
ያሬድ የኔዓለም
በመጀመሪያ አቶ ክርስቲያን ታደለ ለዓመታት ሲማቅቁበት ከነበረው ኢ-ፍትሐዊና ጨለማ እሥር እንኳን ተፈቱ፤ እንኳን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጆቻቸውና ለመላው ደጋፊዎቻቸው በሰላም ለቤታቸው አበቃቸው ማለት እወዳለሁ። የሰው ልጅ በነጻነቱ፣ በአካሉና በሕሊናው ላይ የሚደርስ የግዞት መከራ በቀላሉ የሚገመት ባለመሆኑ፣ የክርስቲያን ወደ ቤተሰቡና ወደ ነጻነቱ አየር መመለስ በራሱ ትልቅ የምሥራችና የደስታ ምንጭ ነው።
አቶ ክርስቲያን ታደለን በቅርበት የማወቅ ዕድል ያገኘ ሰው በቀላሉ የሚረዳው አንድ እውነት አለ፦ በርቀት የሚታየው ቁመናውና በቅርበት ያለው ማንነቱ አይጣረሱም። በሥነ ልቦናው ዓለም “ጀግኖችህን በቅርበት አትወቅ“ (Never meet your heroes) የሚባለው አባባል፣ የሩቅ አድናቆት በቅርብ ትዝብት እንዳይደበዝዝ የሚሰጥ ማስጠንቀቂያ ነው። ክርስቲያን ግን ይህንን የተለመደ ስብራት ይሽረዋል። የሚናገረውን የሚኖር፣ በባሕሪ (Character) እና በጽናት (Integrity) የሚመዘን፣ ጥልቅ አሰላሳይ፣ ደፋርና ላመነበት ዓላማ በጽናት የሚቆም የፖለቲካ ሰው ነው።
ስለ ሰብእናው ብዙ ብል ደስ ባለኝ፤ ነገር ግን ወደ ወቅታዊ ሁኔታው መሻገር አለብኝ::
ሰሞኑን እርሱ የይቅርታ ሰነድ ሞልቶ ከእስር መፈታቱን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያው መንደር የተቀሰቀሰው ክርክር እጅግ የሰላ ሆኗል። ጉዳዩ የግለሰብ ነጻነት ብቻ ሳይሆን የሞራል፣ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ሕግ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፍልስፍና ፍጥጫ ሆኖ አደባባይ ወጥቷል። በሁለቱም ወገን የተሰለፉትን ሙግቶች መፈተሽ ለፖለቲካ ብስለት ወሳኝ ነው።
፩. የማኅበራዊ ሚዲያው ተቃውሞ እና የትችት መነሻዎች
የክርስቲያን ታደለን ውሳኔ አጥብቀው የሚተቹ ወገኖች የሚያነሷቸው መከራከሪያዎች በዋናነት በሞራልና በክስ መዝገቡ ይዘት ላይ ያተኮሩ ናቸው፦
• የወንጀልና የሽብር ኃላፊነትን የመቀበል አጣብቂኝ፦ የይቅርታ መጠየቂያ ሰነዱ ቀላል የወረቀት ጉዳይ ሳይሆን፣ በመንግሥት የቀረበውን የሽብርተኝነትና የወንጀል ክስ አምኖ መቀበልን፣ ለጠፋው የሰው ሕይወትና ለወደመው ንብረት ጭምር ኃላፊነት መውሰድን የሚጠይቅ ይዘት አለው። ተቺዎች “ይህንን ሰነድ መፈረም አገዛዙ በሕዝቡ ትግል ላይ የለጠፈውን የሽብር ታርጋ ሕጋዊነት ማላበስ ነው፤ ታጋዩንና የትግሉን አጋሮች ወንጀለኛ አድርጎ ማሳየት ነው” በሚል ይሞግታሉ።
• የእስረኞች አንድነትና “የክህደት“ ስሜት፦ አብረዋቸው የታሰሩ ሌሎች የፖለቲካና የሕሊና እስረኞች “ባልሰራነው ወንጀል ፊርማችንን አንሰጥም” በሚል ሰነዱን ሳይፈርሙ በእስር ቤት ጽናትን እየመረጡ ባለበት ወቅት፣ የአመራር ቁመና ያለው ሰው አስቀድሞ ፈርሞ መውጣቱ የተጋድሎ ጓዶቹን ብቻቸውን እንደ መተውና አደራን እንደ ማጉደል ተቆጥሮበታል፡፡
• ለገዢው ሥርዓት የተሰጠ የፕሮፓጋንዳ ስጦታ፦ መንግሥት ይህንን ፊርማ በመጠቀም “ጥፋተኛ መሆናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው አምነዋል” የሚል የፖለቲካ ድል እንዲያውጅ በር መክፈት ነው የሚል ብርቱ ትችት ይሰነዘራል።
፪. ተጨባጭ ፖለቲካ (Realpolitik) እና የታሪክ አውድ
እነዚህን ትችቶች ከፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታና ከተግባራዊ ትግል አንጻር ስንፈትሻቸው መሠረታዊ ክፍተቶች ይታዩባቸዋል፦
ሀ. ፖለቲካ ምድራዊ እንጂ የጽድቅ መንገድ አይደለም
የኢትዮጵያ ፖለቲካ መደበኛ ባልሆነ ምኅዳር ውስጥ ተዘፍቆ፣ በሴራና በተንኮል በሚነዱ ኃይሎች እየተናጠ ባለበት ወቅት፣ ያለ ፍርድ የታሰረን የፖለቲካ ሰው ለ”Political Correctness” ወይም ለፍጹም ፖለቲካዊ ንጽሕና እንዲጨነቅ መጠበቅ የፖለቲካ የዋህነት (political naivety) ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ራስን ማጥፋት (political suicide) ነው።
የአማራ ፖለቲካ አንዱ ትልቁ ማጥ ሃሳባዊነት (Idealism) እና ፖለቲካን እንደ ሃይማኖት ዶግማቲክ በሆነ መንገድ የመረዳት አባዜ ነው። ፖለቲካ በ Realpolitik—በተጨባጭ ነባራዊ ኩነት እና በኃይል ሚዛን ላይ ተመስርቶ ነገን እና ዛሬን የመወሰኛ ጥበብ እንጂ ግትር ሰማያዊ እሳቤ አይደለም። በተጨባጭ ዓለም ውስጥ “ንጹሕ ፖለቲካ” (Political Purity) የለም፤ በጥቁርና በነጭ ብቻ ለመመዘን መሞከር የፖለቲካ ድንቁርና ነው።
ወደ ፖለቲካ የገባነው ለጽድቅ የሚመስለው ብዙ ሰው አለ። አይደለም፤ ፖለቲካ ፈጽሞ ምድራዊ ነው። ዓላማህን ሳትቀይር ስልትህን እየቀያየርክ የሕዝብህን መብት፣ ፍላጎትና ጥቅም ለማስጠበቅ የምትሠራበት ሜዳ እንጂ ከዚህ ዓለም ባሻገር የምታተርፈው ሰማያዊ አክሊል የለም።
ለ. ታሪክ እና የአማራ ሕዝብ ነባራዊ አውድ
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የሚያስተምረን ትልቁ ቁምነገር ግትርነት ሳይሆን ስልታዊ ብልጠት (Strategic Flexibility) ህልውናን እንደሚያተርፍ ነው። የዐፄ ምኒልክ የውጭና የውስጥ ዲፕሎማሲ የሚያሳየው፣ ጊዜያዊ ማፈግፈግ ወይም ስምምነት የትልቅ ድል አካል መሆኑን ነው። በተቃራኒው በ1960ዎቹ የተነሳው ትውልድ ትልቁ ውድቀት “ፍጹም ንጽሕና ካልሆነ አንቀበልም” የሚለው ግትርነትና ያመጣው የርስበርስ መበላላት ነበር።
በተለይ ዛሬ የአማራ ሕዝብ ካለበት ዘርፈ ብዙ የህልውና አደጋ፣ መፈናቀል፣ ጦርነትና የመሪ እጦት አንጻር ሲታይ፣ እያንዳንዱ ህያው ድምፅና አቅም ያለው የፖለቲካ መሪ ለነገው ተስፋ ወሳኝ ነው። የአማራ ትግል ስሜታዊ ሰማዕትነትን ሳይሆን፣ በሕይወት ኖረው ሕዝብን የሚያስተባብሩ፣ በፖለቲካው ማዕድ ድምፅ የሚሆኑ ብልህ መሪዎችን ይፈልጋል። በግዞት ቤት ውስጥ በማቀቅ የሚባክን አቅም ለሕዝቡ የሚፈይደው ምንም ነገር የለም።
ሐ. የሶፋ ላይ አርበኞች (Armchair Critics) ግብዝነት
ከመከራውና ከእስር ቤቱ ግድግዳ ርቆ፣ በምቾት ዓለም ውስጥ ተቀምጦ የሌላውን ሰው ሕይወትና መስዋዕትነት በ”ፖለቲካል ፒዩሪቲ” መለኪያ መመዘን በራሱ ከፍተኛ የሞራል ዝቅጠት ነው። አንድ የፖለቲካ ታጋይ ነጻ ሲሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በእስር ቤት ውስጥ ከሚከፍለው ዋጋ በእጅጉ ይበልጣል። የሞተ ወይም በእስር ማቆያ ውስጥ የዛለ ሰማዕት ለሕዝቡም ሆነ ለትግሉ የሚፈይደው አንዳች ፋይዳ የለም።
፫. የይቅርታ ሰነዱ ሕጋዊ ዋጋ ማጣት፦ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ ሕግ ሚዛን
ክርስቲያን ታደለ በፍርድ ሂደት ጥፋተኛ ተብሎ የተፈረደበት እስረኛ ሳይሆን፣ ያለ ተገቢ የፍርድ ሂደት የታሰረ የሕሊና እስረኛ ነው። በመሆኑም በግዞት ወቅት የፈረመው ሰነድ በሕግ ዓይን ፍጹም ውድቅና ዋጋ ቢስ ነው፤ ይኸውም በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች በግልጽ ተደግፏል፦
• የኢፌዲሪ ሕገ–መንግሥት ድንጋጌዎች (አንቀጽ 19 እና 20)፦ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 20(3) እና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሠረት፣ ማንኛውም ተከሳሽ ጥፋተኛነቱ በፍርድ ቤት በማያዳግም ማስረጃ እስካልተረጋገጠ ድረስ እንደ ንጹሕ የመገመት መብት (Presumption of Innocence) አለው። በተጨማሪም በአንቀጽ 19(5) መሠረት ማንኛውም ተጠርጣሪ በማስገደድ፣ በማስፈራራት ወይም በከባድ ጫና ውስጥ እንዲያምን የተደረገ ቃል በማስረጃነት ተቀባይነት እንደሌለው (Inadmissibility of Coerced Confessions) በግልጽ ተደንግጓል።
• የፍትሐብሔር ሕጉ የነጻ ፈቃድ መርህ (Duress – አንቀጽ 1706)፦ በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 1706 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሠረት፣ አንድ ስምምነት ወይም ፊርማ አስገዳጅ ሕጋዊ ዋጋ የሚኖረው በነጻ ፈቃድ (free will) ሲከናወን ብቻ ነው። ነጻነቱን በተነጠቀ፣ በእስርና በከባድ የስነ-ልቦና ጫና ውስጥ (under duress) ባለ ሰው የተሰጠ ማንኛውም ይሁንታ፣ ፈቃድ ወይም የተፈረመ ሰነድ በሕግ ፊት ፈራሽ (null and void) ነው።
• ዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR – አንቀጽ 14(3)(g))፦ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው ይኸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌ፣ ማንኛውም የተከሰሰ ሰው በራሱ ላይ ምስክር እንዲሆን ወይም ጥፋተኛ ነኝ ብሎ እንዲያምን ሊገደድ እንደማይችል (right not to be compelled to confess guilt) ያስቀምጣል። የሥርዓቱ ይቅርታ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓትም ቢሆን (በይቅርታ አሰጣጥ አዋጅ ቁጥር 840/2006 መሠረት)፣ ይቅርታ የሚጠየቀው ጥፋተኝነቱ በፍርድ ቤት በይፋ በተረጋገጠ ሰው ላይ እንጂ፣ ፍርድ ሳይሰጥበት በፖለቲካ ውሳኔ የታሰረን ሰው “ጥፋትህን እመን” ብሎ ማስፈረም በራሱ የሕጉን መንፈስ የሚቃረን የፖለቲካ ቁማር (political expediency) ነው።
በተጨማሪም የፍትሕ ሥርዓት በሌለበት ምኅዳር ውስጥ በጠላት ጫና የተፈረመን ወረቀት እንደ እውነተኛ የጥፋተኝነት ማስረጃና የሞራል መለኪያ አድርጎ መውሰድ የሕግ መርሆችን ካለመረዳት የሚመነጭ የፖለቲካ የዋህነት ነው።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ፣ የክርስቲያን ታደለ ከእስር መውጣት በስሜታዊነትና በግብዝነት በሚሰላ የ”ፖለቲካዊ ንጽሕና” መነጽር የሚታይ ሳይሆን፣ በህልውና ትግል ውስጥ እንደተገኘ ስልታዊ ድል ሊወሰድ ይገባል። ፖለቲካ በሕያው ሰዎች መካከል የሚደረግ የተጨባጭ ጥቅም እና የኃይል ሽኩቻ እንጂ የሰማዕታት ሙዚየም ማደራጃ አይደለም።
የአማራ ሕዝብ ዛሬ ካለበት ዘርፈ ብዙ ቀውስና የህልውና አደጋ ለመውጣት የሚታደገው በእስር ቤት ውስጥ ማቀቀው የተረሱ ሳይሆን፣ በአካል ነጻ ሆነው አደባባይ ላይ የሚሞግቱ፣ የሚያስተባብሩና የሚመሩ ብልህ ታጋዮች ናቸው። ክርስቲያን የወሰደው ውሳኔ ዓላማውን የሸጠበት ሳይሆን፣ ለቀጣዩ የትግል ምዕራፍ ራሱን ወደ ሜዳው የመለሰበት የብስለት ውሳኔ ነው። የታሪክ ዳኝነትም የሚለካው በጠላት ጫና በተፈረመ ጊዜያዊ ሰነድ ሳይሆን፣ ወደፊት በሚመዘገበው ተጨባጭ የትግል ውጤት ይሆናል።
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena







Well, whatever the case, the decision to take responsibility and accountability for something that is absolutely wrong is the right of any individual . Yes, if a person who involved in the right way of fighting back the evil- driven ruling elites becomes frustrated and cowardly for any reason he or she may have and lose all values of what he or she used to be and bowed down to those ruling crooks , that is a complete dead alive!!!
He or she becomes a very bad example of a generation that was supposedly expected to make itself free by fighting back the brutal regime!
Multiplying one’s positive contribution earlier by zero will not be any thing + but zero! That is a very hard reality !