Homeመጣጥፍየኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ገድል በአፍሪካ/ኮንጎን በወፍ በረር!!

የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ገድል በአፍሪካ/ኮንጎን በወፍ በረር!!

Advertisement
World Wide Travel Group

(ይህ ጽሑፍ ማስታወሻነቱ፡- በተባበሩት መንግሥታት የኮንጎ ሰላም አስከባሪ የጦር አባል ለነበሩት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች፤ ለጀግናው ለኮ/ል ካሣ ገ/ማርያም፤ ለኮ/ል መንገሻ ወ/ኪዳን፣ ለ5ቱ ዓመት አርበኛና የኮንጎ ዘማች ለመ/አ/ ወርቁ ደስታ እና በሕክምና ሙያ ዘርፍ ዘማች ለነበረችው ለሻምበል ሲስተር አስቴር አያና ይሁንልኝ፤)

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)፤

  1. እንደ መንደርደሪያ፤

ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ተቋም/Addis Ababa University Institute of Peace and Security ዳይሬክተር፣ ‹‹Africa in the Global Security Governance: A Critical Analysis of Ethiopia’s Role in the UN Peacekeeping Operations›› በሚል ርእስ እ.አ.አ. በ 2018 ባስነበቡት ጥናታዊ ጽሑፋቸው፤

‹‹… የተባበሩት መንግሥታት እ.አ.አ ከ 1948 እስከ 2013 በዓለም ዙሪያ 67 የሰላም ማስከበር ዘመቻዎችን ማካሄዱን በመጥቀስ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚህ የሰላም ማስከበር ተልእኮ እ.አ.አ ከ 1950ዎቹ እስከ 2017 በ 12ቱ ተልእኮዎች ውስጥ መሳተፏንና በአጠቃላይም እ.አ.አ. እስከ 2017 ድረስ 90 ሺሕ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮችም በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ዘመቻ በመሳተፍ አኩሪ የጀግንነት ገድል መፈጸማቸውን…፤›› በዚሁ ለሕትመት በበቃው ጥናታዊ ወረቀታቸው ጽፈዋል፡፡

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የታሪክ መዛግብት እንደሚጠቁሙት፤ ኢትዮጵያ በዓለማችን ሰላም እንዲሰፍን- ከባለ ቃል-ኪዳን አገሮች ማኅበር/League of Nations እስከ ተባበሩት መንግሥታት/United Nations መቋቋም ድረስ ብቸኛ አፍሪካዊትና የጥቁር ሕዝቦች ተወካይ በመሆን ደማቅ የሆነ አሻራዋን አኑራለች፡፡ የአፍሪካ ሕዝቦች ሰላም፣ አንድነትና የወንድማማችነት እንዲሰፍን- የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን/Organization of African Union፣ የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረትን/African Union በማቋቋም ግንባር ቀደሙንና ትልቁን ሚና የተጫወተች ባለ ታላቅ ታሪክ አገር ናት፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ከሰሜን አሜሪካ እስከ ካረቢያና ጃማይካ፣ ከኮሪያ ልሣነ ምድር እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኮትዲቯር፣ በብሩንዲ፣ በሩዋንዳና በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በሰላም አስከባሪነት ጀግና ልጆቿን በመላክ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም አገራት ሁሉ ትልቅ ባለውለታ ናት፡፡

ከዚህ የታሪክ እውነታ ጋር ተያይዞም የተባበሩት መንግሥታት እ.ኤ.አ. በ 2020 ባወጣው መረጃ መሠረትም፤ የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ- በአፍሪካና በመላው ዓለም ባደረገችውና አሁንም እያደረገችው ባለው ‘የሰላም አስከባሪነት’ የጎላ ተሣትፎዋ ምክንያት- በአፍሪካ ‘የአንደኝነትን’፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ‘በሁለተኛነት’ ደረጃ እንደሚያስቀምጣት እንዲህ ሲል የሚከተለውን ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር፤

Besides being a seat to various International Nongovernment Organizations (NGOs) and Diplomatic Seats, Ethiopia is the Political Capital City of Africa. This ancient state has been wholeheartedly and constructively contributing to world peace and stability in line with the principles and missions of the UN so that the world could enjoy peaceful coexistence. Evidently, it is number one in Africa and the Second largest Peace Keeping Force producer in the world.

- Advertisement -
Advertise here _ borkena
  1. የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በኮንጎ/ዛየር፤

የኮንጎ ሪፐብሊክ መንግሥት እንደ እ.አ.አ. በ1960 ከቤልጂየም የቅኝ ግዛት ተላቆ ነጻነቱን ቢጎናጸፍም ሀገሪቱ ባላት ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ምክንያት ጨርሰው ነጻ ሊለቋት ያልፈለጉት የቅኝ ገዢዎች ሌላ ስትራቴጂ ቀየሱ፡፡ ይኸውም፤ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ የእርስ በርስ የጎሳ ግጭትና በመከፋፈል ካታንጋን ለመገንጠል በቤልጅግ መንግሥት የሚደገፉ የተደራጁ ኃይሎች ሀገሪቷን ወደ እርስ በርስ ጦርነት አፋፍ ላይ ጥለዋት ነበር፡፡

በወቅቱም የነበረው የኮንጎ መንግሥት የአመራር ማእከልም ተጓድሎ ስለነበር ይህን የፀጥታ ችግር ለማስተካከል የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ሚ/ር ዳግ ሐመርሾልድ ሁኔታውን ለሴኩሪቲ ካውንስል አባላት አሳወቁ፡፡ የፀጥታው ምክር ቤትም በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ኮንጎ የሰላም አስካባሪ ጦር እንዲላክ ተወሰነ፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ስር በመሆን የኢትዮጵያ የሰላም አስካበሪ ጦር የመጀመሪያው ተልእኮው በሆነው በኮሪያ የሰላም ማስከበር ዘመቻው በፈጸመው አስደናቂ የጀግንነት ገድል የተነሳ፤ በተባበሩት መንግሥታት በኩል በኮንጎ የሰላም ማስከበር ዘመቻ- ሀገራችን ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ኮንጎ እንድትልክ ተጠየቀች፡፡ በወቅቱም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የተባበሩት መንግሥታት ለኮንጎ ሰላም ማስከበር ተልእኮ በጠቅል ሻለቃ የተሰየመውን 4 ብርጌድ ጦር እና አራት የአየር ኃይል እስኳድሮን በአራት ዙር ወደ ኮንጎ ለመላክ ተስማማች፡፡

የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ ፖለቲካ የወታደራዊ ሥልጠና በመስጠት፤ የአፍሪካ ሀገራትን የነጻነት ትግልን በሞራል፣ በገንዘብና በሐሳብ የደገፈችው ሀገራችን ኢትዮጵያ-  በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት ‹ለኮንጎ የሰላም ማስከበር ተልእኮ› ግብዣ ሲቀርብላት የሁኔታው አሳሳቢነትና አጣዳፊነት ግንዛቤ ውስጥ በመክተት በአቋማቸው፣ በወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት ብስለታቸውና ሥነ-ሥርዓታቸው የተመሰገኑ ወታደሮችን በአምስት ቀን ውስጥ መርጣ ላከች፡፡

- Advertisement -

የኮንጎ ሰላም አስካበሪ በመሆን ወደ ኮንጎ ከዘመቱት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መካከል የሆኑት፤ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን- ብ/ጄ ውበቱ ጸጋዬ ጋር በአንድ ወቅት በነበረን ቆይታ ስለ ኮንጎ ዘመቻ ካወጉኝ ትዝታቸው በጥቂት ለመቀንጨብ ወደድኹ፤ 

ወደ ኮንጎ/ዛየር የተላከው ዘማች ጦር የተመረጠው ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪቃ፣ ከአውሮፓና ከእስያ አኅጉር ነበር፡፡ የምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያም ኢትዮጵያ የምትልከውን ለማዘጋጀት ኃላፊነት ስላለበት የጦሩን አስተዋፅዖ ለመላክ ያተኮረው በሁለት ዕውቅ ብርጌዶች ማለትም በ2ኛው እና በ3ኛው እግረኛ ብርጌድ ላይ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ብርጌዶች በአዲስ አበባና በደብረ ብርሃን አካባቢ ስለነበሩ ምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ በሥልጠናና ድርጅት በኩል ቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ስለሚያደርግላቸው የሰራዊቱ ሥልጠናና የሥነ-ሥርዓት ይዘት ከፍተኛ ነው፡፡

የምርጫው ቀደምትነት ለእነዚህ ብርጌዶች የተሰጠው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ በተለይም ብርጌዶችንና ሻለቆችን እንዲሁም እስከ መቶ መሪ ድረስ አመራር በመስጠት ተመድበው የሚገኙት መኮንኖች በአገር ውስጥ፣ በፈረንሳይ፣ በአሜሪካና በእንግሊዝ ሀገራት ከፍተኛ ሥልጠና የወሰዱና ልምድ ያካበቱ ዘመናዊ የጦር መኮንኖች ናቸው፡፡ እኔም በአዲስ አበባ በሚገኘው 2ኛ እግረኛ ብርጌድ ውስጥ ስለነበርኩ ወደ ዛየር/ኮንጎ ወደ ሚላከው ጦር የ3ኛ ሻምበል 3ኛ የመቶ መሪ በመሆን እንደምሠራና ለተልክኦ እንደምነቃነቅ በምድር ጦር ዘመቻ መኮንን በሌ/ጄ ኃይሌ ባይከዳኝ በኩል ተገለጸልኝ፡፡

ለዚህ የተቀደሰና ዓለም አቀፍ ግዳጅ በመመረጤ ሞራሌ ከፍተኛ ነበር፡፡ በእንዲህ ያለ ዓለም አቀፍ ግዳጅ ጊዜ ጦሩን በአካል እየተገኙ የሚያበረታቱትና አሸኛኘት የሚያደርጉት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የሰጡን የማበረታቻ ንግግር በጥቂቱ እንዲህ ያስታውታል ጄ/ል ውበቱ፤

‹‹… በአፍሪካ ክፍ ዓለማችን የምትገኘው የኮንጎ ሪፐብሊክ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ነጻነትዋን ባከበረችበት ጊዜ የደስታዋ ተካፋዮች ሆነን መልእክተኞቻችንን በኮንጎ ዋና ከተማ ሊዎፓልድቪል እንዲገኙ አድርገን ነበር፤ በዚያን ጊዜ ደስታችን የበዛውን ያህል አሁን በኮንጎ ሰላም መድፍረሱ አሳዝኖናል፡፡ ወደ ኮንጎ ሰላም ለማስከበር የምንልካችሁ ይህ ሰራዊት ግዳጁን በሚፈጽምበት ጊዜ ብቃት ያለውና ምሳሌ መሆን የሚችል ወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት ማሳየት ወይም መላበስ እንዳለበትና እንደ ኮሪያው ሁሉ ሀገራችንን በሁለተናው የሚያኮራ መልካም ስም ይዞ እንዲመለስ ያስፈልጋል፤››

በጠቅል ብርጌድ ስም የተሰየመው የኢትዮጵያ ጦር ለሰላም ማስከበር ተልእኮ ወደ ኮንጎ ሲዘምት፤ በኮሪያ ልሣነ-ምድር በሰላም ማስከበር ተልእኮው የተሰጠውን ግዳጅ በታላቅ ኃላፊት፣ ጀግንነትና ወታደራዊ ዲስፕሊን ፈጽሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ ስምና ዝናን የተጎናጸፈው የኢትዮጵያ ጦር በአፍሪካ ቆይታውም ይህንኑ ገድሉን እንዲደግመወው ነበር ከንጉሠ ነገሥቱና ከእናት ሀገሩ ታላቅ የሆነ ሕዝባዊ አደራን ተርኮቦ ወደ ኮንጎ የዘመተው፡፡

የኢትዮጵያ ሰላም አስካበሪ ጦር በሌላ 2ኛ ዙር ዘመቻ ሁለት የክብር ዘበኛና ሁለት የጦር ሰራዊት በአጠቃላይ 4 ሻለቆች ወደ ኮንጎ/ዛየር ተልከዋል፡፡ በጥቅል ስማቸውም 1ኛ ጠቅል ብርጌድ ተብለው ተሰየሙ፡፡ ብርጌዱ በኮ/ል ወ/ዮሐንስ ሽታ (በኋላ ብ/ጄነራል) ሲታዘዝ የበላይ አስተባባሪው ደግሞ ሌ/ጄኔራል ኢያሱ መንገሻ ነበሩ፡፡ ብርጌዱንም በዘመቻ መኮንንነት ተመድበው ይመሩ የነበሩት ደግሞ ሜ/ጄኔራል ግዛው በላይነህ ነበሩ፡፡

በአጠቃላይ በኮንጎ ጦርነቱ ተጀምሮ እስካበቃ ድረስ ለተባበሩት መንግሥታት ድ/ት ጦር ኃይል የተመደቡ አዛዦች 5 ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያዊው ጄ/ል ከበደ ገብሬ ነበሩ፡፡ ጄ/ል ከበደ ከሌሎቹ አዛዦች ሁሉ ለረጅም ወራት- ለ16 ወራት ያህል የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ጦርን በብቃት የመሩ፤ ምስጉን ኢትዮጵያዊ ጀግና ነበሩ፡፡

በኮንጎ ሰላም ማስከበር ተልእኮ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 12 ሺሕ መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረጎችን ወደ ኮንጎ አዝምታለች፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 24 መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረጎች ሕይወታቸውን ሲያጡ 33 መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረጎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት/የሴኩሪቲ ካውንስል ሰነዶች እንደሚጠቁሙትም፤ በኮንጎ ሰላም ማስከበር ዘመቻ ወታደሮችን ከላኩ 21 ሀገራት ውስጥ 127 መኮንኖችና ወታደሮች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በልዩ ልዩ ምክንያትና ባልታወቁ አደጋዎች 74 መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረጎች ሲሞቱ 133 ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በዚህች አገር ሰላም መታወክ ምክንያትም የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የነበሩትን ሚስተር ዳግ ሐመርሾልድን የሚያህል ታላቅ ሰው የመንግሥታት ማኅበሩ አጥቷል፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት እ.አ.አ ከ1960 እስከ 1964 በኮንጎ/ዛየር ለፀጥታ/ለሰላም ማስከበር ሥራም 290 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንዳደረገ ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡

በኮንጎ ዘመቻ ከተሳተፉ ታላላቅ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን መኮንኖች መካከል ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህልም፤

  1. ብርጋዴር ጄኔራል ካሣ ወ/ሰማዕት፤ ከፍተኛ ወታደራዊ ትምህርታቸውን በሀገር ውስጥ፣ በሩሲያና በአሜሪካ ሚሊታሪ አካዳሚ የተከታተሉት ጄኔራል ካሣ ወደ ኮንጎ በዘመቱበት ወቅት መ/አ ነበሩ፡፡ የ4ኛው ጠቅል ሻለቃ አባል የሆኑት ካሣ ወ/ሰማዕት፤ በኮንጎ ሰላም ማስከበር ተልእኮ እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ የሰጠቻቸውን አደራና አኩሪ የጀግንነት ገድል የፈጸሙ መኮንን ናቸው፡፡ እኚህ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን፣ ብርጋዴር ጄኔራል ካሣ ወ/ሰማዕት በኮንጎ የሰላም ማስከበር ዘመቻን የተመለከተም፤ ‹‹በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በኮንጎ እና የሕይወቴ ጉዞ (Operation Barakuda)›› የሚል ታሪካዊ የሆነ መጽሐፍን አበርክተውልናል፡፡
  1. ኮሎኔል ካሣ ገ/ማርያም፤ እህኚ ኢትዮጵያዊ ጀግና በተባበሩት መንግሥታት የ4ኛ ጠቅል ብርጌድ ዘመቻ መኮንን በመሆን የብርጌዱን ቀዳሚ መምሪያ ይዘው ካታንጋ ከገቡ በኋላ ብርጌዱ ተጠቃሎ ኮንጎ እስኪሚገባ ድረስ በ3ኛ ጠቅል ብርጌድ መምሪያ በኃላፊነት ሲሠሩ የቆዩ መኮንን ነበሩ፡፡ መኮንኑ በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት፣ በሐረር የጦር አካዳሚ፣ በውጭ ሀገር በአሜሪካ፣ በዩጎዝላቪያ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በአዛዥነት፣ በሐረር የጦር አካዳሚ ደግሞ በአስተማሪነት፣ በበረራ ድኅንነት ሙያና በተለያዩ ወታደራዊ ግዳጆች ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ልጃቸው ዶ/ር ስንታየሁ ካሣ፤ ‹‹ታሪክ የምትመሰክርልን፤ ካሣ ገ/ማርያም›› በሚል አርእስት የጀግና አባታቸውን የሕይወት ታሪክ በሰፊው ጽፈውልናል፡፡
  1. ኮ/ል መንገሻ ወ/ኪዳን፤ የሐረር ጦር አካዳሚ ምሩቅ የሆኑት ጀግናው ኢትዮጵያዊ መኮንን፣ ኮ/ል መንገሻ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር የ3ኛው ጠቅል ብርጌድ አባል ሲሆኑ፣ ይህን ጦር በአዛዥነት ሲመሩ የነበሩት ደግሞ ኮ/ል በኋላ ሜጀር ጄኔራል የሆኑት ጄኔራል ወርቁ መታፈሪያ ነበሩ፡፡

ኮ/ል መንገሻ ወ/ኪዳን በኮንጎ ካታንጋ በነበራቸው የሰላም ማስከበር ተልእኮቸውም ከሌሎች ጀግኖች ኢትዮጵያውያን መኮንኖች ጋር በመሆን አኩሪ የጀግንነት ገድል የፈጸሙ ናቸው፡፡ ለዚህ የጀግንነት ገድላቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት የሙሉ ኮሎኔልነት ማዕረግ፣ ሜዳሊያ፣ ከአፍሪካ አንድነት ድ/ት እና ከተባበሩት መንግሥታት ደግሞ የክብር ኒሻንና ሜዳሊያን ተቀብለዋል፡፡ በሀገር ውስጥም በአስመራ፣ በባሌ፣ በኦጋዴን፣ በነገሌ ቦረና፣ በምድር ጦር በአዛዥንትና በተለያዩ ሀገራዊ ግዳጆች ሀገራቸውን በጀግንነትና በቅንነት አገልግለዋል፡፡ 

  1. ሻምበል ሲስተር አስቴር አያና፤ በኮንጎ ሰላም ማስከበር ተልእኮ አስደናቂ የጀግንነትና የሰብአዊነት ተግባርን የፈጸመች ጀግና ሐኪም ናት፡፡ ሲስተር አስቴር ቀደም ሲልም ከ1ኛው ቃኘው ሻለቃ ጋር ወደ ኮሪያ ዘምታ ነበር፡፡ ሻምበል ሲ/ር አስቴር በኮንጎ ለፈጸመችው ታላቅ የሰብአዊነት ተግባርና የጀግንነት ሥራዋ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ መንግሥት ዘንድ ሹመትና ሽልማት አግኝታለች፤ ከአፍሪካ አንድነት ድ/ት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሚዲሊያና የክብር ኒሻኖችን ተሸልማለች፡፡
  1. መ/አ ወርቁ ደስታ፤ ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ሀገራችንን በግፍ የወረረውን የፋሽስት ኢጣሊያ ጦርነት በመፋለም፣ በጎንደር (በሊቦ፣ ከምከም፣ በለሳና አርማጭሆ) አኩሪ የጀግንነት ገድልን የፈጸሙት አርበኛ ናቸው፡፡ የሆለታ ገነት ጦር ት/ቤት ምሩቅ የሆኑት መ/አ ወርቁ ደስታ በተባበሩት መንግሥታት የኮንጎ ሰላም አስከባሪ በመሆን የ4ኛው ጠቅል ብርጌድ አባል በመሆን በሰላም አስከባሪነት ዘመተዋል፡፡

በኮንጎ ሰላም ማስከበር ለፈጸሙት የጀግንነት ገድልም ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከአፍሪካ አንድነት ድ/ት እና ከተባበሩት መንግሥታት የክብር ኒሻንና ሜዲሊያን አግኝተዋል፡፡ በሀገር ውስጥም በኤርትራ (በምፅዋ፣ በአሰብ፣ በአቁርደት፣ ተሰነይ፣ ባሬንቱ)፣ በኦጋዴንና በቦረና ወታደራዊ ግዳጀቸውን የፈጸሙ አርበኛና ወታደራዊ መኮንን ነበሩ፡፡

3. እንደ ማጠቃለያ፤

የኢትዮጵያ ሰላም አስካበሪ ሰራዊት በዓለም አቀፍ ደረጃና በአፍሪካ ሰላም ማስከበር የፈጸመውን የተሳካ ተልእኮውንና ያስመዘገበውን ስኬት አስመልክቶ ኮንጎን እንደ መነሻ በማድረግ በወፍ በረር የጀግኖቻችንን ታሪክ በጣም፣ በጣም በጥቂቱ ለማንሳት ሞክሬያለሁ፡፡ በዚህ አጭር ጊዜና ውስን ገጽ የጀግኖቻችን ገድል መተረክ የሚሞከር አይደለም፡፡ ከኮሪያ ልሣነ-ምድር እስከ አፍሪካ በርካታ ሀገራት (ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ሱዳን፣ ላይቤሪያ፣ ኮትዲቯር፣ ቻድ፣ ሶማሊያ) ድረስ በሰላም ማስከበር ዘመቻ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ክብር፣ ስምና ዝና ያለው የጦር ኃይል ያለን ሀገር ነን፡፡

ጽሑፌን ለማጠናቀቅ ያህል፤ ከወራት በፊት የአውሮፓ የሳይንስ ጆርናል (Europe Scientific Journal/ESJ)፤ የኢፌዲሪ War College ኮሌጅ ባልደረባ ካሌብ ሥጋቱ፤ ‹‹Unveiling the Dynamics of Ethiopian Defence Diplomacy: A Focus on Peacekeeping Contributions›› በሚል አርእስት የጻፉትን አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አስነብቦ ነበር፡፡

ካሌብ ሥጋቱ በ‹አውሮፓ የሳይንስ ጆርናል› ላይ ባሳተሙት በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸው፤ ‹‹በከኮሪያ ልሳነ-ምድር የተጀመረው የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልእኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስካበሪ ጦር በኮንጎ የተጀመረውና በሶማሊያ፣ በሱዳንና በዳርፉር በነበረውና አሁንም በቀጠለው የሰላም ማስከበር ተልእኮ ለሀገራቱና ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት የነበረውና ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያሰምሩበታል፤

እንዲሁም የኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ጦር በመላክ በአፍሪካ ኅብረት/AU ቀዳሚውን ስፍራ ስትይዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በUN ደግሞ ሁለተኛዋ ሀገር መሆኗን በጥናታዊ ጽሑፋቸው እንደሚከተለው አጋርተውታል፤

In our sub-region, the deployment of Ethiopian troops in Darfur, Abyei, and Somalia has made a significant contribution to the maintenance of regional peace, security, and stability. … Ethiopia is the second-largest troop-contributing country to UN peacekeeping missions. If we add to this our involvement in African Union peacekeeping missions, we will find that Ethiopia is the largest contributor of peacekeeping troops in the world.

ትናንትናም ሆነ ዛሬ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ግዳጅ- ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን በተሰማሩበት ሀገራት ሁሉ የሰላም አምባሳደርነታቸውን በአኩሪ የጀግንነት ገድል ለማስመስከር መቻላቸውን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ይህ ከአኅጉረ አፍሪካ፤ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ ተሻግሮ በኮሪያ፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ ድረስ ከፍ ያለ ‘‘የሰላም ማስከበር’’ አኩሪ የታሪክ አሻራ እንዲኖረን ያደረጉ ጀግኖቻችን ደግሞ የሚገባው ዕውቅና እና ክብር ሊቸራቸው ይገባል፡፡

በዚህ ረገድም፤ የመከላከያ ሚ/ር እነዚህ በሀገር ውስጥ እና በውጪ (በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ) የጀግንነት ገድል የፈጸሙና ለሰው ልጆች ሰላም ሕይወታቸውን የከፈሉ፤ ታሪካቸውን በደማቸው ለጻፉ ጀግኖች መታሰቢያ የሚሆን፣ ትውልድ ታሪካቸውንና የጀግንነት ገድላቸውን የሚማርበት ቤተ-መዘከር/ሙዚየም ለመገንባት በእንስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ የእነዚህ ጀግኖቻችን አኩሪ ታሪክና ቅርሶቻቸው በአንድነት በክብር ተቀምጠው የምናይበት ቤተ-መዘክር/ሙዚየም ተገንብቶ፤ ተጠናቆ ለማየት የብዙዎች ኢትዮጵያውያን ናፍቆትና ጉጉትም ነው፡፡

ሰላም!

ሰላም ለኢትዮጵያ!! 

__

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

2 COMMENTS

  1. ሀገራችን ኢትዮጵያ፡ በአፍሪካና መላው ዓለም አገራት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በ1960 በሰላም አስከባሪነት በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት “ለኮንጎ የሰላም ማስከበር ተልእኮዕ” ከላከቻቸው ጀግና ልጆቿ መካከል የኔ አባት መጋቢ ፶ አለቃ ተፈራ ተገኝ አንዱ ነበር። የእነዚያ በሀገር ውስጥ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጀግንነት ገድል የፈጸሙና ለሰው ልጆች ሰላም ሕይወታቸውን የከፈሉ፤ ታሪካቸውን በደማቸው የጻፉ ጀግኖች ልጅ መሆኔ ታላቅ ክብር ይሰማኛል። ይህን ታሪክ ያስነበብከን ተረፈ ወርቁ (ዲ፨ን) አመስግናለሁ።

  2. ወደ ኋላ ተመልሰህ የእውን ጀግኖችን ታሪክ ስላቃመስከን እናመሰግናለን። ውድ ሃገራችን እንደዛሬው የብሄር ወንፊት ሳትሆን ሃይማኖት/ዘርና ጎሳ/ቋንቋ ሳይለያቸው ሁሉም ለሃገርና ለወገን በውጭና በውስጥ ተዋድቀዋል። ያው ሳንጃ ባፈሙዝ ተብሎ መጤውን የቁስ አካል ፍልስፍና ሰው በግድ ከተጋተ በህዋላ የፈረሰውና ያለቀውን ትውልድ ይቁጠረው። የሚያሳዝነው የ 17 ዓመት የመከራ ዘመን የናደውን ወያኔና ሻቢያም ተቀብለው መቀመቅ ማግባታቸው ውድቀታችን መራራ መሆኑን ያሳያል። ለምድሪቱ ሰላምና አንድነት የታገሉት ወገኖች ቤተሰብ ሜዳ ላይ ተጥሎ ገንጣይና አስገንጣይ የፈነጨበት ጊዜን በአርምሞ ለተመለከተ በእውነትም የሞተላት ቀርቶ የገደሏት እንደሚበሉ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
    ይኸው ከዘመናት በህዋላ ደግሞ ቀኑ የኦሮሞ ነው ተብሎ ሰው ሳይፈልግ በግድ ኦሮምኛ ቋንቋ እንዲማር እየተደረገ ነው። ቋንቋ መግባቢያ መሆኑ ቀርቶ የፓለቲካ መሳሪያ እንዲሆን እየተተለመ እንደሆነ አይንና ጀሮ ያለው ይረዳል። በዚህም በዚያም የብሄር ነጻ አውጭ ነን ብለው ከመሸ በህዋላ ነፍጥ ያነሱትም በህዝቡ ውስጥ ተደብቀው በዚህም በዚያም ወገንን በእሳት ያስጠብሳሉ ይጠብሳሉ። ባጭሩ የአሁኑን የአስረሽ ምቺው ፓለቲካ በአንክሮ ለተመለከተው እብደት እንደሆነ ይረዳል። በከተማና በገጠር አዛውንት/ህጻናት/የመንግስት ሰራተኞች ታፍነው ገንዘብ ክፍሎ ያለዚያ ይገደላሉ ይባላል። አፋኙ ማን እንደሆነ ለይቶ ማወቅ አይቻልም። ጥርጣሬው ግን ከመንግስት የጸጥታ ተቋማት እስከ የብሄር ታጣቂዎች አልፎ ተርፎም በየመንደሩና በየጎጡ እንዲሁም በየከተማው በተደራጅ ዘራፊዎች እንደሚሆን ይገመታል። የባንክ ቤት ሰራተኛው የደንበኛውን በባንክ ያለ ገንዘብ ለአፋኞቹ አስቀድሞ ይናገራል… እሱም የቅሚያው ተሳታፊ ነውና። በነገሩ ነቅተው ጉዳዪን ወደ ህዝብ ጀሮ ሊያደርሱ የሞከሩት ደግሞ በቀትር ይገደላሉ። ባጭሩ ሃገሪቱ ህግ የሌለባት ማንም እንደፈለገ የሚፈነጭባት ሆናለች። በዚህ ላይ የወያኔን/የሻቢያን/የፋኖና የኦላን ተንኮል ስናክልበት ህዝባችን ከመከራ ወደ ሌላ የባሰ መከራ እየተሸጋገረ ለመሆኑ መረዳት አያቅትም።
    በቅርቡ የፋኖ ቱልቱላ ስለ መጭው ምርጫ አስመልክቶ ሲናገር “ማንም በዚህ ምርጫ ቢሳተፍ እርምጃ እንወስዳለን” እያለ ሲደነፋ መስማት ከመገረም አልፎ ሱባኤ ያስገባል። ሰው የሚፈልገውን መምረጡ መብቱ እንጂ በዚህም በዚያም የታጠቀ ብቅ እያለ ወዪላችሁ የሚልበት መድረክ ሊሆን አይገባም ነበር። ግን ጊዜው ተጣርሷልና እውነት ተቀብራለች። ነጻነትን የሚያውጀው ለራሱ ነጻ ያልወጣው ነው። ስለ ህዝቦች መብት የሚከራከረው ዘራፊና ደም አፍሳሹ ነው። ግን ሰርቶ ለፍቶ ጥሮና ግሮ ለማደር የማይችለው ዛሬ ገቢው በዝርፊያና በግድያ የሚገኝ ብቻ ነው። ህዝባችን በቀን አንድ ጊዜ በልቶ ቀኑን ለማሳለፍ በሚፍጨረጨርባት ምድር በቢሊዪን የሚቆጠር የሃብት ቁልል ያከማቹ ብዙ ናቸው። ዝርፊያው ጥልቅ ነው። ጉቦው ሚስጢራዊ ነው። ግድያው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት ነው። ፍትህ/ርትዕ ተጓደለ ያሉም ዝም ተደርገዋል። አሁን ከሆነ ደግሞ ውጭ ያላችሁ ስትሞቱም ለመቀበር ወደዚህ አትምጡብን ብለውናል። አይ ጊዜ! አይነጋ መስሏት ደሮ… እንዲሉ ነው። ግራም ነፈሰ ቀኝ የሚሆነውን ከማየት ሌላ በአሁኑ ዓለም ላይ ይህ ነው ተብሎ የሚነገር እውነት እየከሰመ ነው።
    በማጠቃለያው Mark Felton Productions – The Emperor’s Battalion – Ethiopian Troops in Korean war በሚል ርዕስ የለቀቀውን የዪቱቭ ዘገባ ፈልጎ መመልከት ነው። ያኔ አንድ ሆነው በአንድ ተሰልፈው ለሃገራቸውና ለህዝባቸው በጨለማው ሰአት የቆሙ ልጆች እንደነበሯት ሁሉ ዛሬም የተዳፈነ እሳት በየስፍራው አለ። ጊዜ ሁሉንም ቦግ ብሎ እንዲቦገቦግ ያደርገዋል። ጠብቀን እንይ! በቃኝ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News