
ቦርከና ዜና
በህወሓት እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ያለው ልዩነት ወደ ከረረ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም፣ የፌደራል መንግሥት የፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደን የሥልጣን ዘመን ለብቻው ማራዘሙ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ በመሆኑ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፈርሷል። በዚህም ምክንያት ከስድስት ዓመት በፊት የተመረጠው “የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት” ወደ ሥራው እንዲመለስና አዲስ ፕሬዝዳንትና ካቢኔ እንዲሰይም ተወስኗል ብለዋል።
ቃል አቀባዩ፣ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ “ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ርክክብ” ካላደረጉ ስህተት እንደሚሆን ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለው የግንኙነት “ገመድ መበጠሱንም” ገልጸዋል። ህወሓት በ2012 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ “ታግዶ” የቆየ እንጂ “ያልፈረሰ” በመሆኑ ሕጋዊ ነው ሲል ይከራከራል። በአሁኑ ወቅት ክልሉ 40 በመቶ የሚሆነው መሬቱ በሌሎች ቁጥጥር ስር በመሆኑ አዲስ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻልና ብቸኛው አማራጭ የቀድሞውን ምክር ቤት መመለስ እንደሆነ ድርጅቱ ያምናል ብለዋል።
በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ የህወሓትን ውሳኔ በጽኑ በመቃወም፣ ድርጊቱ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚያፈርስና ወደ ጦርነት የሚመራ “መፈንቅለ መንግሥት” ነው ሲሉ ገልጸውታል። ፕሬዝዳንቱ የሚመሩት ካቢኔ መደበኛ ሥራውን እንደሚቀጥል ቢያስታውቁም፣ ህወሓት ግን ምክር ቤቱን ዳግም በማዋቀር አዲስ አስፈጻሚ ለመሰየም በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል። ይህ አዲስ ፍጥጫ በትግራይ ክልል ውስጥ “ሁለት መንግሥት” የመኖሩን ስጋት እያባባሰው ይገኛል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






