስለ ትግሉ መዳረሻ የሚነገረን ነገር የለም። አሁንም ጥያቄው፣ በአጠረ ጊዜና በአነሰ መስዋዕትነት እንዲያልቅ የሚታሰበው ይህ ትግል፣ ውጤቱ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ ስለመሆኑ ዋስትናው ምንድን ነው? የሚለው ነው።

ልደቱ አያሌው፤ “ስለ ታጣቂ ኃይሎች ትብብር መፍጠር ስናስብ ትብብሩ አገዛዙን ከሥልጣን በማስወገድ አጀንዳ ዙሪያ ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሆነ አድርገን የምናይ ከሆነ ስህተት ነው።” ይሉና፤ ነገር ግን፣ ትብብሩ አገዛዙን ከማስወገድ የተሻገረ ራዕይ እንዳለው አድርገን እንድናይ የሚያስችል ተጨባጭ መረጃ አያቀርቡም። እንዲያውም፣ የራሳቸውም ድጋፍ በግምትና ከርቀት ባገኙት መረጃ ላይ የተመሠረተ መሆኑን፣ ትንሽ ዝቅ ብለው፤ “ለምሳሌ የእኔ ድጋፍ የሚመነጨው ታጣቂ ኃይሎቹ የጀመሩት የትብብር እንቅስቃሴ አገዛዙን ከማስወገድም ባለፈ ህዝቡንና ሀገሪቱን ከሕልውና አደጋ አትርፎ የማስቀጠል አጀንዳንም ያካትታል ብዬ ስለምገምት ነው—-ከርቀት ከማገኘው መረጃ ለመረዳት እንደቻልኩትም ታጣቂ ኃይሎቹ በዚህ ረገድ የደረሱበትን ስምምነት ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው”፤ በማለት ይገልጻሉ።

ልደቱ አያሌው፣ የታጣቂ ኃይሎቹ ትብብር አገዛዙን ከሥልጣን በማስወገድ አጀንዳ ዙሪያ ላይ ብቻ የተወሰነ ስላለመሆኑ፣ ከመላምት ያለፈ ተጨባጭ ነገር አያቀርቡም ብቻ ሳይሆን፤ ቀደም ብለው “ጽምዶ” እስከምን ድረስ? በሚል ርዕስ ባወጡት መጣጥፍ እንዳሰፈሩት ሀሳብ ከሆነ፣ ታጣቂ ኃይሎች ከናካቴው በመሠረታዊ ቅራኔዎቻቸው ላይ ተጨባጭ መፍትሄ ላይ መድረስ አለባቸው ብለውም የሚያስቡ አይመስልም።

ልደቱ አያሌው፤ “ጽምዶ” እስከምን ድረስ? በሚል ርዕስ ባወጡት መጣጥፍ እንዲህ ይላሉ። “ታጣቂ ኃይሎቹ በመካከላቸው ላሉ መሰረታዊ ቅራኔዎች ምን ዓይነት የተጨበጠ መፍትሄ /Solution/ እንዳላቸው መጠየቅም ሆነ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በአሁኑ ወቅት መጠበቅ ተገቢ አይደለም ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን ቅራኔዎቹ በምን አግባብ /Mechanism/ መፈታት እንዳለባቸው አስቀድሞ መስማማትና ውጤቱን ለሕዝብ ማሳዎቅ ይገባል።” ይሉና፣ ቀጥለው ሀሳባቸውን በሚከተለው ምሳሌ ያብራራሉ።

- Advertisement -

“ጉዳዩን በአንድ ተጨባጭና ብዙዎች ሊያነሱት በሚፈሩት ምሳሌ የበለጠ ግልጽ ላድርገው። ለምሳሌ—፣ ፉኖ እና የትግራይ ኃይሎች ወልቃይትን በተመለከተ “የአማራ ክልል አካል ይሁን ወይንስ የትግራይ?” በሚለው ቅራኔ ዙሪያ አሁንም ሆነ ወደፊት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ መጠበቅ የለብንም። በእንዲህ ዓይነቱ ዝርዝር ጉዳይ መፍትሄ ላይ እንዲደረስ መጠየቅም ጊዜውን ያልዋጀና ትብብርን ሳይሆን ቅራኔን የማስቀጠል ውጤት የሚያስከትል ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ጊዜውን ያልጠበቀና ተገቢ ያልሆነ ጥያቄና ግፊትም ከአገሩና ከህዝቡ ይልቅ አገዛዙን የበለጠ የሚጠቅም ውጤት ሊያስከትል ይችላል። በሱ የቁማር ካርታ መጫዎት ነውና።“

“ልዩነቶቻችንን በይደር እናቆይ፤ አሁን ዋናው ትኩረት ሕልውናችንን ማስጠበቅ ነው፤ ሌላው ሌላው ኋላ ላይ፣ ወይ በድርድር፣ ወይ በሽግግር መንግስት ይፈታል” የሚለው ጠቅለል ያለ ሀሳብ፣ የልደቱ አያሌው ብቻ አይደለም። ከራሳቸው ከታጣቂ ኃይሎቹ ጀምሮ፣ በአጠቃላይ ትብብሩን በሚደግፉ ወገኖች አካባቢ ተደጋግሞ እየተነሳ ያለ ሀሳብ ነው።

ፖለቲካችን ስሱና ለግጭት የተጋለጠ ከመሆኑ አንጻር፣ በልዩነቶች ላይ ደፍሮ ለመነጋገር ያለው ስጋት ከምን እንደሚመነጭ ግልጽ ነው። ሆኖም፤ በአንድ ወገን መንግስትን ለመጣል እየታሰበ፣ በሌላ ወገን በመሠረታዊ ቅራኔዎች ላይ አንነጋገርም ማለት አብሮ አይሄድም። ልደቱ አያሌው እንደ ምሳሌ ያቀረቡት የወልቃይት ጉዳይና መሰል ስሱና አወዛጋቢ የፖለቲካ ቅራኔ መስመሮች፣ በራሳቸው የበቀሉ ሳይሆኑ፣ ሀገሪቱ የተመራችበት የፖለቲካ እሳቤ ያዋለዳቸው ናቸው። ለምሳሌ፤ የወልቃይትን ውዝግብ ነጥለን ካየን፣ መሠረታዊ መንስኤው፣ ማንነትን ከመሬትና ከአስተዳደር ጋር ያጋመደው የፖለቲካ እሳቤያችን ነው። ይህን ከምንጩ ለማድረቅ፣ ወደ ኋላ ተመልሶ የመጣንበትን መንገድ በጋራ በጥልቅ መመርመርና፣ አዲስ የሚያግባባን እይታ መፍጠር ይጠይቃል። ያለበለዚያ፣ ዞሮ ዞሮ እነዚህ ቅራኔዎች አንድ ቦታ ላይ እንደገና ወደ ግጭት ማምራታቸው አይቀሪ ነው።

እንደ ሀገር የተጋረጠብን ፈተና፣ ይህኛው ወይም ያኛው አገዛዝ ከሚፈጥረው ተግዳሮት ያለፈ፣ የተጠላለፈና የተወሳሰበ ነው። መንግስትን፣ ያውም በኃይል፣ ለመጣል አልሞ የሚንቀሳቀስ ወገን፣ አገዛዙን ከመርገም ባለፈ፣ በመሠረታዊ ተግዳሮቶቻችን ላይ የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ፣ ለመነጋገርና ለመደራደር የሚያስችለውን አቅም ሊገነባ ይገባል። ታጣቂ ኃይሎቹ አሁን ላይ ሆነው ይህን አቅም መገንባት ካልቻሉ፣ አራት ኪሎ ሲደርሱ ከየት ያመጡታል? በደፈናው “መጀመሪያ አገዛዙን ተባብረን እንጣልና፣ ልዩነታችንን ኋላ በድርድር፣ በሽግግር፣ በህዝበ-ውሳኔ ወዘተ እንፈታለን” የሚለው አባባልም፣ ራስንም ሕዝብንም ከመሸንገል ያለፈ እርባና የለውም።

በነገራችን ላይ፣ ከወቅቱ ታጣቂ ኃይሎች የትብብር ዜና ጋር በተያያዘ፣ ውይይት፣ ድርድር፣ የሽግግር መንግስትና መሰል ቃላት፣ “አይ፣ ይህኛውን እንወጣው እንጂ፣ ያኛውማ እዳው ገብስ ነው” በሚል አይነት፣ ቀለል ተደርገው የሚወረወሩበት ሁኔታ ትንሽ ግርምት የሚፈጥር ነው። የፖለቲካ ባህላችንን ዘነጋነው እንዴ? እንዲህ መወያየቱና መነጋገሩ ቢሆንልንማ ኖሮ፣ ቀድሞውኑ እንዲህ ምስቅልቅላችን መች የወጣ ነበር?

ዛሬ ላይ ቁመን፣ መንግስትን ስለመጣል ስናስብ፣ ወደ ኋላ ተመልሰን ያለፉት የመንግስት ለውጦች ምን መልክ እንደነበራቸው ማስታወሱ የሚጠቅም ይመስለኛል። ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት፣ በአንድ አገዛዝ ሥር ፍትህ ማጣት፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ሌላ ሌላውም በደልና ሮሮ ይጠራቀማል፤ የተጠራቀመው ብሶት ቀስ በቀስ ወደ ተቃውሞ ያድጋል፤ አገዛዙን ከሥልጣን የማስወገድ ትግል ይወለዳል። ትግሉ ተጠናክሮ፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አገዛዙን ያስወግዳል።

አገዛዙ ሲወገድ፣ የመንግስት ለውጡ አዲስ ተስፋ ይዞ ይመጣል፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ተስፋው ወደ አዲስ የፖለቲካ ፍጥጫና ግጭት ይሸጋገራል። ሥልጣን ለመጠቅለል ፍትጊያ፣ ሴራና አሻጥር ይጀመራል። አንድ አካል አሸናፊ ሆኖ ይወጣል፤ ሥልጣኑን ማጠናከር ይጀምራል። አሸናፊው ወገን ሥልጣኑን ባጠናከረ ቁጥር፣ በአዲሱ ሥርዓት ቦታ ያጡ፣ የታፈኑና የተገፉ የፖለቲካ ኃይሎች በተለያየ መልክ እየተንጠባጠቡ ይወጡና አዲስ ትግል ይጀምራሉ።

አዲሱ መንግስትም ቀስ በቀስ በሕዝብ ውስጥ የራሱን ብሶትና ተቃውሞ ያከማቻል። ቀስ እያለ አመጽ ይቀሰቀሳል፤ አመጹ እየተቀጣጠለ ይሄዳል፤ አገዛዙ መጀመሪያ ይዳከማል፣ ቀጥሎም ይወገዳል። “አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ይከፈታል” የሚል ተስፋ እንደገና ይፈጠራል። ብዙም ሳይቆይ ተስፋው ይከሽፍና፣ ለውጡ እንደገና ወደ ግጭት ያመራል። አዲስ ኃይል አሸንፎ ይወጣል፤ አሸናፊው ሥልጣኑን ይጠቀልላል፤ የተገፋው ደግሞ አዲስ ትግል ያፋፍማል። አዙሪቱ ይቀጥላል።

ያለፉት ለውጦች በሰው ሕይወት፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ መረጋጋትና በብሔራዊ ጥቅም ያስከፈሉን ዋጋ ቀላል አይደለም። ብዙ ደም ፈሷል፤ ብዙ ሰው ተሰዷል፣ ተፈናቅሏል፣ ተንገላቷል፤ ሀብት ወድሟል፤ የልማት ዕድሎች ባክነዋል፤ ሀገሪቱም ከአንዱ የፖለቲካ ቀውስ ወደ ሌላው እየተሸጋገረች፣ የረጅም ጊዜ መረጋጋት እንዳታገኝ ሆናለች። ይህ ሁሉ ዋጋ ተከፍሎም ግን፣ አንድን አገዛዝ በሌላ አገዛዝ ከመተካት ያለፈ፣ ለዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓት የሚሆን መሠረት እስካሁን መጣል አልቻልንም።

ታጣቂ ኃይሎቹ መቀራረብና መነጋገር መጀመራቸው እሰየው ነው። ነገር ግን፣ አገዛዝ በወደቀ ማግስት የሚነሱትን የሥልጣን፣ የፖለቲካ አቅጣጫና የመሠረታዊ ቅራኔዎች ጥያቄዎች በሰላም ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ አቅም ባልተገነባበት ሁኔታ፣ መንግስትን ማስወገድ፤ ትርፉ ሀገርንና ሕዝብን ለተጨማሪ ዋጋ መዳረግ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ወደ ሥልጣን ያመጣው የ2010 ዓ.ም. ለውጥ፣ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ያመራል የሚል ተስፋ እንዲጣልበት ካደረጉት ነገሮች አንዱ፣ የለውጡ አራማጆች ከራሱ ከኢህአዴግ የወጡ መሆናቸው ነበር። በሰዎችና በድርጅቶች መካከል ያለ ትስስር በራሱ፣ ከለውጥ በኋላ የሚነሳውን የሥልጣን ሽኩቻ ለማስቀረትና ሰላማዊና ዘላቂ ሽግግር ለማድረግ ዋስትና ቢሆን ኖሮ፣ ለዓመታት በአንድ ድርጅት ጥላ ሥር አብረው ሀገር የመሩ፣ የረጅም ጊዜ አብሮነትና ጓድነት ያፈሩ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ጥል ተነስቶ፣ ኢህአዴግ ተፈረካክሶ፣ በለውጡ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ለየለት ጦርነት መች እንገባ ነበር።

ልዩነትን ማስተናገድ፣ ቅራኔን ያለ ኃይል መፍታት፣ የሥልጣን ፉክክርን በሕግና በተቋማት ማስተናገድ የሚችል የፖለቲካ መደላድል ባልተዘረጋበት ሁኔታ፣ በማናቸውም ኃይሎች መካከል የሚፈጠር ትብብር፣ ለዘላቂ ሰላም ዋስትና አይሆንም።

በአንድ በኩል፣ አሁን መንግስትን ለመጣል ትብብር እየፈጠሩ ነው የሚባሉት ኃይሎች (አፋብን፣ ኦላ እና ህወሓት)፣ በፖለቲካ እይታቸው መሠረታዊ ቅራኔዎች ያሏቸው መሆኑ፤ በሌላ በኩል፣ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች መሆናቸው፣ መንግስትን ለመጣል የሚደረገውን ትግልም ሆነ፣ ትግሉ ተሳክቶ መንግስት ቢወድቅ ቀጥሎ ሊከተል የሚችለውን ሁኔታ፣ እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል።

ከዚህ ቀደም፣ ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል ደርግን ከሥልጣን አስወግዶ ሥልጣን ሲቆጣጠር፣ ትግሉ ደም አፋሳሽና ሀገርን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈለ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ አንዴ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ግን፣ በአንጻራዊ ፍጥነት ማዕከላዊ የፖለቲካ ሥልጣንን ተቆጣጥሮ ሀገርን ማረጋጋት ችሎ ነበር።

ይህ እንዲሆን ግን፣ የትጥቅ ትግሉ በርዕዮተ-ዓለምም ሆነ በወታደራዊ አቅም የበላይነት በነበረው አንድ አውራ ድርጅት (በህወሓት) መመራቱ፤ ተሰናባቹ ደርግ በብሔር ያልተዋቀረ መሆኑ፤ ብሔርተኝነት አሁን ባለበት ደረጃ አለመንሰራፋቱ፤ ኢህአዴግ በአንጻራዊ ፍጥነት ማዕከላዊ የፖለቲካ ሥልጣንን እንዲቆጣጠር የየራሳቸው አስተዋጽኦ ነበራቸው።

ዛሬ ላይ ግን፣ እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች በሙሉ የሉም። ከታጣቂ ኃይሎቹ መካከል በፖለቲካም ሆነ በወታደራዊ አቅም የበላይነት ያለው አንድ አውራ ኃይል የለም፤ ታጣቂ ኃይሎቹ በየራሳቸው ውስጥ እንኳን የጠነከረ ድርጅታዊ አንድነት አላቸው ለማለት ያስቸግራል፤ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታትም ብሔርተኝነት እጅግ ተስፋፍቷል። ሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝም፣ የፖለቲካ ቅራኔዎችን ወደ ብሔር ተቃርኖ የመጠምዘዝ አዝማሚያ ያለው ነው። ይህ ሁሉ ተደራርቦ፣ መንግሥትን በኃይል የመጣሉን ትልም እጅግ የተወሳሰበና አደገኛ ያደርገዋል። 

ማንም አገዛዝ ቢቻለው፣ ሁሉንም ሰጥ ረጭ አድርጎ፣ የኃይል የበላይነትን ይዞ መግዛት ይጠላል ብዬ አላምንም። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ፣ ቀድመውት ከመጡ አገዛዞች በተለየ፣ ከማዕከላዊ የፖለቲካ የበላይነት ያፈናቀለውን አካል፣ ጠራርጎ ከፖለቲካው መድረክ ማስወጣት አልቻለም፤ ህወሓት ተፎካካሪ የኃይል ማዕከል ሆኖ ቀጥሏል። በሌላም በኩል፣ የለውጡ መንግሥት ገና ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ ነው፣ በኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች ጋር ትንቅንቅ ውስጥ የገባው። በተመሳሳይም፣ አዲሱ መንግሥት ሥልጣኑን ገና ለማጠናከር እየተውተረተረ ባለበት ወቅት፣ እንደ አማራ ብሔርተኝነት ያሉ አዳዲስ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ሊገመት በማይችል ፍጥነት አድገው፣ የትጥቅ ትግል መልክ የያዙበትና ተፎካካሪ ኃይል ሆነው የወጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ለማለት የፈለኩት፣ ተገዳዳሪ ኃይሎች ሲበራከቱ፣ የኃይል ሚዛን ሲበታተንና ማዕከላዊ መንግሥት በአስተማማኝ ሁኔታ የኃይል የበላይነትን መያዝ ሳይችል ሲቀር፣ የሚፈጥረውን የጸጥታ ክፍተትና የሚያስከትለውን የደህንነት አደጋ፣ በተወሰነ መልኩ አሁን እያየነው ነው። በዚህ ሁኔታ ላይ፣ መንግሥትን በኃይል የመገልበጥ ሙከራ ምን ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አያዳግትም። እነዚህ የተበታተኑ ታጣቂ ኃይሎች ለጊዜው ልዩነታቸውን እንደምንም አቻችለው፣ አራት ኪሎ መድረስ ቢችሉ እንኳን፣ እንደ ቀደሙት ለውጦች አንድ አምባገነን በማንገሥ የመጠናቀቅ ዕድላቸው እጅግ ጠባብ ነው። ከዚያ ይልቅ፣ ማንም የበላይ መሆን ወደማይችልበት፣ አሸናፊ ወደሌለውና መጨረሻው ወደማይታይ የእርስ በእርስ ግጭት ሀገርን የመክተት ዕድሉ የበለጠ ሰፊ ነው።

ይህ አደጋ ግን፣ ታጣቂ ኃይሎቹ ተባብረው ከሚያደርጉት ትግል ብቻ የሚመጣ አይደለም። አሁን በየአቅጣጫው በተናጠል ከሥርዓቱ ጋር የሚያደርጉት ግብግብ እልባት ሳያገኝ በዚህ መልክ ከቀጠለም፣ በተመሳሳይ አሸናፊ ወደሌለውና የማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት የማደግ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።

ይህን ስል፣ “ታዲያ መንግስት ለችግሩ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት ካልፈለገ፣ ሰው አፈናንና በደልን በጀ ብሎ፣ እጁን አጣጥፎ ይቀመጥ ወይ?” የሚል መከራከሪያ እንደሚነሳ ይገባኛል። የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲያሰፋ፣ የሕዝብን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱንም እንዲወጣ፣ መንግስት ላይ ጫና ማድረግ ተገቢ ነው። በግልባጩ ግን፣ የሕዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ፣ ግፍና በደልን ለማስቀረት እታገላለሁ የሚል ወገንም፣ የመረጠው የትግል መንገድ የሕዝብን መከራ እያቃለለ ነው ወይስ ይብሱን እያከፋ ነው ብሎ ራሱን የመጠየቅ ኃላፊነት፣ ለሚያስከትለው ውጤትም ተጠያቂነት አለበት።

አሁን ላይ በየክልሉ የሚደረጉትን የትጥቅ ትግሎች፣ “እከሌ ሕዝብ ራሱን ከሕልውና አደጋ ለመከላከል የሚያደርገው ትግል”፣ “እከሌ ሕዝብ የተቃጣበትን ጥቃት ለመመከት የሚያደርገው ትግል” እያሉ መግለጽ ልማድ ሆኗል። እውነት እንነጋገር ከተባለ ግን፣ ሕልውናውን በትግል እያስጠበቀም፣ ራሱንም ከጥቃት እየተከላከለም ያለ ሕዝብ የለም። ይልቁንስ፣ በአማጺያኑና በመንግስት መካከል በሚደረገው ግብግብ፣ ሕዝብ መሃል ቤት በሁለት ጥይት እየተመታ ነው። በአንጻሩ፣ ታጣቂዎቹ ከሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች በአንጻራዊ ርቀት ላይ ያሉ ቦታዎች፣ የተሻለ መረጋጋት አላቸው።

ከለውጡ በኋላ በሕዝብ ደህንነት ላይ ለተፈጠረው አደጋ፣ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የለውጡ መንግሥት የፈጠረው የደህንነት ክፍተትና፣ የሕዝብን ደህንነት ከማስጠበቅ ረገድ ያሳየው፣ ለማመን የሚከብድ፣ ፈጽሞ ከመንግሥት አካል የማይጠበቅ ቁርጠኝነት ማጣትና ግዴለሽነት ነው። ሆኖም፣ ቀጥለው በየአካባቢው የተነሱት ግጭቶች የደህንነት ስጋቱን ይልቁን አባባሱት እንጂ አላቃለሉትም። ጦርነቱ፣ መንግሥት አማጺያኑን፣ አማጺያኑ መንግሥትን እየከሰሱ፣ ለሕዝቡ ደህንነት ኃላፊነት የሚወስድ አካል የጠፋበት ሁኔታ ነው የፈጠረው። 

በጦርነቱ ምክንያት፣ ትምህርት፣ ሥራ፣ እርሻ፣ ንግድ፣ ከቦታ ቦታ መዘዋወር፣ ሰርግና ለቅሶ ሳይቀር እየተስተጓጎለ ነው። ጦርነቱ በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ውስጥ እየፈጠረ ያለውን የስጋትና ያለመረጋጋት መንፈስ መተመን የሚቻል አይመስለኝም። በዚያ ላይ፣ የአሁኑ ጦርነት፣ እንደ ቀድሞው “ውረድ እንውረድ” ተባብሎ ሜዳ ወርዶ የሚደረግ አይደለም፤ ማህበረሰቡ መኃል፣ ሕዝብን ለቀጥተኛ ጥቃት ተጋላጭ በሚያደርግ ሁኔታ የሚካሄድ ነው። ጦርነቱ ሕዝብ ላይ እየጋረጠ ያለው አደጋና እያስከፈለ ያለው ዋጋ፣ የጦርነቱን ፋይዳ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው።

በየክልሉ ያሉት ታጣቂዎች ሕዝብን ከጥቃት በአስተማማኝና በዘላቂ ሁኔታ ሊከላከሉ አይችሉም። የሕዝብ ደህንነት በአስተማማኝና በዘላቂ ሁኔታ የሚጠበቀው፣ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ሲኖረን ብቻ ነው። ሌላ አቋራጭ የለም። ይህ እንዲሆን የግድ መንግስት መቀየር አለበት ከተባለም፣ ጦርነት ብቸኛው የመንግስት መቀየሪያ መንገድ አይደለም። ለምሳሌ፣ ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በሀገራችን ከተከሰቱት ሦስት ዋና ዋና የመንግስት ለውጦች፣ በሁለቱ ውስጥ ሕዝባዊ ተቃውሞና እምቢተኝነት ወሳኝ ሚና ነበረው። ሕዝባዊ እምቢተኝነትም የራሱ ዋጋ አለው፤ ሆኖም፣ ከጦርነት እጅግ የተሻለ አማራጭ ነው።

ከቅንጅት መፈራረስ በኋላ፣ ግንቦት 7 በሁለገብ ትግል የህወሓት/ኢህአዴግን አገዛዝ ለመጣል አልሞ ሲመሰረት፣ ሥርዓቱን በኃይል ለመጣል አስፈላጊነት አመክንዮ ሆኖ ይቀርብ የነበረው፣ ከምርጫ 97 በኋላ ኢህአዴግ ደንብሮ፣ በጥቂቱም የነበረውን የፖለቲካ ምህዳር ጥርቅም አድርጎ በመዝጋት፣ ለሰላማዊ ትግል ምንም መፈናፈኛ ስላሳጣ፣ ያለው አማራጭ ሥርዓቱን፣ በሁለገብ ትግል በኃይል መጣል ብቻ ነው፣ የሚል ነበር። እውነትም፣ በወቅቱ ኢህአዴግ ምርጫ 97ን ተከትሎ የወሰደው እርምጃ እንዲህ ያሰኝ ነበር። ሆኖም ግን፣ በስተመጨረሻ የሆነው ሌላ ነው። የግንቦት 7 ሰዎች ከኤርትራ በረሃ ሳይወጡ፣ መኃል ሀገር በተቀጣጠለ ሕዝባዊ አመጽ የመንግስት ለውጥ መጥቶ፣ የግንቦት 7 ሰዎችም ወደ አዲስ አበባ በቦሌ በኩል የገቡበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው።

ያለጊዜው፣ የሚሆን ነገር ላይመስል ይችላል። ጊዜውና ሰዓቱ ሲደርስ ግን፣ በአንድ ልብ “እምቢ” እንዳለ ሕዝብ አስፈሪ ኃይል የለም። በ2010 ዓ.ም. ለውጥ ዋዜማ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሱት ሕዝባዊ አመጾች መቀጣጠላቸውና እርስ በርስ መናበብ መጀመራቸው፣ ኦህዴድ ሀገራዊ መልእክት ይዞ ወደ መሃል መገስገስ መጀመሩና ከብአዴን ጋር ጥምረት መፍጠሩ ተዳምረው፣ በሕዝብ ውስጥ የፈጠሩት ተስፋና መነቃቃት፣ የፖለቲካውን የሥልጣን ሚዛን በመቀየር፣ የመንግስት ለውጥ እንዲመጣ ወሳኝ ግፊት መፍጠር ችሏል። የለውጡ መጨረሻ እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ይሆናል። ዞሮ ዞሮ ግን፣ ክስተቱ፣ ፍርሃቱ የለቀቀው፣ ተስፋ ያየና በአንድ ላይ መቆም የቻለ ሕዝብ ያለውን አቅም አሳይቶናል።

ወደፊትም ኢትዮጵያ ውስጥ፣ መንግስትን አስገድዶም ይሁን ቀይሮ፣ ወደ ተደላደለና ዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓት ለመሸጋገር ያለው ብቸኛው አስተማማኝ አማራጭ፣ በአገዛዙ ላይ ካለን ምሬት ባለፈ፣ በመሠረታዊ ቅራኔዎቻችን ዙሪያ መፍትሄ ማፈላለግ፣ እይታችንን ማሰናሰል፣ በጋራ መቆምና፣ ዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓት የሚቆምበትን መደላድል መገንባት ነው። ይህ ቀላል ሥራ አለመሆኑ ግልጽ ነው። ወደ ኋላ ተመልሰን የመጣንበትን መንገድ መፈተሽ፣ ስለምንመኘው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለንን ግንዛቤ ማስፋት፣ ስለ ሰው ተፈጥሮ፣ ስለ ማህበረሰብ፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ታሪክ፣ ስለ መንግስት፣ ስለ ዜግነትና መሰል መሠረታዊ ጉዳዮች ያለንን እሳቤ በጥልቀት መመርመር ይጠይቃል። ትግስትና ሆደ ሰፊነትን ይጠይቃል።

ጥቂቶች ሥልጣን ጠቅልለው ያሻቸውን የሚያደርጉበት፤ ሌላው ዜጋ በገዛ ሀገሩ ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ የሚጠበቅበት፤ ብዙ እንግልትና በደል የሚደርስበት ሀገር ነው ያለን። ምሬታችን፣ ቁጣችን ምክንያታዊ ነው። ነገር ግን፣ “ሕዝባዊ መንግሥት አሁን!”፣ “ፍትህ አሁን!”፣ “ነጻነት አሁን!” እያልን ስንፎክር ሃምሳ ዓመት አለፈን። ችኮላው የት አደረሰን? “የፈጀውን ይፍጅ፤ ያለቀው ይለቅ፤ የመጣው ይምጣ” የሚል የትግል ዘይቤ፣ መከራችንን አለቅጥ አራዘመው እንጂ ምን መፍትሄ ሆነልን?

መሠረታዊ ሀገራዊ መግባባት ሳይፈጠር የሚደረግ የመንግስት ለውጥ፣ ከእስካሁኑም በከፋ ዋጋ፣ የትናንቱ ተገፊ የዛሬ አሸናፊ፣ የዛሬው ተገፊ ደግሞ የነገው ታጣቂ የሚሆንበትን የግማሽ ምዕተ ዓመት አዙሪት ያስቀጥል እንደሆን እንጂ፣ ዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓት አያመጣም። ይልቁንም ደግሞ፣ መሠረታዊ መግባባትን ሳያስቀድም፣ አገዛዙን በጋራ ክንድ በማስወገድ ላይ ብቻ ተመርኩዞ፣ በሚፈጠር ወታደራዊ ጥምረት የሥርዓት ለውጥን መመኘት፣ ለባሰ የእርስ በእርስ ግጭት ያጋልጠናል እንጂ፣ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓትን አያዋልድም።

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian NewsBorkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

1 COMMENT

  1. የአንደኛው ዓለም ጦርነት የጦርነቶች ሁሉ ማብቂያ፤ የሰላም ደወል መደወያ ተብሎ ዓለም በእልልታ ሲቀበለው የጦርነት ማክተሚያ መሆኑ ቀርቶ ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ተክቶ ወደ 80 ሚሊዪን የሚሆን ሰዎችን በልቶ በሥፍራው ቀዝቃዛው ጦርነትን ተካ። በዚህ የፍጥጫ ዘመን ምዕራቡና ምስራቁቡ ተፋጦ በአንጻሩ ሌሎችን እያስታጠቁ እንዲተላለቁ አድርገዋል አሁንም በማድረግ ላይ ናቸው። ጦርነትና እልቂት ከሰው ልጆች ርቆ አያውቅም። የሃበሻዋን ምድር ከሌሎች ሃገራት የተለዬ የሚያደርጋት የእርስ በእርስ ጦርነቱና ፋታ የማይሰጥ ሆኖ መገኘቱ ነው። የ3ሺህ ዘመን ነጻነት አለኝ የምትለው ኢትዮጵያ ያኔም አሁንም በራሷ ልጆች መናኮር ሰላምን ተነፍጋለች። ጉራና ፉከራውን ወደ ጎን አድርገን ተምረናል የሚሉትን በውጭ ሃገር የመሸጉ የብሄር በሽተኞች የሚሉትን መስማትና ማንበብ ያንገፈግፋል። መማር ለውስልትና፤ መማር እንደ አውሬ በዘርና በቋንቋ ለመሰለፍ ከሆነ ድንቁርናው ይመረጣል።
    አሁን እንሆ በውጭና በውስጥ ሆነው የብልጽግናውን መንግስት በሃይል ለመጣል የሚኳትኑት ሁሉ ህልማቸው ቢሳካ በመንገድ ላይ የሚገዳደሉ አንድ ቀን አብረው የማይውሉ ለመሆናቸው የዛሬው ተልካሻ አቋማቸውና ያልጠራ የፓለቲካ ጥምረታቸው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የሻቢያ/የወያኔ/የኦላ/የፋኖና የሌሎችም ብሄሮች ጥምረት ብልጽግናን ገፍትሮ በምድሪቱ ሰላም ያመጣል ብሎ ማመን ጅል መሆን ነው። ትላንት ሻቢያና ወያኔን ሌሎችንም የሃገራችን አጥፊ ሃይሎችን አይዞአቹሁ በማለት ሲያስታጥቁ የነበሩት ሁሉ በጊዜ እነርሱም በሰፈሩት መስፈሪያ ተርፎ እየተመለሰላቸው እንደሆነ በሱዳን/በሊቢያ/በሶሪያ/በኢራቅ/በየመን እያየነው ነው። ገና ይቀጥላል! ከአመታት በፊት በተማሪዎች ጩኽት የተጀመረው የየመን ግርግር ዛሬ ላይ ሃገሪቱን ለሶስት ቆርሶ እያፋጃቸው ነው። ማን ያስታውስ ይሁን የመን ሁለት ሃገር እንደነበረች? ከዚያ በፊት በኦቶማኖችና በእንግሊዞች ሥር ሃበሳ እንዳየች? በእንግሊዝ ግዛት ጸሃይ አይጠልቅም የተባለላት ታላቋ ብርታኒያ ዛሬ ምላስ የምታክል ሃገር እየሆነች ነው። ገና ብዙ እናያለን። እንሰንብት!
    ፓለቲከኞች ድኩማን ናቸው። የዛሬን እንጂ ነገ የሚሆነውን አያዩም። ትላንት በብልጽግናው መንግስት የተበተነ ድቄት የተባሉት ወያኔዎች ሁለት ሶስት ጊዜ ጦርነት ከፍተው እልፍ ሰው አልቆ፤ ንብረትና ሃብት ወድሞ እንሆ እንደገና በጽምዶ ስም ሃተፍ ተፍ በማለት ላይ ይገኛሉ። ያኔ በጦርነቱ ጊዜ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው ያለው ጻድቃን ሸገር ላይ እየቀባጠረ ይገኛል። ለዚህ ነው ፓለቲካ የቆሻሻ ክምር ነው የምንለው። ሁሌ ሲጨስ የሚኖር! ጊዜ ሰጠን በማለት አሁን ላይ የህዝብን እንባና ጮኸት ያራቡት የኦሮሞ ብሄርተኞች ደግሞ በወረፋቸው ባበደሩት ልክ ይመለስላቸዋል። ይህ ፉከራ ሳይሆን ኑረን ያየነው የፓለቲካችን አዙሪት ውጤት ነው።
    አቶ ልደቱ የታጣቂ ሃይሎች ጥምረት ፋይዳ ምንድን ነው ለሚለው መልሱ የለማኛ ቆማዳ ነው። ሁሌ ሲፈታ ሲታሰር የሚኖር። ዝንቅ ነገር በውስጡ የያዘ። አንድ የሻገተ ደህናውን የሚበክልበት። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቀናቃኝ ሃይሎች የሚመዘኑት ካሳለፍነው ታሪክ ወደኋላ ተመልሶ በማየት ብቻ ነው። ይህ በየወንዙ የሚማማለው ተጠማጅ እንኳን ተጠምዶ ይቅርና ብቻውን ቆሞ እንኳን ጥላውን የማያምን ተቅበዝባዥ ፍጡር ነው። ዛሬ አብሮ ተዋግቶ ቆይቶ እርስ በእርስ መጋደል የተለመደ ነው። ለዚህ ደግሞ ወያኔና ሻቢያ የተካኑ ናቸው። የራሳቸውን ታጋዪች ከጀርባ አስተኩሰው የሚያስገድሉ፤ በየምክንያቱ የነቁና የበቁትን አፈር የሚያለብሱ መሆናቸው በራሳቸው ታጋዪች የተረጋገጠ ሃቅ በመሆኑ ለማመን አያስቸግርም። ወያኔና ሻቢያ አረመኔዎች ናቸው። እጃቸውን ባነሱ ሰዎች ላይ ታንክ የነድ፤ የማረኳቸውን ወታደሮች በጅምላ የጨፈጨፉ፤ የኢትዮጵያን ሰራዊት ከፍራቻ የተነሳ የበተኑና አሉ የሚባሉትን በተጠና መልኩ በመርዝ፤ በመኪና በመግጨት፤ ገደል በመገፍተር፤ በማፈንና ደብዛቸውን በማጥፋት ለ 27 ዓመት ሃገሪቱ ላይ ጨፍረዋል። አሁን ደግሞ እንሆ ለሌላ ጦርነት ዝግጅት ላይ ናቸው። በአንጻሩ የኦሮሞው የብሄር ሰካራም በምድሪቱ ላይ የሚያደርገውን ግፍ በየጊዜው እያየን ስለሆነ ከእነዚህ በራሳቸው የፈጠራ ታሪክ ከታመሙ ስብስቦች አንድም ሰላም ለሃገራችን አይመነጭም። በተለይ የፋኖ ከእነዚህ አማራ ጠል/ኢትዮጵያ ጠል/የኦርቶዶክስ ቤ/ክ አፍራሽና አቃጣዪች ጋር ለመጣመር መከጀሉ ምን ያህል እንደተጃጃሉ ያሳያል። አማራ ይሁን ኦሮሞ፤ ትግሬ ይሆን ሌላ በብሄር ተደራጅቶ ሃገር ነጻ ማውጣት አይችልም። የሚያዋጣው በድርድር በሰላም ነገሮችን በማላላት ጦርነትን ማቆም እንጂ! መገዳደሉን ኖረንበታል፤ እያየነውም ነው ትርፍ የለሽ በህዝባችን ላይ የመከራ ዶፍ አዝናቢ ነው። ብልጽግናም ልብ ሰጥቶት ፉከራውን ትቶ በእስር ቤት ያጎራቸውን ሁሉ መፍታት ይኖርበታል። ሰው ተናገረ፤ ጻፈ ተብሎ በፈጠራ ክስ ሃበሳ መቁጠር አይገባውም። ያልተሄደበት መንገድ የሰላም ጎዳናው ብቻ ነው። ሌላውን ሁሉ ነጉደንበታል። አይሰራም። አልሰራም። በጊዜ ነገሮችን አርግበን ስለ ሰላም ስንል ጦርነትን እስካላቆምን ድረስ የሱዳን/የየመን/የሶማሊያ ወዘተ እጣ ፈንታ በእኛ ሃገር ላይ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። ጦርነት ይብቃ። ጥምረቱም ይፍረስ ለማንም አይጠቅምምና ወደ ሰላም ድርድር ተመለሱ። እንደ አቶ ልደቱ አያሌው ያሉ ፓለቲከኞችም እነዚህ የደመ ነፍስ የብሄር ሰካራሞችን ከእንቅልፋቸው እንዲነቁ በሰላም ስም መቀስቀስ እንጂ ጦርነትን እንደ አማራጭ ወስዶ መንደፋደፍ ለማንም ለምንም እንደማይረባ በማስረዳት ሊቀሰቅሱ ይገባል እንጂ ጦርነትን እንደ አማራጭ መውሰድ አላዋቂነት ነው ባይ ነኝ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News