
ቦርከና ዜና
በኢትዮጵያ የሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ፈረንሳዊቷ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ ኦገስቲን ፓሲሊ ከሀገር እንድትባረር የተደረገበትን ምክንያት በተመለከተ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ማብራሪያ ለመጠየቅ ጥረት ቢያደርግም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ አስታውቋል።
ኤምባሲው የጋዜጠኛ ኦገስቲንን ሁኔታ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ሚዲያ ባለስልጣን ጋር ለመገናኘት ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር መግለፁን መሰረት ሚዲያ ከኤምባሲው የመረጃ ምንጭ አገኘሁት ባለው መረጃ ተንተርሶ ዘግቧል።
ነገር ግን በተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢደረጉም ኤምባሲው ጋዜጠኛዋ ከተባረረችበት ምክንያት ጀርባ ስላለው ዝርዝር ጉዳይ እስካሁን ምላሽ ወይም ማብራሪያ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ በይፋ አስታውቋል።
ለፈረንሳዩ ታዋቂ የዜና አውታር ላ ክሯ እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ቆይታዋ ሰብአዊ ጉዳዮችን፣ የሱዳን ስደተኞችን ሁኔታ እና ማህበራዊ ቀውሶችን ስትዘግብ የነበረችው ፍሪላንስ ጋዜጠኛ ኦገስቲን ፓሲሊ ከሁለት ቀናት በፊት ከኢትዮጵያ መባረሯ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኛዋን ያባረሩበትን ዝርዝር ምክንያት እስካሁን በይፋ የገለፀው ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የጋዜጠኛዋን የመኖሪያ ፍቃድ እና የሚዲያ ዕውቅና በአስቸኳይ እንዲመልሱና ወደ ሀገር ውስጥ ገብታ ስራዋን እንድትቀጥል እንዲፈቀድላት ጠይቋል።
የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር አንጄል ኩንታል ጋዜጠኛዋ የተባረረችው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ተገኝታ ነዋሪዎች ወደ ጦርነት ልንመለስ እንችላለን በሚል ስላላቸው ስጋት የሰራችውን ዘገባ ተከትሎ የተወሰደ የበቀል እርምጃ ነው ብለዋል።
ባለስልጣናት በይፋ መወያየትና መፈተሽ የማይፈልጉትን የፖለቲካ እና የፀጥታ ጉዳይ በገለልተኝነት የዘገበችን ጋዜጠኛ በቁጥጥር ስልጣናቸው ተጠቅመው መቅጣታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
የጋዜጠኛ ፓሲሊ ከሀገር መባረር በሀገሪቱ ውስጥ ገለልተኛ በሆኑ የሀገር ውስጥና የአገር ውጭ መገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞች ላይ እየተወሰደ ካለው ተከታታይ እና ጠንካራ እርምጃ ጋር የተያያዘ መሆኑ ተገልጿል።
በድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የዓለም የፕሬስ ነፃነት መውጫ ጠቋሚ መሠረት የኢትዮጵያ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በማሽቆልቆል ላይ እንደሚገኝ ያመላክታል።
በተለይም በቅርብ ዓመታት በሀገሪቱ ከተቀሰቀሱት የውስጥ ግጭቶች የአንዳንዶቹ መጠናቀቅና አዳዲስ አለመረጋጋቶች መፈጠር ማግስት መንግስት መረጃዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርገው ጥረት መጨመሩን እና የሚዲያ ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መምጣቱን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ እያሳሰቡ ይገኛሉ።
_
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkenaየቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena






