
ቦርከና ዜና
ፓርቲው “ገዢው ፓርቲ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ተአማኒ ምርጫ ለማካሄድ እንዲሁም ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹና አስቻይ የፖለቲካ ምኅዳር ይፈጥራል የሚል እምነት ባይኖረንም የሕዝባችንን ድምፅ ለማሰማትና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ባህልን ለማስረጽ በፓርቲያችን ምክር ቤት ውሳኔ ወደ ምርጫው ገብተናል ” ብሏል
ጎጎት ፓርቲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ “21 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 82 ዕጩዎችን በ4 ክልሎች በማሰለፍ በምርጫው እየተሳተፍን ነው ” ሲል ገልጿል።
ይሁን እንጂ በተለይም በሁለቱ የጉራጌ ዞኖች ውስጥ በገዢው ፓርቲ አመራሮች አማካኝነት በርካታና ስልታዊ የሆኑ የምርጫ ሕግ ጥሰቶች እየተፈጸሙ እንደሆነ አመልክቷል።
ይፈፀማሉ ካላቸው ሕገ-ወጥ ድርጊቶች መካከል ዕጩዎችንና ቀስቃሾችን ማስፈራራት፣ የምርጫ ቅስቀሳ ባነሮችን መቅደድ፣ በራሪ ወረቀቶችን መልቀም፣ የዕጩዎችን ቤተሰቦች ማንገላታት፣ ከፓርቲው /ጎጎት/ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ዜጎች ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ማባረር መሆናቸውን ጠቁሟል።
በተጨማሪም ያለፈቃድ ፎቶና ቪዲዮ በመቅረጽ ማሸማቀቅ፣ የመንግሥትን ተሽከርካሪዎች ታርጋ ፈትቶ ለገዢው ፓርቲ ቅስቀሳ ማዋል፣ የፍርድ ቤት ዳኞችን ለፓርቲ ቅስቀሳ መጠቀም፣ ” አቅመ ደካሞች ናችሁ፤ እኛ እንመርጥላችኋለን ” በሚል ሰበብ ከምርጫው ዕለት አስቀድሞ የሕዝብን የምርጫ ካርድ ቤት ለቤት እየዞሩ እስከ መሰብሰብ የደረሱ እጅግ አሳሳቢ ጥሰቶች እንደሆኑ አመልክቷል።
ፓርቲው በየምርጫ ክልሉ ተፈጽመዋል ያላቸውን ግፎችና የሕግ ጥሰቶች ፓርቲው በዝርዝር አቅርቧል። እየተፈጸሙ ያሉ ሕገወጥ የማሰናከል ስራዎችና ሥርዓት አልበኝነቶች በአስቸኳይ ታርመው እልባት ካልተሰጣቸው ራሱን ከሀገራዊ ምርጫው ለማግለል እንደሚገደድ በመግለጫው አስታውቋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena






