
ቦርከና ዜና
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በየደረጃው የሚገኙ የሀገር መሪዎችና የፖለቲካ ልሂቃን ሁሉ ፈሪሐ እግዚአብሔርን በልባቸው እንዲያሳድሩና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከመጨከን እንዲቆጠቡ በጥብቅ አሳሰቡ።
ፓትርያርኩ ይህንን መልእክት ያስተላለፉት ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረው ዓመታዊው የረክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ፓትርያርኩ በመልእክታቸው እንደገለጹት፣ በላዕላዊ፣ በማእከላዊና በታሕታዊ መዋቅር የምትገኙ የሀገር መሪዎችም ሆናችሁ አማራጭ ሐሳብ አለን ብላችሁ የምትንቀሳቀሱ ልሂቃን ሁሉ የሕዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ ይገባችኋል።
ሕዝቡ የሚፈልገው በአንድነትና በእኩልነት መኖርን፣ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ በሰላም ወጥቶ መግባትንና ለኑሮው የሚበቃ ምጣኔ ሀብት ማግኘትን መሆኑን የገለጹት አቡነ ማትያስ፣ እነዚህ መሠረታዊ ፍላጎቶች ሲሟሉለት ብቻ ሕዝቡ ተደመጥኩ ብሎ አመራሩን እንደሚከተል አስገንዝበዋል።
ሰውን መያዝ የሚቻለው በኃይል ሳይሆን የሰውን ሕሊና በማሳመንና በመርታት መሆኑን ያመለከቱት አቡነ ማትያስ፣ ማንኛውም ዓይነት ችግር በሰላም እና በሰላም ብቻ እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል።
ከሰላማዊ መንገድ ውጭ የሚደረጉ አማራጮች ሁሉ ለሀገር ዘላቂ ሰላም እንደማይበጁም በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የእርቅ ተልእኮዋን በሚጠበቀው ልክ መወጣት እንዳልቻለች የገለጹት ፓትርያርኩ፣ አሁን ያለውን ግጭትና መለያየት ለመቀነስ ሕዝቡን ወደ ፍቅርና ወደ ዘላቂ የጋራ ጥቅም ማምጣት የዚህ ጉባኤ ዋነኛ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለቀጣዮቹ ቀናት የሚቆየው ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ በሀገራዊ ሰላም፣ በቤተ ክርስቲያን አንድነትና በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






