
በኢዮብ ትኩዬ
“የቴሌ ሲስተም በመጠቀም ከግለሰብ አካውንት 238 ሺሕ ብር የሰረቀች የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኛ ተያዘች” የተባለችው ግለሰብ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሶዶ ከተማ ፓሊስ መምሪያ፣ የቴሌ ሲስተምን በመጠቀም ከግለሰብ አካውንት ብር የሰረቀች የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኛ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላለች ማለቱን ቦርከና ተመልክቷል።
“አቢሲኒያ አዱኛ የተባለችው ይህች ግለሰብ በኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ በኤጀንት አገልግሎት የምትሰራ” ናት ሲሉ የከተማው ፖሊስ መምሪያ የታክቲክ ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ታመነች ባሳ ገልጸዋል።
ቦርከና የተመለከተው ይሄው የፓሊስ ቃል፣ “የአንድን ተበዳይ ሲም ካርድ ዘግታ በማውጣት በቀን 29/11/17 ዓ.ም ከግለሰቡ አካውንት ልትሰርቅ ችላለች” ይላል።
የሶዶ ከተማ ነዋሪ የሆኑት በደል ደረሰብኝ ያሉ ግለሰብ አደረሱት በተባለ ጥቆማ መሰረት ወንጀሉን የተከታተለው የሶዶ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ግለሰቧን ከአዲስ አበባ ከተማ መያዙንም የመምሪያው ዲዢዥን ኃላፊ ተናግረዋል ተብሏል።
የሶዶ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ሀብታሙ አሰፋ በበኩላቸው፣ ማህበረሰቡ በራሱ አካውንት የወንጀል ተግባር ሊፈጸም ስለሚችል የዲጂታልና ኤሌክትሮኒክስ ንብረቶችንም ጭምር ጠንቅቆ መያዝ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የፓሊስ መረጃ ያስረዳል።
ፓሊስ ደረስኩበት ያለው የግለሰቧ ድርጊት ብዙዎችን ከማስቆጣቱም ባሻገር፣ በኢትዮ ቴሌኮም አሰራር ላይ ብርቱ ትችትን ሲያሰነዝር የተስተዋለ ሲሆን፣ ተቋሙ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ጉዳዩን አስመልክቶ ያለው ነገር የለም።
በተያያዘ ዜና፣ የቄራዎች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰይድ እንድሪስ ከማል እና ምክትላቸው አቶ ዮሴፍ ድሪብሳ ማሞ የድርጅቱን አገልግሎት ለማግኘት የሄዱ ተገልጋዮችን “‘ገንዘብ ካላመጣችሁ አገልግሎት አታገኙም’ በማለት ከቆዩ በኋላ ከተገልጋይ ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በቁጥጥር ስር” መዋላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትላንት ማስታወቁ ይታወሳል።
__
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






